Connect with us

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን፡- ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ጥቁር ሕዝብ መብት ጠበቃ!

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ለአፍሪካ አሜሪካውያን መብት ጠበቃ

ባህልና ታሪክ

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን፡- ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ጥቁር ሕዝብ መብት ጠበቃ!

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን፡- ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ጥቁር ሕዝብ መብት ጠበቃ!
ከተረፈ ወርቁ  በድሬቲዩብ

እንደ መንደርደሪያ
ባሳለፍነው ሳምንት አንድ ነጭ ፖሊስ አንድ አፍሪካ አሜሪካዊ ጎልማሳን በጠራራ ጸሐይ አስፋልት ላይ አጋድሞ በጉልበቱና በክርኑ ተጭኖ ለሞት እንዲያበቃ ያደረገበት፣ በዓለም ዙሪያ የተሰራጨው ኢ-ሰብአዊና አሰቃቂ የሆነ ቪዲዮ በአሜሪካና በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ አፍሪካ አሜሪካውያን ‘‘Black Life Matters’’ በሚል በቀድሞ ዘመን የትግል መርሕአቸው ኃይል የተቀላለቀበት የበቀል ርምጃ እየወሰዱ እንዳሉ በመገናኛ ብዙኃን በስፋት እየዘገቡ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት አርብ ምሽት በቲውተር ገጻቸውና በኤቢሲ ቴሌቪዥን፤ ‘‘when the looting starts the shooting starts’’ የሚል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ቲዊትር ይህን የትራምፕ መልእክት ግጭትን የሚባብስ፣ ከቲዊተር የማኅበራዊ ትስስር ሕግ የወጣ ጠብ አጫሪ መልእክት ነው በማለት እንዲታደግ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ለአፍሪካ አሜሪካውያን መብት ጠበቃ
ይህ ሰሞኑን በአፍሪካ አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ አሟሟት በአፍሪካ አሜሪካውያን ሕዝብ መካከል ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን አንድ ታሪክ እንዳስታውስ አሰገደድኝ፡፡ በዚህ በሰሞኑ ክሥተት መነሻነት በአፍሪካ አሜሪካውያን/በጥቁር ሕዝቦች መብት ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያንና ኢትዮጵውያን ለአፍሪካ አሜሪካውያን ጥቁር ሕዝብ የመብት ትግል ያደረጉትን አስተዋጽኦ ከታሪክ ማስታወሻ በጥቂቱ ለመቃኘት ወደድኹ፡፡

ከዛሬ ሁለት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት ኢትዮጵውያን ተጓዦችና የመርከብ ላይ ነጋዴዎች ወደ አሜሪካ አምርተው ነበር፡፡ እነዚሁ ኢትዮጵውያን ከሥራቸው ቆይታ ባሻገር በሰንበት ለአምልኮተ እግዚአብሔር ወደ ቤተክርስትያን አምርተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዛን ጊዜዋ አሜሪካ ጥቁሮች ከነጮች እኩል አብረው ተቀምጠው አምልኮ እንዲፈጽሙ አይፈቀድም ነበር፡፡ በዚህ በዚህ ዘረኛ አስተሳሰብ ግራ የተጋቡትና በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ያልተገባና ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ ፈጽሞ ያፈነገጠ የቆዳ ቀለም ልዩነት መደረጉ ያሳዘናቸው ኢትዮጵያውያን ከአፍሪካ አሜሪካውያኑ በመመካከር፣ በኒዮርክ ሐርለም ባብቲስት አቢሲኒያ በሚል ስያሜ የራሳቸውን ቤተክርስትያን እ.አ.አ. በ1809 አቋቋሙ፡፡

