አሀዳዊነት እንደ ወንጀል ሊታይ የሚገባው የመንግስት ስርአት ነውን?
(ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ)
ያለፉት ሁለት አመታት ብዙ ነገር እንድናይና እንድንሰማ እያደረጉን መሆኑ በግልጽ የሚታይ እውት ነው፣ ከእነዚህ ሁነታዎች መካከል አንደኛው በትህነግና ተባባሪዎቹ አማካኝነት አሀዳዊነት እንደ ወንጀል ፌዴራላዊነት ደግሞ እንደ እንከን የለሽ ስርአት ተደርገው ሲቀነቀኑ መስማታችን ነው፡፡ ትህነግና አጫፋሪዎቹ ያልወደዱትን ነገር በስድብነት በመጠቀም ጭምር በእጅጉ እንዲጠላ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡
በዚህም ምክንያት የለውጡን አመራር አሀዳዊ ነው ብለው በመወንጀል ወደ ድሮው ስርአት ሊመልሰን ነውና ብሔር-ብሔረሰቦች ተባብራችሁ አስወግዱት እስከማለት ይደርሳሉ፣ ዶ/ር አብይ ኦሮሞ መሆናቸውን በይፋ ባይክዱም በአህዳዊ የአማራ ልሂቃን ስለሚመሩ የፌዴራል ስርአቱን አፍርሰው አህዳዊ ሊያደርጉት ነው በማለት ነጋ ጠባ ያላዝናሉ፡፡ እኔ ባለኝ መረጃ መሰረት ገዥው ፓርቲም ሆነ ሀገራዊ ቅርጽ ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች አህዳዊ የመንግስት ስርአትን እስካሁን በአማራጭነት ያቀረቡት አለመሆናቸው ነው፡፡
ይህም ሆኖ አሀዳዊ የመንግስት ስርአት በአማራጭነት ቢቀርብ ምንድነው ችግሩ የሚል ጥያቄ በማንሳት ሀሳባቸውን በማስረጃዎችና በምሳሌዎች አስደግፎ መሞገት ይቻላል፣ ይኸ ስርአት በየትስ በኩል ነው አንድን አካል ለመወንጀያነት የሚያገለግለው? በአለማችን ከሚገኙት 194 የተባበሩት መንግስታት አባል አገሮች ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ መንገድ የፌዴራል ስርአትን የሚከተሉት 28 አገራት ብቻ ናቸው፡፡
ይህም ማለት 166 እውቅና ያላቸው አገራት አሀዳዊ የሆነውን የመንግስት ስርአት የሚከተሉ መሆኑና አሁን ላይ የፌዴራል ስርአትን ተግባራዊ ያደረጉ አገራትም ጭምር አሀዳዊ የመንግስት ስርአትን ይከተሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የፌዴራል ስርአት ከሚከተሉትም በተሻለ ዴሞክራሲን በተሟላ አኳኋን የሚተገብሩት ታላቋ ብሪታኒያ፣ ጣሊያን፣ ጃፓንና ፈረንሳይ በግንባር ቀደምነት ይገኙበታል፡፡
ከአፍሪካ ደግሞ እስካሁን ድረስ ከ55 የአፍሪካ አገራት ውስጥ ከነችግሩም ቢሆን የፌዴራል ስርአትን የሚከተሉት ሶስት አገራት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ናይጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እነዚህ የአፍሪካ አገሮች ዴሞክራሲን በተሟላ መልኩ ስራ ላይ በማዋል የሚታወቁ አይደሉም፣ ከእነዚህ ይልቅ አሀዳዊ የመንግስት ስርአት የሚከተሉት ጋና እና ቦትስዋና ዴሞክራሲያዊ ስርአት በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡
እናም አሀዳዊ የሆነው የመንግስት ስርአት ሲነሳ ሁል ጊዜ የእኛውን የደርግ ስርአትንና የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንጉሳዊ አገዛዝን ብቻ በምሳነት በማቅረብ አህዳዊ ስርአትን ጭራቅ አስመስሎ ለማሳየት የሚደረገው ጥረት እውነታውን ያላገናዘበ፣ በጥላቻ ላይ የተመሰረተና የደካሞች አስተሳሰብ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
በእርግጥም ጤናማ አዕምሮ ያለውና ነገሮችን በተገቢው ሁኔታ የሚያመዛዝን ሰው ይህንን መሰረተቢስ ውንጀላና ክስ ተቀብሎ እንደገደል ማሚቶ ያስተጋባል የሚል እምነት መያዝ ቂልነት ይመስለኛል፡፡ የዚህ አይነቱ አቀራረብ በተለይም የአማራ ምሁራንን እና ፖለቲከኞችን በማጥላላት ለማሸማቀቅና በፖለቲካው መድረክ ላይ ጉልህ ሚና እንዳይጫወቱ ለማድረግ ሲባል ስራ ላይ የዋለ ፍረጃ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
በዛ ላይ መሬት ላይ የሌለን ነገር በማንሳት የዋህ የሆነውን ህዝብ እና በጥላቻ የሰከሩ አክራሪ ፖለቲከኞችን እንዲሁም የእነዚህ አካላት ደጋፊ የሆኑ የማህበረሰብ አንቂዎችንና ወጣቶችን በማነሳሳት የአማራ ህዝብና ልሂቃንን ለማጥቃት መሞከር በእሳት የመጫወት ያህል ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ግን መታወቅ አለበት፡፡