ክብር እና ፍቅር ለዚህ ነፃነት ላበቁን ጀግኖች፣ አባትና እናት አርበኞቻችን!!
በተረፈ ወርቁ*
1. እንደ መንደርደሪያ
ደቡብ አፍሪካዊው የነጻነት ታጋይ፣ የዕርቅና የሰላም ሰው፣ የዓለም ሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት፣ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ፤ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የሺሕ ዘመናት ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔ፣ ሕዝቦቿን ‘የእምቢ ለነጻነቴ’ የአይበገሬነት ጽኑ መንፈስንና በዓለም ሁሉ የተሰማው አኩሪ የነጻት ተጋድሎ ያሳደረባቸውን የአፍሪካዊነት ኩራት፣ ከፍ ሲልም ሰው የመሆናቸውን ታላቅ ክብርና የመንፈስ ልእልናቸውን- ኢትዮጵያና ኢትዮጵዊነት እንዴት ባለ ሁናቴ ከፍ እንዳደረገላቸው ‘‘Long Walk to Freedom’’ በሚለው የሕይወት ታሪካቸውን በጻፉበት ድንቅ መጽሐፋቸው ያጋሩትን ስሜታቸውን ባማስቀደም ጽሑፌን ልጀምር፡፡
ወጣቱ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በ1950ዎቹ ለወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ወደ ሀገራችን በመጣበት ወቅት ልዑላዊነቷና ነጻነቷ በዓለም ደረጃ ታፍራና ተከብራ ወደኖረችው ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ መምጣቱ ያሳደረበትን የመንፈስ ኩራት ሲገልጽ፤
ማንዴላ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሱዳን በብሪቲሽ አየር መንገድ ያደረገውን ጉዞ አጠናቆ የጉዞው ፍፃሜ ወደሆነችው ሀገር ኢትዮጵያ ለመጓዝ የሁላችን ኢትዮጵውያንና የአፍሪካ ኩራት ወደሆነው የኢትዮጵ አየር መንገድ አውሮፕላን ሲገባ ያየው ነገር አግራሞትን የቀላቀለ ስሜትን አጫረበት፡፡ ለወጣቱ የነፃነት ታጋይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ በጥቁር ኢትዮጵያውያን አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች የሚመራ መሆኑ እጅጉን ያሰገረመውና ያስደነቀው ነገር ነበር፡፡ እርሱና ወገኖቹ በዘረኛው አፓርታይድ ሥርዓት ቅኝ ግዛት ሥር ወድቀው በሚማቅቁባት በአገሩ ደቡብ አፍሪካ እንዲህ ዓይነቱ የአእምሮ ጥበብንና ትምህርት የሚጠይቅ ሥራ በነጮች እንጂ በጥቁሮች ሊሠራ እንደማይችል ለዓመታት የተሰበከው የዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት ስብከት ከንቱ መሆኑን ነበር ያረጋገጠለት፡፡
ማንዴላ በዚህ የነጻነታችን ክብርና ኩራት በሆነው በአየር መንገዳችን በቃል ሊገለጽ የማይችል ክብርና ኩራት ነበር የተሰማው፡፡ ማዲባ በዚህ የነጻት ዓርማችን ክፍ ብሎ በሚታየበት በኢትዮጵያ አየር መንገዳችን ለሦስት ሰዓታት ያደረገው በረራ ልዩ ስሜት፣ ናፍቆትና ትዝታ ነበር የጣለበት፡፡ ይህን የነጻት ክብር መንፈስ በደማቸውና በአጥንታቸው ከፍ ያደረጉ ኢትዮጵያውን የጀግኖች አርበኞቻችን አኩሪ ተጋድሎ በምናቡ ማመላለስ ጀመረ፡፡ የሚበርበት አውሮፕላን የሱዳንን የአየር ክልል አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሲገባም በመስኮቱ አሻግሮ የኢትዮጵያን ተራሮችና ሽንተረሮች በጥልቅ የነጻነት ስሜት ውስጥ ኾኖ በምናብ እንደወጋቸው በዚሁ መጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ይተርክልናል፡፡
እነዚህ ተራሮችና ሸለቆዎች፣ ሜዳና ሸንተረሮች ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች ወራሪውን የኢጣሊያን ሰራዊት ያንበረከኩበት፣ እነዚህ ተራሮች በኢትዮጵያን ጀግኖች አባቶቻችን ደምና አጥንት የተዋቡ … ዘመናትን ያስረጁ የነጻነት ተስፋ ጎሕ ያበሰሩ- ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በእነዚህ አድማስ ጥግን የነኩ በሚመስሉ ተራሮች ለአፍሪካውያን፣ ለጥቁር ሕዝቦችና ነጻነታቸውን ለሚያፈቅሩ ለሰው ልጆች ኹሉ የተበሰረ የነጻነት ሕያው ድምፅ ዛሬም ጎልቶ፣ ደምቆ የሚሰማበት ነው፣ በደምና በአጥንት መሥዋዕትነት የተዋቡ የነፃነት ተራሮች!!
