Connect with us

የአቶ ሽመልስ አብዲሳ “የአፍ ወለምታ” በግምገማ ብቻ ይጠራ ይሆን?

Photo: Social media

ትንታኔ

የአቶ ሽመልስ አብዲሳ “የአፍ ወለምታ” በግምገማ ብቻ ይጠራ ይሆን?

የአቶ ሽመልስ አብዲሳ “የአፍ ወለምታ” በግምገማ ብቻ ይጠራ ይሆን? | (ጫሊ በላይነህ)

የኦሮሚያ ክልል ኘረዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከወራት በፊት ተናግረውታል የተባለ ንግግር ሾልኮ መውጣት ራሱ የብልፅግና ፓርቲን ምሰሶ እየነቀነቀ ይገኛል። በተለይ ኦሮ- ማራ በሚል በአንድ ወቅት ውሀ በወንፊት እንቅዳ ሲሉ የነበሩት የኦሮሞ እና የአማራ ፓለቲከኞች መካከል ያለውን አንድነትና መተማመን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑ፣ እንደገና ንግግሩም የአቶ ሽመልስ አቋም ብቻ ነው ወይንስ የኦሮሞ ብልፅግና ፓለቲከኞች የሚጋሩት ነው የሚለው ነገሩን ከአፍ ወለምታ በላይ ከፍ ብሎ እንዲታይ አድርጎት ሰንብቷል።

ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ትላንት በባህርዳር የብልፅግና ፓርቲ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግሩ ስህተት መሆኑንና አቶ ሽመልስም ሊገመገሙ እንደሚገባ መናገራቸው ተሰምቷል።

አቶ ሽመልስ በዚሁ አወዛጋቢ ንግግራቸው በኦሮማራ ግንኙነት ጅማሮ ወቅት የሚያምነውን በማሳመን ቀሪውን ግራ በማጋባት መሰራቱን፣ የአማርኛ ቋንቋ በማዳከም ኦሮምኛ የማሳደግ ጥረት መከናወኑን፣ በአዲስአበበባ በህጋዊና ህገወጥ መንገድ ሰዎችን የማስፈር፣ ነዋሪው ከወር ገቢው ላይ በመቀነስ ቆጥቦ የሰራውን ቤት ለእኔ ለሚሉት ወገን የማደል ህገወጥ እንቅስቃሴዎችና ፓለቲካን ከተራ ቁማር ጋር ያመሳሰሉበት አውድ ብልፅግናን እንደፓርቲ የቆመበትን መሰረት የሚያናጋ፣ የህዝቦችን አብሮነት የሚያላላ፣ ለጠላትም ምቹ መደላድልን የሚፈጥር ሆኗል።

ብዙዎች አቶ ሽመልስ ከዚሁ ንግግራቸው ጋር በተያያዘ ብቻ በቅርቡ ከስልጣናቸው ሊነሱ እንደሚችሉ በማህበራዊ ድረገፃች እየፃፉ ነው። በግሌ ግን ይህ ቢሆን እንኳን የአቶ ሽመልስ መባረር ብቻውን መፍትሄ ይሆናል ብዬ አላስብም። አቶ ሽመልስ ካሏቸው ነገሮች በተለይ ዲሞግራፊ የማስተካከሉ ነገር ቀደም ሲል በአቶ ለማ መገርሳ ሲቀነቀን እንደነበርና መሬት ላይ የማውረድ እንቅስቃሴዎች በስፋት እንደታዩ ህዝብም ጠንቅቆ የሚያውቀው ነው።

እናም ብልፅግና እንደፓርቲ በተለይ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ አንደበት የተነገሩ ነገሮች አቋሙ ስለመሆኑ ወይንም አለመሆኑ ለህዝቡ በግልፅ መናገር አለበት። ኦሮምያ ክልል በአዲስአበባ ላይ ያለው ጥቅም በሚመለከት ህገመንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት በግልፅ፣ በሚታወቅ ህግና ስርአት የሚፈፀም እንጂ በመንግስት በሚደገፍ የመሬት ወረራ ሊሆን አይችልም። እናም ብልፅግና ውስጡን ባላጠራበት ሁኔታ አቶ ሽመልስ አምልጦት በተናገረው ብቻ እሱን መሰዋእት አድርጎ ነገሩን ማለባበስ የሚቻል አይሆንም።

እናም ብልፅግና ከምንም በላይ ውስጣዊ አንድነቱን ለመጠበቅ፣ ህዝባዊ ድጋፉንም በተጠናከረ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ ከፈለገ በየጊዜው “ኢትዮጵያ አትፈርስም” የሚል ዲስኩር ማሰማት ብቻውን በቂ አይሆንም። እንደአቶ ሽመልስ ያሉ መርዘኛ ንግግሮች በሚገባ አገርን ያፈርሳሉ። በፓለቲከኞች መካከል አለመተማመንን በማንገስ ሰላምን ያርቃሉ። በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየ አብሮነትን ይሸረሽራሉ። በፓለቲከኞች መካከል የማይጠፉ ትናንሽ ውስጣዊ ቅራኔዎችን ያጦዛሉ።

ያው ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ እንዲሉ…የብልፅግና ፓርቲ እንደሽመልስ ያሉ አክራሪ ፅንፈኞች የፀዳ እና ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅም በእኩል ደረጃ መቆም የሚችል አቅም ያለው ፓርቲ መሆኑን ለማሳየት ከንግግር በላይ የሚታይ፣ የሚዳሰስ ስራ ይጠበቅበታል እላለሁ።

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top