Connect with us

ኢዜማ በአዲስአበባ ታይቶ የማይታወቅ የመሬት ወረራ እና የኮንደምኒየም እደላ መካሄዱን በጥናት አረጋገጠ

ኢዜማ በአዲስአበባ ታይቶ የማይታወቅ የመሬት ወረራ እና የኮንደምኒየም እደላ መካሄዱን በጥናት አረጋገጠ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ኢዜማ በአዲስአበባ ታይቶ የማይታወቅ የመሬት ወረራ እና የኮንደምኒየም እደላ መካሄዱን በጥናት አረጋገጠ

በአዲስ አበባ ከተማ ታይቶ በማይታወቅ መጠን እና ስፋት ግልፅ የሆነ የመሬት ወረራና ሕገ-ወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ እንደተካሄደ ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትኅ ፓርቲ (ኢዜማ) ተናገረ፡፡

ኢዜማ ዛሬ ይፋ ባደረገው የጥናት ግኝት ሪፖርት፣ ‹‹የከተማው አስተዳደር እያየና እየሰማ በሕገ ወጥ እና በተደራጀ መልኩ በወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታ እና ፕላን ተሠርቶላቸው ለ3ተኛ ወገን በሽያጭ ተላልፈዋል በማኅበር እና በግል፣ ለማምረቻና ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉም ተደርገዋል›› ብሏል፡፡

‹‹በዋናነት የመሬት ወረራው ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ‹ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን መሬቶች ናቸው› እና ‹በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል› የሚሉ ግለሰቦች እና ወረራ በተፈፀመባቸው ቦታዎች አካባቢ የሚገኙ የክፍለ ከተማና የወረዳ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች ናቸው›› ሲል የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ‹‹ጉዳዩን በማፋጠን ሕገ-ወጥ ደላላዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ›› ብሏል፡፡
‹‹በጠራራ ፀሐይ፣ በተደራጀ መልኩ የተፈፀመው የመሬት ወረራ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ባሉ አመራሮች እና የፍትህ አካላት ተጠሪዎች ከፍተኛ እገዛ የተደረገበት ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ አካላት የጉዳዩ ዋና ተዋንያን የነበሩበት ነው›› ብሏል ኢዜማ ይፋ ያደረገው የጥናት ግኝት ሪፖርት።

‹‹በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮችና የፍትህ አካላት ተጠሪዎች በተለያየ መልኩ ሊጠቅሟቸው ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና አደረጃጀቶች መሬቱን ወርረው እንዲይዙ አመቻችተዋል፣ የመንግሥትን ሥልጣን ለሕገ-ወጥ ተግባር ከለላና ሽፋን አድርገው ተጠቅመዋል፤ ከዚህም ባስ ሲል ከግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ራሳቸው ወረራ ፈፅመዋል›› ብሏል ሪፖርቱ።

‹‹ሕገ-ወጥ የሆኑ የግንባታ ፈቃዶች፣ ካርታ እና ልዩ ልዩ ሰነዶችን ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በማዘጋጀት ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ሕጋዊ መስለው እንዲቀርቡ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋልም›› ብሏል።

‹‹በአጠቃላይ በመሬት አስተዳደር በግንባታ ፈቃድ እና በደንብ ማስከበር እንዲሁም በፀጥታ መዋቅር ውስጥ ባሉ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች ግዴለሽነት እና የወንጀል ተባባሪነት ከፍተኛ የህዝብ ሀብት ተዘርፏል›› ብሏል የጥናቱ ግኝት ሪፖርት።

‹‹ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ተግባር በሀገራችን አዲስ ያልሆነና በተለያዩ ጊዜዎችና አካባቢዎች ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየ መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ ግን በዚህ ደረጃ እና ፍጥነት የተስፋፋበት ጊዜ አልነበረም›› ብሏል፡፡

‹‹የመሬት ወረራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች እንደሚስተዋለው በአገልግሎት ላይ የሚውሉት ቦታዎች ስፋት ከፍተኛ ከመሆናቸውም በላይ ወረራው የከተማ አረንጓዴ ቦታዎችን፣ የወንዝ ዳርቻዎችን እንዲሁም ለመሠረተ ልማት አውታር ዝርጋታ በፕላን የተከለሉ ቦታዎችን ያካተተ በመሆኑ የጉዳቱን መጠን ከፍተኛ አድርጎታል›› ብሏል፡፡

