Connect with us

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከምርጫ  ጋር ተያይዞ የመረጃ ነፃነት ህግ አተገባባርን  ክትትል ማድረግ ጀመረ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከምርጫ ጋር ተያይዞ የመረጃ ነፃነት ህግ አተገባባርን ክትትል ማድረግ ጀመረ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

ዜና

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከምርጫ  ጋር ተያይዞ የመረጃ ነፃነት ህግ አተገባባርን  ክትትል ማድረግ ጀመረ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከምርጫ  ጋር ተያይዞ የመረጃ ነፃነት ህግ አተገባባርን  ክትትል ማድረግ ጀመረ

 (በስድስተኛዉ ሀገራዊ ምርጫ የመረጃ ነፃነት ህግ ትግበራን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ   ተቋም የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ)

መረጃ ለሰው ልጅ ሀይል ነው፣ ሃብት ነው፤ ጊዜ ነው፡፡ በተለይም የዜጎችን የመወሰን አቅምን ለማጎልበትና ለማብቃት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ሃብቶች አንዱና ዋነኛው መረጃ ነው፡፡ መረጃ ያላቸው ሰዎች እንዳሉበት ሁኔታ እና በአቅማቸው ልክ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ብልሹ አሰራሮች እንዳይገነግኑ መረጃን መሠረት በማድረግ ያጋልጣሉ፡፡ የመረጃ ነጻነት ሲከበር ዜጎች በመንግስት አስተዳደር አካላት ላይ ጠንካራ እምነት ይኖራቸዋል፡፡ 

ስለሆነም የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ከመሆኑም በተጨማሪ ለሌሎች መብቶች መከበር መሠረት ስለመሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት መግለጫ (UDHR) እንዲሁም ኢትዮጵያ በፊርማዋ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) እና በአፍሪካ ህብረት የሰብአዊና የሰዎች መብት ቻርተር (ACHPR) ሰፊ እውቅና አግኝቷል፡፡ በዚህም የመረጃ ነፃነት ዓለም አቀፍ ህግ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆናቸው፤ የሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት የሚገለፀው ደግሞ ወቅቱን ጠብቆ በሚከናወን ነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ እና ሕዝቦች በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሣትፎ አማካይኝት እንደሆነ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት ተረጋግጧል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በማንኛውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው እና ምርጫው ሁሉ አቀፍ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሠረተና በሚስጢር ድምጽ አሰጣጥ መራጩ ሕዝብ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን እንዳለበት በሕገ-መንግሥቱ በግልጽ ተደንግጓል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘት እና የማሰራጨት መብት መሠረታዊ መብት መሆኑ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት እና በመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 የተረጋገጠ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነትና ዴሞክራሲያዊ ተሣትፎ እንዲሁም ለግልጽ የመንግሥት አሰራርና ተጠያቂነት መረጋጥ መሠረት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ 

በተጨማሪም ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት መከበር ለነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ተአማኒ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሠላማዊ ምርጫ እውን መሆን መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ስለመሆኑ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በማያሻማ መልኩ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግሥትም የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነትና ተሣትፎ ባረጋገጠ እና ዓለም አቀፍ የምርጫ መርሆዎችን በተከተለ መንገድ በየደረጃው በሚደረጉ ሁሉን አቀፍ ነጻ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫዎች ዜጎች በትክክለኛና በበቂ መረጃ ላይ በመመስረት በምርጫ ላይ እንዲሣተፉና ፈቃዳቸውን በእኩልነትና በነጻነት እንዲገልጹ ለማድረግ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ ዓላማና አመለካከታቸውን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለመራጩ ሕዝብ በመግለጽ በምርጫ የሚሳተፉበት የምርጫ ሥርዓት ለመዘርጋት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ በዚሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ህግ ላይ ሰፍሯል፡፡ 

