ወላጅ ነኝ፤ ልጆቼ ላልተማሩበት አልከፍልም!!
(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)
ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ልጆቻችን ቤት በተቀመጡበት ሁኔታ ወላጅ ከ50 እስከ 70 በመቶ ወርሀዊ ክፍያ ይክፈል ብሎ ትምህርት ሚኒስቴር መበየኑን ሰማሁ። ትምህርት ሚኒስቴር በክፍያ ጉዳይ በቀጥታ እጁን አስገብቶ እገሌ ይህን ያህል ይክፈል፣ እገሌ ይህን ያህል አይክፈል የማለት ሥልጣን ማን እንደሰጠውም በግሌ ግልፅ አልሆነልኝም። ከምንም በላይ ደግሞ ልጆቻችን ቤት በተቀመጡበት ሁኔታ ወላጆች ከወርሀዊ ክፍያቸው ከ50 እስከ 70 በመቶ ይክፈሉ ብሎ ሲበይን መነሻው ምን እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው።
ከፍተኛ ትርፍ የሚዝቁት፣ አንዳንዶቹም ትምህርትን እንደተራ ሸቀጥ ለሚያዩ የግል የትምህርት ተቋማት በጣም የወገነ መመሪያስ ለማውጣት ሚኒስቴሩ የተጣደፈው ለምንድነው? በት/ቤቶችና በወላጆች መካከል ያለው ውል ግልፅ ነው። ት/ቤቱ በክፍል ውስጥ ትምህርት ይሰጣል። ወላጅ ደግሞ ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ ይከፍላል። ይህ ውል ማክበር በማይቻልበት ሁኔታ ብድግ ብሎ እስከ 70 በመቶ ክፈሉ ብሎ ማወጅ ኢ ሰብአዊነት ነው። በአጭሩ ለህዝብ ውግንናን የሚያሳይ አይደለም። በዚህ ላይ ደግሞ መመሪያው ግልፅነት ይጎድለዋል። ምን ሲሆን ነው 50 በመቶ የሚከፈለው? ምን ሲሆን ነው 70 በመቶ የሚከፈለው? የሚለው። በእኔ ግምት ሆን ተብሎ ቀዳዳ ተከፍቶ የተተወ ይመስላል።
ከምንም በላይ ኮሚክ የሆነው የመመሪያው ክፍል ት/ቤቶቹ በቴሌግራም ትምህርት ይስጡ ማለቱ ነው።ይህ ካልተቻለም በስልክ ይላል።እንግዲህ ት/ቤቶቹ እስከ 70በመቶ የሚደርስ ቀለብ የተቆረጠላቸው ይህ እንደስራ ተቆጥሮ ነው ማለት ነው።
ለመሆኑ ለኬጂ እና ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በቴሌግራም ምን አይነት ትምህርት ሊሰጥ ታስቧል? ተማሪዎቹስ ምን መልኩ ሊያገኙት የሚችሉት? ስማርት ስልክ ወይንም የኢንተርኔት አክሰስ የሌላቸው ብዛት ያላቸው ወላጆች ምን ታስቧል?
ለመሆኑ ከወላጆች መካከል ምን ያህሉ በትክክል ቴክኖሎጂ ይጠቀማል? ከዚህ በፊት በዚህ መልክ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ልምድ አለ ወይ? ት/ቤቶቹ ይህን ባይፈፅሙ ትምህርት ሚኒስቴር በምን መልኩ ተከታትሎ ያርማል? የቴሌግራም ትምህርትን ሲቀበል ምን መነሻ ይዞ ነው?
ይገርማል!…ትምህርት ሚኒስቴር ፍፁም ወደ ባለሀብቶች የወገነ ውሳኔ ላይ የደረሰው በምን ምክንያት እንደሆነ ባስበው ባስበው ሊከሰትልኝ አልቻለም። በኮሮና ምክንያት ከዕለት ገቢው፣ ከሥራው ተፈናቅሎ ቤት ለተቀመጠ ወላጅ ድጎማ እንደማድረግ ልጆች ላልተማሩበት ይክፈሉ ማለት ኢ ሰብአዊነት ነው። በግሌ ይህ መመሪያ በወላጆችና በት/ቤቶች መካከል ክፍያን አስመልክቶ ያለውን ውጥረት ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የለውም። በግሌ ደግሞ አልቀበለውም።