በሶስት ወራት ውስጥ ብቻ 15 ሚሊዮን የቤት ውስጥ ጥቃቶች ተፈጽመዋል
በዘመነ ኮሮና በሴቶች ላይ ይፈጸሙ የነበሩ የቤት ውስጥ ጥቃቶችን ተባብሰዋል። ባለፉት ሶስት ወራት 15 ሚሊዮን የቤት ውስጥ ጥቃቶች ተመዝግበዋል ።
ይህ የሆነው ደግሞ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዞ ወረርሽኙን ለመከላከል በተጣሉት ገደቦች ምክንያት ነው። በዚህም ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 15 ሚሊዮን የቤት ውስጥ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ለአለም የማህበረሰብ ጤና ትልቅ እንቅፋት እየሆነም ነው።
ወረርሽኙ በሴቶች ላይ አሰቃቂ ተፅእኖ ይኖረዋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል። በዚህም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሰዎች በቤታቸው እንዲቀመጡ ሲደረግ በተለይም ሴቶች በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ በመደረጋቸው ብቻ 20 በመቶዎቹ ለቤቱ ውስጥ ጥቃት ተጋልጠዋል።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለመከላከል ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት፣ በወረርሽኙ ምክንያት በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና በከፍተኛ ሁኔታም እየተባባሰ ነው።
ከኮሮና ቫይረስ ቀውስ ለማገገም የሥርዓተ- ጾታ ስርዓትን ማሻሻልና ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ብዙዎች ይስማማሉ።እንደዚህ ዓይነት ማህበራዊ ከስተቶችን ስንመለከት በመጀመሪያ የችግሩ ተጎጂዎች ሴቶች በመሆናቸው ትኩረት አድርጎ መስራት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ይጠበቃል።
በተለይም ከድህነት፣ ከዘር ወይም ከአካል ጉዳተኝነት ጋር በተዛመዱ ለበርካታ መድልዎ ዓይነቶች የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመር ሲሆን በሴቶች ላይ የሚፈጸሙት ጥቃቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይወስዳሉ። የቅርብ ጊዜያት መረጃዎች እንደሚያሳዩት 30 በመቶ የሚሆኑት በሆነ ወቅት ላይ ከአጋሮቻቸው አካላዊና ወይም ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ግን ከዚህ የተለየ ነው። በዚህ ልዩ ባህርይ አሁን ያለው የጤና ቀውስና ተጓዳኝ እርምጃዎች በተለይም ሴቶች በዓለም ዙሪያ በሚኖሩበት አኗኗር ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደሩ መገንዘብ አዳጋች አይሆንም።
ቀድሞውኑ በቤት ውስጥ ጥቃት ብዙ ሴቶች ችግር እየደረሰባቸው ቢሆንም ቫይረሱን ለመከላከል በቤታቸው እንዲቆዩ መደረጋቸው ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ አድርጓቸዋል። በዚህ ዘመን እራሳቸውን ችለው በሚኖሩ ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ የጥቃት ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው። በዓለም ዙሪያ ለሚከሰቱ የቤተሰብ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ የመጨመር እድሉ ከፍተኛ ሆኗል።
የተባበሩት መንግስታት በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን የቤት ውስጥ ጥቃት ለመቋቋም አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በትዊተር ገጻቸው ጠቅሰው፤ የዓለም መንግስታት ሁሉ ለሴቶች ደህንነት ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ጭምር አሳስበዋል።
በዚህ በተባባሰ ጭንቀትና ፍርሃት ወቅት የጥቃት ሰለባዎች ከፍተኛ አደጋ እየደረሳባቸው ነው። በተለይም ጠንካራ ማህበራዊና የህግ አገልግሎት በሌላቸው ሀገሮች ሁኔታው የከፋ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች መንግስትና ሌሎች ሲቪል ማህበረሰብ በጋራ ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
በተመሳሳይም በሴቶች ላይ የሚደርሱትን ማህበራዊ ጥቃትና ቀውስን አስመለክቶ የአለም የኢኮኖሚ ፎረም / World economic forum/ በድረ ገጹ እንዳስነበበው ከሆነ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ላይ ሊባባሱ ከሚችሉ ማህበራዊ ቀውሶች መካከል አንዱ ሴቶች በቤታቸው በማዋላቸው ብቻ ላልተፈለገ እርግዝና እየተጋለጡ ነው። ይህም የአለም ህዝቦች ስጋት የሆነውን የኮሮና ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት በላይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።
በቤተሰብ ዕቅድ ውስጥ ተደራሽነት አለመኖር፣ ከጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ መሰናክሎች መኖር ጋር በተያያዘ በመጪዎቹ ወራቶች ሰባት ሚሊዮን ያልታሰበ እርግዝና ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እያሰጠነቀቀ ይገኛል። ሴቶች በኮሮና ቫይረስ እንያዛለን በሚል ፍራቻ የህክምና ቀጠሮዎችን እየዘለሉ ሲሆን በተቋረጠ አቅርቦት ሰንሰለት ምክንያት የወሊድ መቆጣጠሪያዎችን ማግኘት የበለጠ ከባድ እየሆነም ነው።
የጤና አገልግሎቶች ተቋርጠው ለስድስት ወራት ያህል ከቆዩ በእነዚህ አገሮች ውስጥ 47 ሚሊዮን ያህል የሚሆኑት ሴቶች ዘመናዊ የወሊድ መከላከያዎችን ማግኘት እንደማይችሉ የተባበሩት መንግስታት የሕዝብ መረጃ ድጋፍ ትንታኔ ያሳያል። ተመራማሪዎቹ በበኩላቸው በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን እያገኙ አይደለም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2012