ከምርጫ ጋር በተያያዘ ለሕዝብ የሚገለጹ የመረጃ ዓይነቶችና ፈጻሚ አካላትም በዚሁ አዋጅ በአብዛኛው ተለይተዋል፡፡ በእርግጥም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ህብረተሰብ የሚፈጠረው በመረጃ ላይ የተመሰረተ እውቀት ሲኖር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በመንግስታዊ አካላት ዘንድ የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት ተግባራዊ የሚደረገው አንድም መረጃ ጠያቂ ሲመጣ የተጠየቀውን መረጃ በመስጠት እና መረጃ ጠያቂ ባይመጣም የሕዝብን ጥቅም የሚመለከቱ መረጃዎችን በተለያየ የማሰራጫ ዘዴ አስቀድሞ ለሕዝብ በመግለጽ  (Proactive Disclosure of Information) ነው፡፡ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት ከምርጫ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና ባለድርሻ አካላት (Electoral Stakeholders) እጅ የሚገኙ መረጃዎች የሕዝብን ጥቅም የሚመለከቱ በመሆናቸው አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ ከሚደረጉት የመረጃ ዓነቶች ጎራ የሚመደቡ ናቸው፡፡ 

ምርጫ ቦርድም እንደማንኛውም መንግሥታዊ አካል በሕገ-መንግሥቱና በመረጃ ነጻነት አዋጁ መሠረት ለመረጃ ጠያቂ መረጃ የመስጠት ወይም የመከልከል እንዲሁም መረጃው የሕዘብን ጥቅም የሚመለከት በሆነ ጊዜ ደግሞ በተለያየ የማሰራጫ ዘዴ አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ሃላፊነት አለበት፡፡ በዚህም ምርጫ ቦርድ የመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 13 እና በተለይም የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጁ በሚያዘው አግባብ የምርጫ ሂደቱ ከተጀመረበት እለት ጀምሮ በርካታ መሠረታዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እያደረገ እንደሆኑ ተቋሙ ይገነዘባል፡፡ 

ይሁን እንጂ ከምርጫ ጋር የተያያዘ መረጃን አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ የማድረጉ ጉዳይ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘንድ በቂ ግንዛቤና ትኩረት አግኝቷል ማለት አይቻልም፡፡ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ  ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ዘንድ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ባለመቻሉ ለአሉባልታ ወሬና ለሀሰተኛ መረጃ መጋለጡ ልብ ይሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 13 መሠረት በመንግስታዊ አካላት ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ ስለታዘዙ መረጃዎች ዘርዝር ማብራሪያ የማዘጋጀት እንዲሁም የመረጃ ነጻነትን አፈጻጸም አስመልክቶ አሰራሮችን ለማዳበር እና ለማሻሻል የሚረዱ አጠቃላይና ወይም ዝርዝር የውሳኔ ሀሳቦችን ለመንግስታዊ አካላት የማቅረብ ሃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ 

ስለሆነም ተቋማችን ከምርጫ ጋር በተያያዘ በሰዎች መረጃ የማግኘት መብት ትግበራ ላይ የሚታዩትን ዋና ዋና ክፍተቶች እንዲሻሻሉ የውሳኔ ሀሳብ ለማቅረብ ይረዳው ዘንድ የክትትልና ድጋፍ ጋይድ ላይን አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በክትትልና ድጋፍ ወቅት በሚታዩት የአፈጻጸም ክፍተቶች ላይ እንደአስፈላጊነቱ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል የውሳኔ ሀሳብ የምናቀርብ ወይም በጋዜጣዊ መግለጫ ለሕዝብ ይፋ የምናደርግ ሲሆን ምርጫ ቦርድና ባለድርሻ አካላት ለተቋማችን የክትትልና ድጋፍ ባለሙያዎች ተገቢውን ትብብር እንድታደርጉ እንጠይቃለን፡፡

የምርጫ ተዋናዮችና የምርጫ መረጃ የማድረስ ሀላፊነት ያለባችሁ አካላትም በሙሉ የምርጫ መረጃዎችን የአካል ጉዳት ያለባቸዉንና ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ የቋንቋ ብዝሃነትን፣ የሀገሪቱን የቆዳ ስፋትና የህዝብ ቁጥር ታሳቢ በማድረግ በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች በመጠቀም የቅድመ- ምርጫ፣የምርጫ ዕለትና የድህረ- ምርጫ መረጃዎችን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ታደርጉ ዘንድ ከወዲሁ እናሳስባለን፡፡

ሚያዚያ 4 ቀን 2013 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top