“ከዋልድባ ገዳም የመጣሁ ባህታዊ ነኝ” ባዩ ሴራ
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ተበዳይ አትጠገብ መኮንን የእራሷን እና የቤተሰቦቿን ኑሮ ለማሻሻል ወደ አረብ ሃገር በመሄድ ጥቂት ገንዘብ አፍርታ ወደ ምትወዳት ሃገሯ ኢትዮጵያ ከተመለሰች ሰነባብታለች ። አረብ ሃገር በነበረችበት ወቅትም ከተከሳሽ ሱራፌል ደሴ ጋር አብሮ አደግ እና ወዳጅ ስለነበሩ በማህበራዊ ሚዲያ እና በስልክ አልፎ አልፎ ይጠያየቃሉ፡፡ በሂደት ተከሳሽ ሱራፌል ለአትጠገብ መኮንን የፍቅር ጥያቄ ቢያነሳም አጥጋቢ መልስ ሳያገኝ ይቀራል፡፡ ተከሳሽ ሱራፌል የ28 ዓመት ወጣት ነው ።
ታድያ አንደ ቀን በድልበር መድሐኒአለም ቤተክርስቲያን እንደአጋጣሚ ሆኖ ሱራፌል እና አትጠገብ ነጠላቸውን ለብሰው ይገናኛሉ። በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ጊቢ ውስጥም ተቀምጠው መጫዋወት ይጀምራሉ። ተከሳሽ ሱራፌልም አብሮ አደጉ ሆነችውን ተበዳይ አትጠገብን ከውጭ ሃገር ከመጣሽ እኮ ብዙ ጊዜ ሆነሽ ለምን ስራ አትጀምሪም ሲል ይጠይቃታል፡፡ አትጠገብም በእጄ ላይ ያለው ገንዘብ ስራ ለመጀመር ስለማያስችለኝ ሌሎች አማራጮችን እያየሁ ነው ስትል ትመልስለታለች። ይሄኔ ነው እንግዲህ ተከሳሽ ሱራፌል ሲያስበው እና ሲመኘው ለነበረው የማታለል ሴራው መንገዱ ወለል ብሎ የተከፈተለት።
እናም ሱራፌል የማሳመን እና የማታለል ሴራውን እኔም እኮ እንደአንች ነበርኩኝ፡፡ እጄ ላይ የነበረውም ጥቂት ገንዘብ ነበር፡፡ እጅግ በጣምም ከጭንቀት ብዛት እያመመኝ እቸገር ነበር፤ አንዱ ጓደኛዬ ነው ከዋልድባ ገዳም የመጡ አባት አገናኝቶኝ ጤናዬ ተመለሰ ያለኝን ገንዘብ፣ ወርቅና ብሮቼን ለእሳቸው አስባርኬ ገንዘቤም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ሆነልኝ አንችንም ከእሳቸው ጋር ላገናኝሽ እና ንብረትሽን አስባርኪ እኔም ሁለት መቶ ሺህ ብር እጨምርልሽና የፈለግሽውን አይነት ሥራ ትሰሪበታለሽ አላት።
በአብሮአደጓ የፍቅር ጥያቄ ባነሳላት እና በቤተክርስቲያን ቅጥር ጊቢ ውስጥ መሆኑ እምነት እንድትጥል ያሳደራባት አትጠገብ ፍቃደኝነቷን ታሳውቃለች።
ተከሳሽም ከዋልድባ ገዳም የመጡ አባት ናቸው ወደተባሉት አባት ወይም ተከሳሽ ንብረቱ ግዛቸው ሱራፌል በራሱ ስልክ ይደውል እና “አባን” አናግሪያቸው ብሎ ስልኩን ለተበዳይ ይሰጣል፡፡ ተበዳይም የዋልድባ አባት ለተባለው ሰው ያለውን ነገር በሙሉ በዝርዝር መናገሯን ለዐቃቤ ህግ በዝርዝር ስታስረዳ ከዋልድባ ገዳም የመጡ አባት ናቸው የተባሉት አባት ወይም ተከሳሽ ንብረቱ ግዛቸው 4 ኪሎ በሚገኘው ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ነገ 4፡00 ሰዓት ላይ አብራችሁ እንድትመጡ አሱ ያለሁበትን ቦታ ስለሚያውቀው እሱ ይዞሽ ይምጣ ተባልኩኝ ትላለች አትጠገብ።
ከዋልድባ የመጡት አባት የተባሉት ወይም ተከሳሽ ንብረቱ ግዛቸው ገና የ29 ዓመት ወጣት ነው።
በተባልነው ጊዜ እና ቦታ ስንደርስ የተባሉትን አባት ማግኘት ባለመቻላችን ስልክ ደውለን አባባ መጥተን እኮ አጣንዎት ስንላቸው አይ ልጆቼ ስትዘገዩብኝ እኮ እንደእናንተ የሚፈልጉኝ ሰዎች ነበሩ ወደ እነርሱ ሄጀ ነው፡፡ መቼም ለመልካም ነገር መድከም ጥሩ ነው፤ በል ልጄ ሱራፌል ወደ ጎላ ሚካዔል ይዘሃት ና ሲሉን ተያይዘን ጎላ ሚካዔል ሄድን በቦታውም ስንደርስ የባህታዊ ልብስ የለበሱ መስቀል የያዙ አባት አገኘን ጉልበታቸውን ተንበርክኬ ስሜ መስቀል ተሳልሜ ተቀመጥን ።