‹‹ከጋራ መኖሪያ ቤት ጋር በተገናኘም በግልፅ የታየው የመንግሥት ሕገ-ወጥ ተግባር ነው›› ያለው ሪፖርቱ፣ ‹‹ኢ-ፍትሐዊ ሕጎችን እና መመሪያዎችን በማውጣትና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሕጎችን እና ደንቦችን በማሻሻል ለካቢኔውና ለከንቲባው በተሰጠ ልዩ ሥልጣን (መመሪያ ቁጥር 1 እና 2/2011፣ ክፍል 2 አንቀጽ 12/2) ከንቲባውም ሆኑ ካቢኔያቸው ቤቶችን እንደፈለጉ እንዲያድሉ ምክንያት ሆኗል›› ሲል አክሏል።

‹‹በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ፈፅሞ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤት የማስተላለፍ ተግባር እንደፈፀመና እየፈፀመ መሆኑን አረጋግጠናል›› ብሏል የኢዜማ የጥናት ግኝት ሪፖርት።

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ያለበትን ከፍተኛ ድክመትና የተንሰራፋውን ሙስና ዋነኛ ማሳያ የሚሆነው መስከረም 2012፣ 5000 ቤቶችን ለግንባታ አቅዶ በበጀት ዓመቱ ምንም የተገነባም ሆነ ግንባታቸው የተጀመረ ቤቶች አለመገኘቱ ነው›› ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ከአሁን ቀደም በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ቦታ እና ኮንዶሚኒየም ቤት የተሰጣቸው መሆኑን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ደግሞ ድጋሚ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየታደሏቸው መሆኑን አረጋግጠናል›› ብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄደው የመሬት ወረራ በብዙ የከተማው አካባቢዎችና ሰፋፊ መሬቶችን ዒላማ ያደረገ በተናጠል የሚደረግ ሳይሆን በተቀናጀ መልኩ የሚፈፀም እንደሆነ በጥናቱ ተረጋግጧልም ተብሏል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ታስቦ የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከታሰበለት ጊዜ በጣም ዘግይቶ ችግሩን መቀነስ አለመቻሉ ሳያንስ ቤቶቹን ለመረከብ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከ15 ዓመታት በላይ የቆጠቡ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤት ሳያገኙ ግንባታቸው ያለቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላልተመዘገቡ እና ቁጠባ ላልፈፀሙ ሰዎች ተላልፈው እየተሰጡ መሆኑን በጥናት ደርሼበታለሁ ብሏል ኢዜማ።

በሥልጣን ላይ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍ የወጣውን መመሪያ በመቀየር በግለሰብ ትዕዛዝ ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ በጥናቱ ተረጋግጧልም ብሏል።

እነዚህ ሕገ-ወጥ ተግባሮች ያላቸው ተፅዕኖ ዛሬን የሚሻገር፣ ለነገም የሚተርፍ እና የህብረተሰቡን ቀጣይ ሕግን የማክበር ባሕሪ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ በመሆኑ ጥፋቱ የከፋ ነው ብሏል የጥናቱ ሪፖርት፡፡
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በጥናቱ የተገኙ ውጤቶችና ድምዳሜዎችን ተመልክቶ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር የጠየቀው ኢዜማ፣ የመሬት ወረራውና ከሕግ አግባብ ውጪ የተካሄደው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ባለስልጣናት እጅግ ሲከፋ ቀጥተኛ በሆነ የጥቅም ተጋሪነት ሲያንስ ደግሞ ኃላፊነታቸውን በትክክል ካለመወጣት በተሰጠ ሽፋን የተፈፀመ በመሆኑ፣ በዚህ ተግባር ውስጥ እጃቸው ያለበት ኃላፊዎች ላደረሱት ጉዳትና ለፈፀሙት ወንጀል በሕግ የሚጠየቁበት ሥርዓት ሊበጅ ይገባል ብሏል፡፡(ሸገር)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top