Connect with us

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የሽመልስ አብዲሳን ንግግር የተሳሳተ ነው አለ

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የሽመልስ አብዲሳን ንግግር የተሳሳተ ነው አለ
Photo: Social Media

ፓለቲካ

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የሽመልስ አብዲሳን ንግግር የተሳሳተ ነው አለ

~ በኦሮምያ ክልል በቅርቡ የተካሄደው ጥቃት ብሄርና ሃይማኖት መሰረት ያደረገ መሆኑን አስታወቀ

የአማራን ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ለማጋጨትና ለመነጠል የሚደረገውን ጥረት ከሕዝቡ ጋር በመሆን ለማክሸፍ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።

ፓርቲው ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ውይይት በማስመልከት ዛሬ ማምሻውን መግለጫ ሰጥቷል።

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት ፓርቲው ያለፈውን የሁለት ዓመት ተኩል የለውጥ ጉዞና ፈተናዎችን በዝርዝር ገምግሟል። በክልሉና በሐገሪቱ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተከናወነው ተግባር፣ ወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት፣ የብልጽግና ፓርቲ ድርጅታዊና ፖለቲካዊ ስራዎች፣ የክረምት የግብርና ሥራዎች፣ ባለፈው ሰኔ 22 ቀን በአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በብሔርና ሐይማኖት ላይ ያነጣጠረውን ጥቃትና ማፈናቀልን በጥልቀት በመገምገም የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ መቀመጡን አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።

ክልሉን ከግጭት ስጋት ለማስወጣት በሕዝብና በመንግስት የተከናወነው ተግባር አበረታች እንደሆነና አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን አንስተዋል።

ከአርቲስት ሐጫሉ ግድያ ማግስት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው አመጽና በብሔርና በሐይማኖት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ብዙዎችን ለህልፈት ዳርጓል፤ ንብረት አውድሟል፤ በርካቶችን አፈናቅሏል ያሉት አቶ አገኘሁ ድርጊቱ የሚወገዝ እንደሆነ በመድረኩ ተገምግሟል ብለዋል። ለእኩይ ተግባሩም ትህነግና ኦነግ ሸኔ በመናበብ ድጋፍ እንዳደረጉ መገምገሙን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ህገ ወጥ ድርጊቱ ያስከተለው ጉዳት እንዳይባባስ ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን ያደረገው ጥረት እውቅና እንደተሰጠው በመግለጽም በቀጣይም አጥፊዎች ወደ ህግ እንዲቀርቡና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድባቸው በቁርጠኝነት መስራት እንዳለብን ተግባብተናል ነው ያሉት በመግለጫቸው።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስለ ብልጽግና ፓርቲ የተናገሩትና ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ሐሳብ የተሳሳተና የፓርቲውን አቋም የማይገልጽ የግለሰብ አቋም ስለመሆኑ በመድረኩ መገምገሙንም አስታውቀዋል። ያነሱት ሐሳብም የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጥልቀት ተገምግሞ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት አቶ አገኘሁ በመግለጫቸው።

የአማራን ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ለማጋጨትና ለመነጠል የሚሰሩ ትህነግና ኦነግ ሸኔን የመሳሰሉ ኃይሎችን ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመተባበር መታገል እንደሚገባም ተግባብተናል ብለዋል። የክልሉ አመራር ያዳበረውን ውስጣዊ አንድነት በማጠናከር በሀገሪቱ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረትም በመሪነት እንዲንቀሳቀስ መግባባት ላይ መደረሱንም በመግለጫቸው አረጋግጠዋል።(አብመድ)

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top