የ29 ዓመት ወጣት የሆነው ተከሳሽ ንብረቱ ድርሳነ ገብርዔል በእጃቸው ይዘዋል ትላለች፡፡ ተበዳይ ለዐቃቤ ህግ ክሱን ስታስረዳ በመቀጠልም ምንድን ነው ፍላጎትሽ ተብዬ ተጠየቁኩ፡፡ ስራ መስራት እፈልጋለሁ ወደ ውጭ ሃገር መሄድም እፈልጋለሁ አልኳቸው፡፡ በይ ሂጅ እና ሁለት ቅጠል ይዘሽ ነይ ሲሉኝ ሁለት ቅጠል በማምጣት ሰጠኋቸው ቅጠሉንም በመፅሐፉ ውስጥ አስቀምጠው አስር ብር እንድሰጣቸው ጠየቁኝ ሰጠኋቸው፡፡ ብሩንና ቅጠሉን በመፅሐፉ ውስጥ አንድ ላይ አድርገው የኔ ልጅ ይሄ ከተቀየረ ህይወትሽ ይቀየራል ካልተቀየረ ግን እንደዚህ ሆነሽ ነው የምትቀሪ ስለት ግን መሳል አለብሽ ስለትሽ ከሰመረ ለሚካዔል ሃምሳ ሺህ ለገብርዔል ሃምሳ ሺህ ብር ታስገቢያለሽ ተባልኩኝ እሽ ብዬ መፅሀፉን ስገልጠው ሁለቱ ቅጠል ሁለት መቶ ብር ሆኖ አገኘሁት።
እጅግ በጣም ስለደነገጥኩ ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ ስቆም ተቀመጭ ሕይወትሽ ከዚህ በኋላ ተቀይሯል ተባልኩ።
አባ ወይም ተከሳሽ ንበረቱ እኔ እግዛብሔር በሰጠኝ ፀጋ ሰዎችን አገለግላለሁ እንጅ ከአንች ምንም አልፈልግም አሁን እቤትሽ ሄደሽ ነገ ማለትም የካቲት 25/2012 ዓ.ም መሆኑ ነው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሳለሚያ እህል በረንዳ አካባቢ ለዘቢብ እና ለሽቶ መግዣ የሚሆን ስድስት ሺህ ብር እንዲሁም እንዲፀለይበት እና እንዲባረክ የምትፈልጊያቸውን ጥሬ ገንዘብ እና ንብረቶችሽን በሙሉ ይዘሽ ነይ ስባል በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው ከአራባ ሰባት ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ጥሬ ገንዘብ፣ የወርቅ ብራስሌት እና የአንገት ሐብሌን ከታናሽ ወንድሜ ጋር በመሆን ይዘን ሄድን ትላለች ተበዳይ አትጠገብ ስታስረዳ ።
በቦታውም ስንደረስ ግቡ ተብለን ሁለት ሻማ አብሪ ተባልኩ፤ አበራሁ፡፡ ነጠላሽን ልበሽ ተባልኩ፤ ለበስኩ፡፡ ታናሽ ወንድሜም ከውጭ እንዲቆይ ተነገረው እና ከቤት ውጭ እንዲጠብቅ ተደረገ፡፡ ያለኝን ንብረት ከሰጠሁ በኋላ አሁን አይንሽን ጨፍኝ እና አንችም እኔም እንጸልያለን ተባልኩኝ፤ ያለማቋረጥ እያነባሁ ፀለይኩ።
ልጄ በይ በቃሽ አሁን ይሄን ገንዘብ ሳትከፍች ወስደሽ ትራስሽ ውስጥ ታሳድሪው እና ነገ ባንክ ወስደሽ አስቀምጭው ብለው በቤተክርስቲያን ጨርቅ የተጠቀለለ የታሸገ ገንዘብ መሳይ ነገር ሰጡኝ፡፡ እሽ አመሰግናለሁ አባ ብዬ ስወጣ ታናሽ ወንድሜ ወዲያውኑ የታሸገውን ገንዘብ ከእኔ ቀምቶ ተቀብሎኝ ከፍቶት ስናየው የተጠቀለለ ወረቀት ብቻ ሆኖ አገኘነው።
ወንድሜም እኔ ሳላውቅ በዙርያችን ፖሊሶችን አዘጋጅቶ ስለነበር ከዋልድባ ገዳም መጣሁ፤ ባህታዊ ነኝ ባዩ ንብረቱ እና አብሮአደጌ ሱራፌል በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደረገ ትላለች ተበዳይ አትጠገብ ።
የክስ መዝገቡ የመጣለት ዐቃቤ ህግም ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1)(ሀ) እና 692 (1) ተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፋቸው ዝርዝር የሰው፣ የሰነድ እና የኢግዚቪት ማስረጃዎችን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በማቅረቡ ፍርድ ቤቱ ህዳር 18/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾችን ያርማል መሰል አጥፊዎችንም ያስተምራል በሚል ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።(የፌ/ጠ/ዐቃቤ ሕግ)