የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደማይራዘም ተጠቆመ
ነባር ሕጎችና አዲስ የሚወጡ መመርያዎች በምትክነት ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሏል
የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል የወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳይራዘም፣ በዚህ አዋጅ ምትክም ነባር አዋጆችንና እነሱን መሠረት አድርገው የሚወጡ አዳዲስ መመርያዎችን በመጠቀም የቫይረሱ ሥርጭትን ለመቆጣጠር መታቀዱ ተጠቆመ።
መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ታውጆ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወሰነለት የአምስት ወራት ዕድሜ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ቢሆንም፣ አዋጁ የወጣበት የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ በጨመረበት በዚህ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘም አስፈላጊ እንዳልሆነ መንግሥት ማመኑን ሪፖርተር ከምንጮቹ ለመረዳት ችሏል።
በአማራጭነትም በሥራ ላይ ያሉ ነባር አዋጆችንና እነዚህን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ ደንቦችንና መመርያዎችን በማውጣት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታለመውን የቫይረሱ ሥርጭትን የመግታት ዓላማና ሚና በመተካት ጥቅም ላይ እንዲውሉ መታቀዱን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከታሰቡት ነበር አዋጆች መካከል የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጁና ሌሎች የማኅበረሰብ ጤናን የሚመለከቱ አዋጆች እንደሚገኙ የጠቀሱት ምንጮቹ፣ በትምህርት ዘርፉ የቫይረሱ ሥርጭትን ለመከላከል ራሱን የቻለ የኮሮና መመርያ እንዲወጣ መታቀዱን ጠቁመዋል።
እነዚህን አዋጆች መሠረት በማድረግም የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ጊዜያዊ መመርያዎችን በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይሰጥ የነበረውን ፋይዳ ማግኘት እንደሚቻል መታመኑንም ምንጮቹ አመልክተዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአምስት ወራት የጊዜ ገደብ የወጣ መሆኑንና ይህ የጊዜ ገደብም በመጪው ቅዳሜ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል። ፓርላማው ሊሰበሰብ የሚችለው አዋጁን ለማራዘም እንደሆነ የጠቀሱት ምንጮቹ፣ ጊዜው ተጠናቀቀ ማለት አዋጁ ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም ማለት እንደሆነና ለዚህ ተብሎ ፓርላማው ሊሰበሰብ እንደማይችል ገልጸዋል።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፀደቀበት ወቅት የአዋጁን አፈጻጸም እንዲከታተል በፓርላማ የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ፣ በአዋጁ አፈጻጸም ላይ ያደረገውን ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የተመለከተ ምክረ ሐሳቡን ለመንግሥትና ለፓርላማው እንዳቀረበ ታውቋል።
ቦርዱ ባቀረበው ምክረ ሐሳብም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት ሲያበቃ መንግሥት የሚያደርገውን የመከላከል እንቅስቃሴ የሚደግፉ ሕጋዊ አሠራሮች አስቀድመው ካልታዩ፣ ለኮሮና ቫይረስ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን በሕግ ለመቆጣጠር ክፍተት ሊፈጠር ይችላል ማለቱ ተሰምቷል።
አዋጁን ተክተው ተግባራዊ የሚደረጉ የሕግ ማዕቀፎች ከወዲሁ መለየት እንደሚገባቸውም ባቀረበው ምክረ ሐሳብ አሳስቧል። በተለይም ከነሐሴ መጨረሻ እስከ መስከረም 2013 ዓ.ም. ማገባደጃ ድረስ በርካታ ሰዎችን የሚያሰባስቡ ብሔራዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት በመኖራቸው፣ ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ስለሚሆኑ ቀዳሚ የጥንቃቄ ዕርምጃ ከወዲሁ መወሰድ እንዳለበት መክሯል።
በተጨማሪም በድጋፍም ይሁን በተቃውሞ፣ ታቅደውም ይሁን በድንገት የሚካሄዱ ሠልፎችና ስብሰባዎች ለቫይረሱ ሥርጭት መስፋፋት ምክንያት ከመሆናቸው በፊት የመፍትሔ መንገዶቹ ከወዲሁ እንዲታሰብ አሳስቧል።
የይቅርታና የአመክሮ መስፈርት የሚያሟሉ የሕግ ታራሚዎች ቢለቀቁ፣ በማረሚያ ቤቶች የሚስተዋለውን የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመቀነስ እንደሚረዳም በምክረ ሐሳቡ ጠቁሟል።(ሪፖርተር – ዮሐንስ አንበርብር)