ይህ በኒው ዮርክ ከተማ፣ ሐርለም የሚገኘው የባፕቲስት አቢሲኒያ ቤተክርስትያን አመሠራረት ታሪክ ከኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ አኩሪ የነጻነት ተጋድሎ ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት አለው፡፡ በተጨማሪም የሀገራችን የኢትዮጵያ ስም በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ተደጋግሞ መጠቀሱና ክርስትናን ቀድማ የተቀበለች ሀገር በመሆኗ- በብዙ አፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን ዘንድ፣ ‘‘ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ አፍሪካዊ እናት ቤተክርስትያን’’ የሚል ስያሜ እንድታገኝ አድርጓታል፡፡

ይህ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን በዓለም አቀፍ መድረክ ሺህ ዘመናት ታሪክና ገናና ሥልጣኔ ባለቤት፣ በነፃነቷ ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገር መሆኗ እውነታ- በባርነት ቀምበር ተይዘውና በቅኝ ግዛት ሥር ወድቀው ሲማቅቁ ለነበሩ አፍሪካውያን፣ አፍሪካ አሜሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች- ለነፃነታቸው እንዲታገሉ፣ በአንድነት ሆ ብለው እንዲነሡ ትልቅ ወኔና እና መነሳሳት ፈጥሮላቸው ነበር፡፡

ለአብነትም ያህል የጥቁሮች መብት ተጋይ የነበረው ማርከስ ጋርቬይ the Universal African Anthem በሚለው የአፍሪካ ብሔራዊ መዝሙሩ ግጥም ውስጥ- ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች ነጻነት እኩልነትና መብት ተስፋ አብሳሪ ሀገር መሆኗን መስክሯል፡፡ ከአፍሪካ ብሔራዊ መዝሙር ስንኞች ውስጥ በጥቂቱ ልንቀጭብ፡

ኦ! ኢትዮጵያ!
ኦ! ኢትዮጵያ!
የአማልዕክት ምርጫ ሰገነት
የዝናቡ ደመና ሲሰበሰብ በማታ
ሰራዊታችን በአሸናፊነት ሲገባ በዕልልታ
ኦ! ኢትዮጵያ… ተዋጊው ጦሩን እየሰበቀ ሲመጣ

በቀይ ጥቁር አረንጓዴ ባንዴራ ሲመራ
አውቀነዋል ድል የእኛ መሆኑን
የጠላት ኃይል
ብትንትኑ መውጣቱን
ኦ! ኢትዮጵያ…

ኢትዮጵያን ኢትዮጵዊነት በአፍሪካ፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ የነጻነት ትእምርት/ ፣ የአይበገሬነትና የእምቢ ለነጻነቴ ትግል ወኔና ስንቅ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በኢትዮጵ የረጅም ዘመን ታሪክ፣ ሥልጣኔና አኩሪ የነጻነት ተጋድሎ ውስጥ ጉልህ ስፍረና አሻራ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን- በአፍሪካውያን፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ከፍ ያለ ተቀባይት እንዲኖራት አድርጓል፡፡

ከዚህ የቤተክርስትያኒቱ የነጻት ታሪክ የተነሣም- በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ በካረቢያንና በጃሜይካ በኢትዮጵያ ስም የተቋቋሙ በርካታ ቤተ እምነቶች አሉ፡፡ አምላካችሁ አምላካችን፣ ሃይማኖታችሁ ሃይማኖታችን፣ ታሪካችሁ ታሪካችን፣ አኩሪ የነጻነት ተጋድሎአችሁ ኩራታችን፣ ተስፋችን ነው ያሉ በርካታ አፍሪካ አሜሪካውያን በሩቅ ሆነው የኢትዮጵያ ቤትክርስትያን ይናፍቁ ነበር፡፡ እንደ እነ ቦብ ማርሌይ፣ ፒተር ቶሽ ያሉ ኢትዮጵያን ለማየት ዕድሉን ያገኙ ደግሞ በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ተጠምቀው አባል ለመሆን በቅተዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ቤተ-እምነቶቻቸውን በኢትዮጵያ ስም በመሰየም፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ያላቸውን ክብርና ናፍቆት በተግባር አሳይተዋል፡፡ በኒው ዮርክ ሐርለም የሚገኘው የአቢሲኒያ ባብቲስት ቤተክርስትያንም የዚህ የአፍሪካውን ኢትዮጵያ ናፍቆት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