የአፍሪካዊውን የነጻት አርበኛና ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵዊነት አኩሪ የነጻት ተጋድሎ የሰጡትን ምስክርነት ያስቀደምኩበት ምክንያት አለኝ፡፡ ይኸውም በነገው ዕለት ሚያዝያ 27 ቀን የድል/የዐርበኞች ቀንን እንዘክራለን፣ እናከብራለን፡፡ ስለሆነም የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶችና እናቶች ስለነጻነታችን ስለሉዓላዊነታችን የከፈሉትን መሥዋዕትነት በጥቂቱ ለመዘከር በማሰብ ነው፡፡
2. ኢትዮጵያዊነት ለሰው ልጆች ሁሉ የተበሰረ የነፃነት ውብ ዜማ
ተዋዳጇና ዕውቋ አርቲስት እጅጋየሁ ሺባባው/ጂጂ ‹‹ዐድዋ›› በሚለው እጅግ ተወዳጅ ዜማዋ፡-
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፣
ስንት ወገን ወደቀ በነጻት ምድር፣
ትናገር ዐድዋ ትናገር አገሬ …፡፡ ብላ እንደተቀኘችው፡፡
በእርግጥም መተኪያ የሌላትን፣ ክቡርና ውድ ሕይወታቸውን ሠውተው፣ ደማቸውን አፍሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ከቅኝ ገዢ ኃይሎች ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው፣ እናት አገሬ እኛ ልጆችሽ በሕይወት ቆም እያለን የአንቺ ክብር፣ የሕዝቦችሽስ ነጻነት እንዴት ይደፈራል ብለው በዱር በገደል፣ በየተራራውና በየሸንተረሩ በታላቅና አኩሪ ተጋድሎ የአገራችን ነጻነትና ልዑላዊነት ያስከበሩና ታሪክ ስማቸውን በወርቀ ቀለም የከተበላቸውን፣ እነዚህን የምንጊዜም ባለውለታዎቻችን የሆኑት ጀግኖቻችን ሕያው ታሪካቸውን ሁልጊዜም ልናከብረውና ለትውልድ ወደ ትውልድ በክብርና በኩራት ልናስተላልፈው የሚገባን ነው፡፡
ይህ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሀገራቸው ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና ክብር የከፈሉት መሥዋዕትነት ትሩፋት- ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ምድር አልፎ እስከ ሰሜን አሜሪካ፣ ጃሜይካና ካረቢያን፣ ከቻይና እስከ ኮሪያ ልሣነ ምድር ድረስ ብዙዎችን ‘እምቢ ለነፃነቴ’፣ ‘እምቢ ለሰውነት ክብሬ’ ብለው በቆራጥነትና በጀግንነት እንዲነሱ የወኔ ስንቅ የኾናቸው ታላቅና አኩሪ የነፃት ተጋድሎ ነው፡፡
ይህን የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ ሰው የመኾን ክብርና የመንፈስ ልእልንና ከፍ ያደረገውንና በሌላ በኩል ደግሞ አውሮፓውያንና ቅኝ ገዢ ኃይሎችን በሃፍረት እንዲሸማቀቁ ያደረገውን የዐድዋውን ድል ለመበቀል ፋሽስት ኢጣሊያ ዳግመኛ ሠራዊቷን ወደ ኢትዮጵያ አዘመተች፡፡ ከአርባ ዓመታት በኋላ በትልቅ ዝግጅት፣ ዘመናዊ መሳሪያና በዓለም መንግሥታት የተከለከለ የመርዝ ጭስ ቦምብ ታጥቀው የመጣው የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ለጊዜው ድል የቀናው ቢመስልም በጀግኖች አባትና እናት አርበኞቻችን አኩሪ የነፃት ተጋድሎ የተነሳ ከአምስት ዓመት በላይ በሀገራችን ለመቆየት አልተቻለውም፡፡
