Connect with us

#የኢዜማ_መግለጫ

#የኢዜማ_መግለጫ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

#የኢዜማ_መግለጫ

#የኢዜማ_መግለጫ

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ 

ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን መሠረት ለመጣል የሚጠይቀው መስዋዕትነት እጅግ ረጅምና መራር ነው፡፡ በተለይም እንደ አፍሪካ ውስጥ ባሉ በበርካታ ውስብስብ አሠራሮች በተተበተቡ አገሮች ውስጥ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ጥበት፣ ከፍተኛ የሥልጣን ጉጉትና የመሳሰሉት እንቅፋቶች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ቀይደው ይይዙታል፡፡ ድህነቱ፣ ኋላቀርነቱ፤ የዜጎች የፖለቲካ አረዳድ ወዘተ ችግሮቹን ይበልጥ ያባብሱታል፡፡

በተለይም በዘውግና በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የአገራችን የፖለቲካ ትርክት ላለፉት 30 ዓመታት ከአንድነት ይልቅ ልዩነቶቻችንን አግዝፎ በትውልዱ ላይ ቁርሾን ዘርቷል፡፡ ዛሬም ከዚህ የማንነት የፖለቲካ አዙሪት ለመላቀቅ አልቻልንም፡፡ 

ከዚህ የችግር አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የዜግነት ፖለቲካው ብርቱ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ነገም ብቸኛው አማራጭ መሆኑ ሊታመን ይገባል፡፡ 

አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ በተለያዩ የመንግሥት ቅርጽና የፖለቲካ ፍልስፍና በየጊዜው ሥልጣን ላይ በወጡ ኃይሎች ስትመራ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ 

ላለፉት 30 ዓመታት እስከ 6ኛው ዙር ምርጫ ድረስ በምርጫ ብቻ ሥልጣን ለመያዝ የተሞከረው ሒደት ተስፋ ሰጪ ባይሆንም ዜጎች  የምርጫ ተሳትፎ ማድረጋቸው አንድ ጥሩ እርምጃ ነው ሊባል ይችላል፡፡ 

ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሂደቱ እና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ የተገለፀ ባይሆንም በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ ነበር፡፡ 

ለዚህ ምርጫ ሰላማዊነትና የአገሪቱን የነገን ቀጣይነት በምርጫ ለማረጋገጥ፣ ዜጎች በምርጫው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ኢዜማ የበኩሉን ድርሻ በኃላፊነት ተወጥቷል የሚል የፀና እምነት አለን፡፡ ከምንም በላይ ለአገር መረጋጋትና ለሕዝብ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነትም በተግባር አስመስክሯል፡፡  

በመሆኑም ለቀጣይ የኢዜማ መዋቅር አደረጃጀት ለፓርቲያችን ደጋፊዎች፣ አባላትና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች የሚከተሉትን ማሳወቅ ይኖርብናል፡፡ 

1ኛ/ ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው የ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት እስከሚገለጽ የምንጠብቅ ሲሆን ቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ኢዜማ በተወዳደረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙትንና በየሰዓቱ ለምርጫ ቦርድ ያሳወቅናቸው በርካታ ተግዳሮቶችን በአጽንኦት ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍትህ አካላት ይዘን የምንሔሄድበትን ሁኔታ ቀድመን ለሕዝብ የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

2ኛ/ ኢዜማ የምርጫ 2013 አጠቃላይ የፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ የሚያስተባብር የምርጫ ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ኮሚቴ ከአመት በፊት አዋቅሮ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ይህ ኮሚቴ አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት በተመለከተ ከሚያዘጋጀው የግምገማ አጠቃላይ ሪፖርት፣ በድርጅት በኩል፣ በብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተቋቋመ ቡድንና ከፓርቲው ውጪ በተመረጡ ገለልተኛ አካላት ከሚቀርበው ግምገማ ተነስተን አጠቃላይ ሁኔታውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንገልጻለን፡፡ 

3ኛ/ እንደሚታወቀው የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ ትግል ቀጣይነት ያለውና ከምርጫ በኋላም ቢሆን ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ እሙን ነው፡፡

በዚህ ረገድ ኢዜማ ጊዜያዊ ፓርቲ ሳይሆን ገና ከመነሻው ከምርጫ ወረዳ ጀምሮ ሲዋቀር ሩቅ ተጓዥና ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ሆኖ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በምርጫው ሒደት ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በሕግ አግባብ እየጠየቅን ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የድርጅቱን መዋቅር ይበልጥ በማጠናከር ወደ ሥራ የገባን መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ 

4ኛ/ ኢዜማ በተቋቋመ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከየትኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ በላቀ መልኩ በመላው አገሪቱ 455 የምርጫ ወረዳ መዋቅሮችን አደራጅቶ በጥንካሬ እየተንቀሳቀሰና በምርጫ 2013 ገዢውን ፓርቲ በብርቱ የሞገተ ፓርቲ ነው፤ ሕዝባዊ መሠረቱም ሰፊና ጠንካራ ነው፡፡ 

ከዚህ አንጻር የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች በምርጫ ሂደት የተገኘውን ውጤት፣ ልምድ፣ የሰው ኃይል፣ ልዩ ልዩ ግብዓቶች እና ወዘተ የመሳሰሉትን ፓርቲውን ይበልጥ ለማጠናከር መጠቀምና ድርጅቱን በጥንካሬ ለመምራት በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ ብርቱ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና በቀጣይ ለሚያጋጥሙን አገራዊ ጉዳዮችና ሰላማዊ ለሆኑ የትግል እንቅስቃሴዎች ራሳችንን እንድናዘጋጅ የከበረ ጥሪ ማስተላለፍ እንሻለን፡፡ 

ኢዜማ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም ከምርጫ መቃረብ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መፍትሄ ሰጪ ፖሊሲዎችን የነደፈ፣ ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ያሳወቀ፣ የምርጫ ቅስቀሳዎችን በሰለጠነ መንገድ ያካሄደ፣ ማኅበራዊ ፍትህ ለማስፈን መሠረቱን ዜግነት ላይ ያደረገ ፓርቲ መሆኑንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ላይ የራሱን ተሳትፎ እንዳደረገ እናምናለን፡፡ 

በመጨረሻም ነገም ኢትዮጵያ አገራችን ሉዓላዊ ግዛቷና የሕዝብን ደህንነት ተጠብቆ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሳት ጠንካራ አገር እንድትሆን ኢዜማ ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ሆኖ በጥንካሬ እንደሚቀጥል እየገለጽን በፀሐይና በዝናብ ወስጥ፤ ቀንና ለሊት ተሰልፋችሁና በብርቱ ጫናና መዋከብ ውስጥ ሆናችሁ ድምጻችሁን ለኢዜማ የሰጣችሁትን ከልብ እያመሰገንን ያልመረጣችሁንንም ውሳኔያችሁን የምናከብር መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top