ይህ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ሐርለም የሚገኘው የአቢሲኒያ ባብቲስት ቤተክርስትያን ለአፍሪካ አሜሪካውያን የነጻነት ትግል ምልክት ሆኖ አገልግሏል፡፡ የጋና የነጻነት አባት የሆነው ፓን አፍሪካኒስቱ ክዋሜ ንኩርማ የፒ.ኤች.ዲ. ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በዚህ ቤተክርስትያን ተገኝተው ለአፍሪካ አሜሪካውያን ታሪካዊ የሆነ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ዶ/ር ንኩርማ በዚሁ ንግግራቸው፤ ‘‘… የአውሮፓውያን ወራሪዎችና ቅኝ ገዢዎች ክንድ ያልጎበኛት፣ ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት የሆነችው አፍሪካዊ እናት የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን፣ ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነትና መብት ትግል- ተስፋና ብርሃን የሆነች ተቋም ናት፡፡’’ በማለት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ታሪካዊ ምስክርነታቸው ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ንኩርማ በአፍሪካ ሀገራት ስብሰባው ሁልጊዜም፤ ‘‘Ethiopia stretch out her hands unto God, Africa must unite!’’ በሚለው የመዝጊያ ንግግሩ ይታወቃል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ግቢ ውስጥ ለጋናዊው ፓን አፍሪካኒስት ለዶ/ር ክዋሜ ንኩርማ በቆመው ሐውልት ስርም ይኸው ንግግሩ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ለጋናዊው ፓን አፍሪካኒስት ዶ/ር ንኩርማና ለበርካታ አፍሪካ አሜሪካውያን መብት ትግል ቋሚ ቅርስ ወደሆነው ወደ አቢሲኒያ ባብቲስት ቤተክርስትያን የመቋጫ ሐሳቤ ጽሑፌን ላሳርግ፡፡ ሦስት ዓመት በፊት በአሜሪካ ኒው ዮርክ ለአፍሪካ አሜሪካውያን ታሪክና ባህል እንዲሆን የተገነባው ቤተ-መዘክር/ሙዚየም- ፕ/ት ባራክ ኦባማና ቀዳሚ እመቤት ሚሼል ኦባማ እና በርካታ እንግዶች በተገኙበት የባብቲስት አቢሲኒያ ቤተክርስትያን መሪ የሆኑት ሬቨረንድ ካልቪን ባትስ ታሪካዊ የሆነ ንግግር አድርገው ነበር፡፡

ሬቨረንድ ባትስ በዚህ ታሪካዊ ንግግራቸው ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ለአፍሪካ አሜሪካውያን ጥቁር ሕዝቦችና ለአሜሪካ አንድነት ያደረጉትን ተጋድሎና ውለታ በክብር ዘክረውታል፡፡ ለበለጠ መረጃ ከዚህ ጽሑፍ በታች ያለውን ቪዲዮ እና ታሪካዊ የሆኑ ምስሎችን ታይዋቸው ዘንድ አደራ እላለኹ፡፡

ጽሑፌን የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት የነበሩት ታቦ እምቤኪ በ፪ሺሕ ፪ ዓ.ም. አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የክብር ዶክትሬት በሰጣቸው ጊዜ ባደረጉት ንግግራቸው፤ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ትእምርት፣ የአፍሪቃ ጥቁር ሕዝቦች የረጅም ጊዜ ታሪክና ሥልጣኔ፣ ቅርስና ባህል ማእክል እንደሆነች፤›› በገለጹበት ንግግራቸው ልሰናበት፡፡

Ethiopia shall soon stretch her hands unto God. … In this context Africans were convinced that when Ethiopia stretched out her hands unto God, as foretold in the Bible, she imbued the Christian Church with an African ethic and ethos. Thus we would the authentic African Church serves as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity.

ሰላም!

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top