በመንግሥት ላይ የ280 ሚሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ የትምህርት ሚኒስቴር ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
በትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሠራተኞች፣ በመንግሥትና ሕዝብ ላይ የ280 ሚሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የተጠቀሰውን ያህል ጉዳት ያደረሱት በ2009 ዓ.ም. ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የእንግሊዝኛ መጻሕፍት ለማሳተም ወጥቶ ከነበረ ጨረታና ሕትመት ክፍያ ጋር በተያያዘ መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ከዓለም ባንክ በተገኘ ዕርዳታ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የእንግሊዝኛ መጽሐፍትና የመምህራን መመርያ (ጋይድ ላይንስ) መጻሕፍት አሳትሞ ለማከፋፈል፣ ጨረታ አውጥቶ እንደነበር የፖሊስ ምርመራ ያስረዳል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የጨረታ ሒደት የግዥ ኮሚቴ ሆነው ሲሠሩ ከተጫራች ድርጅቶች ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ በግዥ ሒደቱ የመንግሥትን ጥቅም ያላስከበረ ጨረታ ማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡ በዚህም በመጻሕፍቱ የገጽ ብዛት ክፍያ በመፈጸም ከተገባው ውል ውጪ የገጽ ብዛት ታሳቢ ሳያደርጉ፣ መጻሕፍቱን በቁጥር ብቻ መቀበላቸውንም የምርመራ ሒደቱ ይጠቁማል፡፡
በውሉ ውስጥ ለግዥ ከቀረበው የገጽ ብዛት አሳንሶ (ቀንሶ) በማሳተምና እንዲቀርብ በማድረግ፣ በመንግሥት ላይ የ217 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም መጻሕፍቱ በ140 ገጽ ታትመው እንዲቀርቡ ክፍያ ከተፈጸመ በኋላ ከውል ውጪ 80 ገጽ ብቻ የያዘ መጻሕፍት እንዲታተም ማድረጋቸውንም ጠቁሟል፡፡ የጥራት ደረጃ ከተገባው ውል ውጪ ሽፋኑ ውኃ የማያበላሸው መሆን ሲገባው፣ ያልሆነ መሆኑንና የመጻሕፍቱ የጀርባ መስፊያ በክር መሆን ሲገባው በብረት ኮርቻ እንዲሰፋ በማድረግ ተጨማሪ የ63 ሚሊዮን ብር ጉዳት ማድረሳቸውንም አብራርቷል፡፡
ፖሊስ አራት የሚኒስቴሩ ሠራተኞችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት በማቅረብ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ለፖሊስ 12 ቀናት በመፍቀድ ለመስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡(ታምሩ ፅጌ ~ ሪፖርተር)