የፋሽስት ቅኝ ገዢ ኃይል በሀገራችን የቆየባቸው አምስት ዓመታትም ሕዝባችንን በዘር፣ በጎሳና በሃይማኖት ከፋፍሎ አንድነታችንን ለመበታተን ያደረገው ጥርት እንዳሰበው ሊሳካለት አልቻለም ነበር፡፡ ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያን፣ ለመላው ጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይም ደግሞ ነጻታቸውን ለሚያፈቅሩ የሰው ልጆች ሁሉ- የመንፈስ ኩራትና ክብር የኾነውን ኢትዮጵያዊነትን የነፃነት መንፈስና አንድነት ለመበታትን የሸረበው ሴራ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ቆራጥ ታላቅ ተጋድሎ ከሸፈ፡፡
ይህ የኢትዮጵዊነት የነጻት ውብ ዜማ፣ የአንድነት ኅብር መንፈስ አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦችን በፍቅርና በወንድማማችነት መንፈስ የሚያስተሳሰር የታሪክ ምዕራፍን ከፈተ፡፡ የፋሽስት ኃይል በኢትዮጵውያን ጀግኖች- አባትና እናት አርበኞችና በወዳጅ ሀገሮች የተባበረ ክንድ ከኢትዮጵያ ምድር በሃፍረት ተሸንፎ ተባረረ፡፡
ይህ ዐድዋውን ድል ያደሰው የጀግኖች ኢትዮጵያውያን አርበኞች የነጻነት ተጋድሎም- ከአፍሪካ አሜሪካውያኑ የጥቁር ሕዝብ መብት ተጋዮች፣ ከማርከስ ጋርቬይ እስከ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ከአፍሪካውያኑ- ከኬንያው የነጻት አባት ከጆሞ ኬንያታ እስከ ጋናው የነጻት አባት ዶ/ር ክዋሜ ንኩርማ፣ ከደቡብ አፍሪካው የነጻትና የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ ከኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ እስከ ኦሊቨር ታምቦ… ወዘተ. ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትእምርት/Symbol፣ ሰው የመኾን ክብርና ከፍ ያለ የመንፈስ ልእልና፣ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክና ቅርስ ሕያው አሻራ ሆኖ ተመዘገበ፡፡
ይህ የኢትዮጵዊነት የነፃት አኩሪ ተጋድሎ ቅርስ በአፍሪካውያንና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ልብ ውስጥ ያለውን ትርጉም በተመለከተ ኔልሰን ማንዴላ ከላይ በመግቢያዬ በጠቀስኩት ‘‘Long Walk to Freedom’’ በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ በአድናቆት ገልጸውታል፤
‘‘Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracting me more strongly than trip to France, England, and America combined I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me an African.’’
3. እንደ መደምደሚያ
እንግዲህ መቼም ይህ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ አውስትራሊያ፣ ከህንድ እስከ ቻይና የተሰማ የኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞቻችንን ተጋድሎ፣ ያጎናጸፉንን ክብርና ኩራት በዚህች አጭር ገጽ ለመተረክ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የእነዚህ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ውለታም በምንንም ዋጋ የሚለካ፣ የሚተመን አይደለም፤ ምክንያቱም ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት የተከፈለበት ነውና!!
