Connect with us

የጀዋር መሐመድ ምላሽ – ለጠ/ሚ ዐብይ መግለጫ

የጀዋር መሐመድ ምላሽ ~ ለጠ/ሚ ዐብይ መግለጫ
Photo: Social media

ፓለቲካ

የጀዋር መሐመድ ምላሽ – ለጠ/ሚ ዐብይ መግለጫ

የጀዋር መሐመድ ምላሽ ~ ለጠ/ሚ ዐብይ መግለጫ

እንወያይ እንደራደር ማለት ከመቼ ወዲህ ነው የጦርነት ግብዣ የሆነው?

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር አዳመጥኩት። በግሌም ሆነ እንደ ፓርቲ መባል ያለበትን ከዚህ በፊት ስለተናገርን አጭር አስተያየት ብቻ ልስጥ

1. ነገሮችን ከሚገባው በላይ ማጋጋል (escalate ማድረግ) ለማንም የሚጠቅም አይደለም። አሁን የተከተልነውን ህገመንግስታዊ ትርጉም የመጠየቅ መፍትሄ የመረጥነው የተለያዩ የድርሻ አካላትን ካሳተፍንና ካወያየን በኋላ ነው የሚለው እውነት እንዳልሆነ እራሳቸውም ያውቁታል። የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጀንዳ ሳይነገራቸው ተጠርተው በተሳተፉበት ስብሰባ መንግስት የራሱን አማራጮች አቀረበ እንጂ ሌሎች አማራጭ ሃሳቦችን ለመመልከት ፍቃደኛ አልነበረም፤ በተጨማሪም ስብሰባውን የጠራው አሁን ገሃድ ያደረገውን መፍትሔ የገዢው ፓርቲ ማዕከላዊ ከወሰነ በኋላና ይህን ውሳኔውን በይስሙላ ቅቡልነት እንዲኖረው ለማድረግ እንጂ በእውነት ትክክለኛ የተለያዩ ሃሳቦች ተንሸራሽረው የተሻለ የሚባለውን አማራጭ ለመከተል አልነበረም። ይህም የቀድሞውን የኢህአዴግ ”ወስኖ የማሳወቅ” (fait accompli) ባህል ያስቀጠለ ነው።

2) በኮቪድ-19 ምክንያት የምርጫን መተላለፍ የተቃወመ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ አመራር እስካሁን አልሰማሁም (በህወሃት በኩል ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች መኖራቸው እንደጠበቀ ሆኖ)።

3) ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብዛኛው ንግግራቸውን ያሳለፉት የሽግግር መንግሥትን ሀሳብ በመተቸት ነው። አከራካሪው ጉዳይ ሕገመንግሥቱ ስለምርጫ ማስተላለፍ እና ማራዘም ምንም ያለው ነገር ስለሌለ ምርጫው እንዴት መተላለፍ እንዳለበትና አዲስ ምርጫ ማካሄድ እስኪቻል መንግሥት እንዴት መተዳደር እንዳለበት ድርድር እና ውይይት ያስፈልጋል ነው። እንደ መፍትሔ አንዳንድ ድርጅቶች የሽግግር መንግሥት፣ ሌሎች የባላደራ መንግሥትን ሲጠቅሱ ሰምተናል። አብዛኞቹ ግን እስካሁን በዚህ ላይ አቋማቸውን አልገለፁም። ሁሉም ድርጅቶች በጋራ እየጠየቁ ያሉት የምክክር እና የድርድር መድረክ ይዘጋጅ ነው። እዛ መድረክ ላይ የየድርጅታቸውን ፕሮፖዛል አቅርበው አስማሚ የሆነው ይተገበራል።

4) በሕገመንግሥት ጉዳይ ላይ ምንም ምርምር ያላደረጉ ሰዎች ናቸው የገዢውን ፓርቲ የሕገመንግሥት መተርጎም አካሄድ የተቃወሙት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። አዎ አብዛኞቻችን የሕገመንግሥት ጥናት ባለሙያዎች አይደለንም። ነገር ግን ልክ እንደ ገዢው ፓርቲ የሕግ አማካሪዎች አሉን። የያዝነውም አቋም የባለሙያዎችን ምክር ሰምተን የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ እና የድርጅቶቻችንን ፖሊሲ አገናዝበን ነው። የውይይቱ ቀን አጀንዳ አስቀድሞ ቢነገረን ኖሮ እኛም እንደ ገዢው ፓርቲ የህግ አማካሪዎቻችንን ይዘን ለመምጣት ያስችለን ነበር። በነገራችን ላይ የሕግ ባለሙያዎች የተስማሙበትን ጉዳይ የፖለቲካ መሪዎች ለውይይት መቅረባቸው ስህተት ነው እንዳሉ ተደርጎ መቅረቡ ትክክል አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ ባለፉት ሳምንታት በእውቅ የሕግ ባለሙያዎች ሰፊ ክርክር በማኅበራዊ ሚዲያ እና በጋዜጦች ሲካሄድ ከርሟል አሁንም ቀጥሏል።

Addis Standard, Ethiopia-Insight, Addis Fortune, etc ማየት ይቻላል። ገዢው ፓርቲ ያቀረባቸው አራት አማራጮች ከመቅረባቸው በፊት ሰፊ ክርክር ሲካሄድባቸው ነበር። ሆኖም ግን በአንዱም ላይ ስምምነት አልተደረሰም። እኛም አስማሚ የሆነ አንቀጽ በሕገመንግሥቱ ስለሌለ የፖሊቲካ አመራሩ መግባባት አስፈላጊ ነው ያልነው ለዚህ ነው። አይደለም ግልጽ እና አስገዳጅ ለሆነም የህገመንግስት ቀውስ፤ የሀገራችንን ፖሊቲካ ሁኔታ ባጠቃላይ ከአዙሪት ለማውጥት ሀገራዊ ውይይት እና ድርድር ወደር የለሽ አማራጭ ነው።

5) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው ስልጣን ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንገድ መያዝ ፈጽሞ የተከለከለ ነው ብልዋል ። ትክክል ነው። በተመሳሳይ መልኩ ህገመንግስታዊ ባልሆነ አሰራር የስልጣን ጊዜን ማስረዘምም የተከለከለ ነው። ህገመንግስቱ ምርጫን ስለማስተላለፍ እና የስልጣን ዘመንን ማራዘም ምንም ያለው ነገር በሌለበት በገዢው ፓርቲ በተሞሉ ምክርቤቶች ‘ህገመንግስት አስተርጉሞ’ የስልጣን ዘመንን ማራዘም ኢህገመንግስታዊ ነው የምንለውም ለዚሁ ነው።

6) ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለው መንግስት ቅቡልነት ያለው ነው ሲሉ አንድ የዘነጉት ጉዳይ ያለ ይመስለኛል። ይሄውም ይህ ገዢ ፓርቲ ቅቡልነት ማጣት ብቻ ሳይሆን በህዝብ አመጽ ተሽነፎ፣ ቅቡልነት ማጣቱን አምኖ፤ ከእንግዲህ እለወጣለሁ ሀገርምን ወደዲሞክራሲ አሸጋግራለሁ ብሎ ቃል የገባ ነው። አሁን ያለው ፓርቲ ለ 27 አመታት ህዝብን ያሰቃየ አምባገናዊ ‘ አሸባሪ’ መንግስት እንደነበር እኮ በግልጽ በፓርላማ የነገሩን እኝሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ታዲያ ከዛ ወዲህ ምርጫ ተካሂዶ ነው አዲስ ቅቡልነት የተጎናጸፈው? አሁን ያሉን የፌደራል እና የክልል ምክርቤት አባላት እኮ የዛው ህዝቡ ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩም በማያሻማ መልኩ ቅቡልነት የነፈጉት ፓርቲ ተመራጮች ናቸው። ልድገመው ይህ ፓርቲ በተጭበረበረ ምርጫ በተመረጠ በወራት ውስጥ ህዝብ አምጾበት ለ4 አመታታ ከፍተኛ መስዋትነት ያስከፈለ ትግል ተሸንፎ፤ እጅ ሰጥቶ ከጊዜው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እስከ ምርጫው ድረስ በባለደራነት እንዲቀጥል የተፈቀደለት መንግስት ነው። ይህን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ሲሉት የነበረ ነው።

7) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨረሻ ላይ ስለ ወጣቶች ደም መፍሰስ እና መንግሥት አስፈላጊውን የኃይል እርምጃ እንደሚወስድ መግለፃቸው ምንም አይነት አግባብነት የሌለው እና አፍራሽ አባባል ነው። ለምንድነው የወጣቶች ደም መፍሰስ ጋ የሚኬዴው? ምንስ ሲሆን አሰቡት? የተጠየቀው ለተፈጠረው ቀውስ በውይይት እና ድርድር መፍትሔ እንፈልግ ነው። እንወያይ፣ እንደራደር ማለት ከመቼ ወዲህ ነው የጦርነት ግብዣ የሆነው? ይህ አካሄድ ትችትን እና ክርክሩን ለማስቆም የተደረገ ማስፈራሪያ ከሆነም ትክክል አይደለም። ሊታረም ይገባል። አይሰራምም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲሞክራሲ እሴቶችን ማጎልበት አስፈላጊ እንደሆነ በአጽዕኖት ተናግረዋል። እነዚያን እሴቶች ማዳበሪያው ዋናው መንገድ በዜጎች እና አመራር መካከል የሚደረግ ትችት፣ ክርክር እና ድርድር ነው። ትችት እና ክርክርን ለማስቆም የሚደረግ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እነዚያን የዲሞክራሲ እሴቶች ለማቀጨጭ እንጂ ለማጎልበት አይረዳም። ይህ ለውጥ ሺዎች ህይወታቸውን ገብረው ያስገኙት ወደ ተሻለ ነጻነት እና ዲሞክራሲ እንድንሸጋገር መሆኑን ሁሉም ለ አንዲት ሰኮንድ መረሳት የለበትም።

8) ፓርቲያቸው ሰፊ ቅቡልነት እንዳለው እና የሚቀጥለውን ምርጫ እንደሚያሸንፍ ጥርጥር የለውም ብለዋል። ከሆነ እሰየው ነው። እንደዚያ ዓይነት በራስ መተማመን ካለ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ማሰር፣ ማሳደድ፣ ማስፈራራት እና ማፈናቀልን ምን አመጣው? ነፃ እና ሰላማዊ በሆነ ምርጫ እንወዳደር፤ በዝረራ አሽንፉን እና ውጤቱን በፀጋ ተቀብለን እንደተቃዋሚ እንቀጥላለን። ምርጫው እስኪካሄድ ግን ምርጫውን በማስተላለፊያ እና የመንግሥትን የሥራ ዘመን ማራዘሚያ ጉዳይ ላይ አሁንም ተወያይተን መግባባት አለብን እንላለን።

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top