Connect with us

ኦሞ ጎሽ መንጋው ፊት፤ ዱሩ ከከተማው አብሮ መኖር ያውቃል

ኦሞ ጎሽ መንጋው ፊት፤ ዱሩ ከከተማው አብሮ መኖር ያውቃል

መዝናኛ

ኦሞ ጎሽ መንጋው ፊት፤ ዱሩ ከከተማው አብሮ መኖር ያውቃል

ኦሞ ጎሽ መንጋው ፊት፤ ዱሩ ከከተማው አብሮ መኖር ያውቃል፡፡

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ተጉዟል፡፡ በኦሞ ቆይታው ከብዙ ችግሮች በኋላም በኢትዮጵያ የገናናነት ክብሩን ያለቀቀው ባለጸጋውን የተፈጥሮ መስህብ ያስጎበኘናል፡፡ ከጎሽ መንጋው ፊት ቆሜያለሁ ሲል ዱሩ ከከተማው እንዴት አብሮ መኖር እንደሚያውቅበት ይተርክልናል፡፡
ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ

ይኽ ኦሞ ነው፡፡ ዓይኔን ማመን አቅቶታል፡፡ ሀገሬ እንዲህ ያለ የዱር ጸጋ እንዳላት አስቤ አላውቅም፡፡ ተቀበረ ያሉት ኦሞ እንደ አልአዛር ከሞት ተነስቷል፡፡ የኦሞ ሜዳዎች የዱር እንስሳቱ መጋለቢያ ሆነዋል፡፡ ኦሞ ከስኳሩ ገዝፎ ጣዕሙ ተሰማኝ፡፡

መንገዱ ሁሉ ተአምር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ሀብት ላይ ያልተፈጸመ ወንጀልና በደል የለም፡፡ ነበረን ያልነው ብዙ ነበር፤ ተስፋ የቆረጥነው በራሳችን መጥረቢያ ነው፡፡ በራሳችን ጥይት ነው፡፡ በራሳችን የተፈጥሮ ጥበቃ ባህል ነው፡፡ መጤው ባህላችን አካባቢን ተጣልቶ ወደ ሰው በተሻገረበት ዘመን ኦሞ ድንቅ ነገር አየሁ፡፡

የሳላውን መንጋ ሳልፈው የቆርኪው ይከተላል፡፡ እሱን ሳልፍ ሌላው፡፡ ኦሞ በኢትዮጵያ ብዙው ክፍሉ ለልማት በሚል ለአገዳ የታረሰ ፓርክ ነበር፡፡ ያም ሆኖ የተፈረው ምድሩ ዛሬም በኢትዮጵያ ሰፊው ብሔራዊ ፓርክ ከመባል አላገደውም፡፡ የጎሽ መንጋ እያየሁ ነው፡፡ በመንጋው የሚርመሰመሰው ጎሽ ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ ሺህዎች ምናልባት ጥሩ አድርገው ይገልጹታል፡፡

ሜዳው ላይ እንስሳው ተሰባጥሯል፡፡ ጎሹ አናት ሳቢሳዋ ዓለሟን ትቀጫለች፡፡ በእንስሳት አለም እኔ አጥቢ አንተ ወፍ ብሎ ጎራ የለም፤ የተፈጥሮን ህግ ለማሸነፍ አብሮ መኖር ግድ ነው፡፡ ከኦሞ ሜዳዎች በሚሰፉ ከተሞቻችን ስልጣኔ ገባን ብለን እንደ ኦሞ ዱር እንስሳት አብረን መኖር አልቻልንም፡፡ አንዳችን ሌላችን እናጠፋለን፡፡ እዚህ የቱም እንስሳ የራሱን ጎራ አያጠፋም፡፡ ከጎራው ከሚርቀው እንኳን ሳይጠፋፋ ይኖራል፡፡

ኦሞ የውድንቢ ምድር ነው፡፡ ውድንቢዎች ከቆርኪ ጋር ሳይ ሜዳ ላይ ይቦርቃሉ፡፡ እነሱ በሁለት ስም የሚጠሩ የተለያዩ እንስሳት ቢሆኑም አንድ ሜዳ ለመዋል አንዳች እንቅፋት የለባቸውም፡፡ እኛ በአንድ ስም የምንጠራ ሰዎች አንድ ከተማ አብሮ መኖር አቅቶን አዳኝና ታዳኝ ሆነናል፡፡

ኦሞ ባለ ጸጋ ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡ ቀና ስትሉ የሚፈራው አንበሳ የዕለት ጉርሱን ሲያሯሩጥ ትመለከታላችሁ፡፡ ዝሆኖ ባተራመሰው ጎዳና ትጓዛላችሁ፡፡ በድክ ድክ ትዳር ውበት ትቀናላችሁ፡፡ በነብሩ ግርማ ትደመማላችሁ፡፡ ያለ ማጋነን ኦሞን ለረገጠ ሁሉ የሚሰጥ እድል ነው፡፡

ግማሽ ክፍለ ዘመን የኖረው ኦሞ ሰባ የሚደርስ አጥቢ እንስሳት ምድር ነው፡፡ 306 የወፍ ዝርያ ይታይበታል፡፡ የመስኖ ካናሉ ዛሬ የዳክዬ መዝናኛ ሆኗል፡፡ ጥቂት ቀሩ የሚባሉት ቀጭኔዎች አሉ ከተባለ የሚኖሩት ኦሞና ገራሌ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ 900 ኪሎ ሜትር ተጉዤ መጥቻለሁ፡፡ ወደ ኦሞ ወንዝ አብረን እንወርዳለን፡፡ ሙይን እንደ ጤግረስ እንሰለጥንባታለን፡፡ አብረን ነን፡፡

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top