አገራችንን ለነጻነትና ለሉዓላዊነት በተደረገ የጦር ሜዳ ውሎ- በጀግንነት፣ በዲፕሎማሲውና በፖለቲካው መስክ፣ በአርቱና በሥነ ጥበብ፣ በስፖርቱና በተሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ የአገር ባለውለታ የሆኑ፣ የትውልድ አርአያና ተምሳሌት የሆኑ ዕንቁዎቻችንን፣ አርበኞቻችን፣ ጀግኖቻችንን የሚገባቸውን ክብርና ዕውቅና ልንሰጣቸው የሚገባ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ መንግሥትና አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ለአገርና ለወገን ፍቅርና መቆርቆር ያላቸው ግለሰቦችና ባለሀብቶች የጀመሩትን ለእነዚህ ባለውለታዎቻችን፣ ጀግኖቻችን የሚገባቸውን ክብርና ዕውቅና እንዲያገኙ እያደረጉት ያለውን በጎ እንቅስቃሴ አጠናክረው በተቀናጀ መልኩ ይቀጥሉበት ዘንድ የሚገባ ነው እላለኹ፡፡
መንግሥት ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃት ክቡር መንፈስን ለናኙ ጀግኖች፣ አርበኞቻችን ለትውልድ ትውልድ የሚተላለፍና ቅርስ የሚኾን ቋሚ መታሰቢያ እንዲኖራቸው ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ሊቀጥልበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋርም ተያይዞ አንድ ጥያቄ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ይኸውም፤
በኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን የነጻት ተጋድሎ ታሪክና አፍሪካዊ ገናና ሥልጣኔ ወኔና ብርታት ሆኗቸው ዘረኛውንና አስከፊውን የአፓርታይድ ሥርዓትን ከሕዝባቸው ጫንቃ ላይ ለማውረድ በጽኑ ለታገሉትና ለ፳፯ ዓመታት ለተጋዙት ለጀግናው፣ የነፃት አርበኛ ኔልሰን ማንዴላ/ለማዲባ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ መታሰቢያ እንዲሆንላቸው የወሰንን እኛ ኢትዮጵያውያንና የአፍሪካ አገራት፤ እንዴት ለአፍሪካ አገራትና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ትልቅ ወኔንና መነሳሳት የፈጠረው ዐድዋን ድል እና እንዲሁም የጀግኖች አባትና እናት አርበኞቻችንን የነጻት አኩሪ ተጋድሎ የሚተርክ የታሪክ ቅርስ/አሻራ በኅብረቱ አዳራሽ ቋሚ መታሰቢያ ወይም መዘክር እንዴት ሊነፈገው ቻለ?!
መቼም ቢሆን የትናንትናውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትንም ሆነ የዛሬውን የአፍሪካ ኅብረት ከሀገራችን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ከሕዝቦቿ አኩሪ የነፃት ተጋድሎ ውጪ ፈጽሞ፣ ፈጽሞ ማሰብ የሚቻል አይደለም፡፡ ስለሆነም መንግሥት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ነጻነቱን የሚያፈቅር ኢትዮጵያዊ ኹሉ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በባህልና በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሠሩና የተሰማሩ አካላትና ምሁራንም የበኩላቸው ጥረት በማድረግ- የጀግኖች ኢትዮጵያውያን፣ አርበኞች አባቶቻችንና እናቶቻችን አኩሪ የነጻት ተጋድሎ የሚዘክሩ ቋሚ የታሪክ አሻራ ልናኖርላቸው ይገባናል፡፡
በቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን የክቡር የሕይወት መሥዋዕትነት የነጻነት አየርን ለመተንፈስ የታደልን እኛ ልጆቻቸው- ዛሬ ለጀግኖች አርበኞቻችን ያለንን ክብርና ፍቅር በተግባር የመግለፅ ሁላችንም ታሪካዊ ግዴታና ሓላፊነት እንዳለብን ይሰማኛል፡፡
እንኳን ለድል በዓላችን/ለአርበኞች ቀን አደረሰን!
ሰላም!