Connect with us

በመተከል ዞን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሁለት ብሔሮች ላይ ያነጣጠረ ነው መባሉን ክልሉ አስተባበለ

በመተከል ዞን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሁለት ብሔሮች ላይ ያነጣጠረ ነው መባሉን ክልሉ አስተባበለ

ወንጀል ነክ

በመተከል ዞን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሁለት ብሔሮች ላይ ያነጣጠረ ነው መባሉን ክልሉ አስተባበለ

በመተከል ዞን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሁለት ብሔሮች ላይ ያነጣጠረ ነው መባሉን ክልሉ አስተባበለ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መተከል ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ሰሞኑን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የማረጋጋትና የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ የመከላከያ ሠራዊት የፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል በጋራ እየሠሩ መሆኑን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ፡፡

በዞኑ ቡለንና ወምበራ ወረዳ አንዳንድ ቀበሌዎች ሠሞኑን በጸረ-ሠላም ኃይሎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ወደ አንጻራዊ ሠላም በመመለስ ላይ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል፡፡

የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባያታ ከጽ/ቤታችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ጸረ-ሠላም ኃይሎች በመተከል ዞን ወምበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ እና በቡለን ወረዳ ኤጳር ቀበሌ በፈጸሙት ጥቃት የንጹኃን ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡

አቶ አበራ፣ የክልሉ መንግስት በድርጊቱ ጥልቅ ኃዘን እንደተሰማው በመግለጽ፣ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሠቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

ጥቃት አድራሾቹ ቀደም ሲል በወምበራ ወረዳ ኮንግ ማዕከል “የብልጽግና ፓርቲ እና የመንግስት ደጋፊ ናችሁ” በሚል በህብረተሰቡ ላይ የግድያ፣ የማገት እና የማፈናቀል ድርጊቶችን መፈጸማቸውን አስታውሰዋል፡፡

በሃምሌ ወር ደግሞ በጉባ ወረዳ ያቡሉ ቀበሌ በንጹኃን ዜጎች ላይ መሠል ጥቃት አድርሰዋል ያሉት ኃላፊው፣ በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስና በክልሉ የጸጥታ ኃይል በተወሰደባቸው እርምጃ አብዛኞቹ የተደመሰሱ ሲሆን፣ 168 አባላቶቻቸውና ግብረ-አበሮቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታዬ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ ጸረ-ሠላም ኃይሎች ከሳምንት በፊት ደግሞ በወምበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ ገብተው 36 የሚሆኑ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የቀበሌ አመራችንና ሚሊሻዎችን፣ እንዲሁም ታዋቂ ሰዎችን አግተው ድብደባ የፈጸሙ ሲሆን፣ አስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ እና ከብቶችን እንዲሰጧቸው ሲያስገድዱ እንደነበር ነው አቶ አበራ የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይ ጳጉሜ 1/2012 ዓ.ም ከሌሊቱ 8፡00 ሠዓት ገደማ በቡለን ወረዳ አጳር ቀበሌ ገብተው ባደረሡት ጥቃት የንጹኃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ኤጳር ቀበሌ ማዕከልን ጨምሮ በዞኑ የጸጥታ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ችግሩ በተፈጠረ ማግስት ወደ ቦታው መድረሳቸውን የገለጹት አቶ አበራ፣ ጸጥታውን የማረጋጋትና የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ችግሩን ለማረጋጋትና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ተገኝተው እየሰሩ መሆኑን በመጠቆም፣ የሠላም ውይይቶች በተለያዩ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

በስጋት ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ማዕከሉ እየተመለሱ ስለመሆናቸውም ነው አቶ አበራ ጨምረው የገለጹት፡፡

የቤኒሻንጉል እና የአማራ ክልል መንግስታት ለሁለቱ ክልል ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንዲሁም በቀጠናው ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን ከዚህ ቀደም የጀመሯቸውን ተግባራት የበለጠ በማጠናከር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡

እየተሠሩ ካሉት የማረጋጋት ሥራዎች ጎን ለጎን በስጋት ምክንያት ከቤታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊ የሰብዓዊ ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የተፈጸመውን ጥቃት በ2 ብሔሮች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያ እየተገለጸ ያለው መረጃ ፍጹም ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጸው፣ ጸረ-ሠላም ኃይሎቹ ጥቃት ያደረሱት “ከእኛ ሀሳብ በተቃራኒ ቆማችኋል” ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እንጂ ብሔርን መሠረት ያደረገ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም በማህበራዊ ሚዲያ በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ እየተገለጸ ያለው አሃዝ መሠረተ-ቢስ ነው ያሉት አቶ አበራ፣ የሟቾችን ቁጥርም ሆነ የደረሰው የጉዳት መጠን ትክክለኛ መረጃ በመጣራት ላይ ሲሆን በቅርቡ ለህብረተሰቡ ይገለጻል ብለዋል፡፡

“አንዳንዴ ሞተዋል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጠፍተዋል” ሲባሉ የነበሩ 27 ሰዎች ተገኝተው ወደ ቤተሰቦቻቸው መቀላቀላቸውንም ኃላፊው አንስተዋል፡፡

በክልሉ በተለይም ለውጡን ተከትሎ ከመጣው የፖለቲካ ስነ-ምህዳር መስፋት ጋር ተያይዞ ጥምረት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱት ቦዴፓ፣ ቤህኔን ሰዴድ እና ጉህዴን የፖሊቲካ ድርጅቶች ህግን አክብረው ከመንቀሳቀስ ይልቅ፣ እየተጓዙበት ያለው ህገ-ወጥ አካሄድ ህብረተሰቡን ውዥንብር ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ጉህዴን ወጣቶችን “የደርጅቱ ወታደሮች ትሆናላችሁ” በሚል ግልጽ ቅስቀሳ ሲያደርግና መልምሎ ሲያሰለጥን እንደነበር ነው የገለጹት፡፡

ሠላም ወዳዱ ሕዝብ እነዚህ ጸረ-ሠላም ኃይሎች የያዙት እኩይ ዓላማ እንዲመክን ከማድረግ ባሻገር፣ የክልሉ መንግስት ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር እየሠራ ላለው ህግ የማስከበር ሥራ የተለመደ ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ አበራ ጥሪ አቅርበዋል::

(ምንጭ፡- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት)

Click to comment

More in ወንጀል ነክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top