Connect with us

ማስክ ስትለብሱ ወፍራም ፓንት እንዳትረሱ

ማስክ ስትለብሱ ወፍራም ፓንት እንዳትረሱ
Photo: Social media

መዝናኛ

ማስክ ስትለብሱ ወፍራም ፓንት እንዳትረሱ

ማስክ ስትለብሱ ወፍራም ፓንት እንዳትረሱ | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ወገኔ ዘንድሮ የመጣብን በሽታ እጅግ ውስብስብ ነው፡፡ ምልክቶቹም ሆነ የመተላለፊያ መንገዶቹ ብዙ በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ባለፈው የዓለም የጤና ድርጅት ከታማማሚዎች በሰበሰበው መረጃ መሠረት የኮሮናን ምልክቶች ዘርዝሮ ነበር፡፡ እናም ያን መረጃ አንብበኸው ከሆነ ማንኛውም የበሽታ ስሜት የኮሮና ምልክት ሊሆን እንደሚችል ትረዳለህ፡፡

ከምልክቱ በላይ ደግሞ ድፍረቱ የሚገርም በሽታ ነው፡፡ ከእግዜርና ከሳኒታይዘር ውጭ የሚፈራው ነገር የለም እኮ! ከጠቅላይ ሚኒስቴር እስከ ጤና ሚኒስቴር፣ ከጀኔራል እስከ ሆሊውድ ስታር፣ ከእግር ኳስ ተጫዋች እስከ ሙዚቃ ተጫዋች ያገኘው ላይ ሁሉ ዘውዱን እየደፋ ሲያሰቃያቸው ከረመ እኮ! ከአረጋውያን ጋር ያለው ጠብ’ማ ‹‹እዚህ ምድር ላይ አያት የሚባል ነገር መኖር የለበትም›› ብሎ የተነሳ ነው የሚመስለው፡፡

መተላላፊያና መከላከያ መንገዶቹስ ቢሆኑ ለእኛ መች የሚመጥኑ ናቸው፡፡ ስሜታችንን መቆጣጠር ወይንም ደግሞ ኮንዶምን ባግባቡ መጠቀም አቅቶን በኤችአይቪ ስናልቅ ለኖርን ሕዝቦች ‹‹መዳፋችሁን ተቆጣጠሩ›› እንደመባል ምን ፈተና አለ? እጅና ፊትን ማጣላት ዜግነትን እና ማንነትን እንደማጣላት ቀላል አይደለማ!

ያም ሆኖ ግን የማይለመድ ስለሌለ ሰላምታውን እንደተውነውና እጃችንን በየደቂቃው መታጠቡን እንደለመድነው ሁሉ መዳፋችንን ከፊታችን ጋር ማለያየቱንም እንለምደው ይሆናል፡፡
አንዱ እኮ ነው!

መጸዳጃ ቤት እንደገባ በጥንቃቄ ጉድለት ካካውን በጠነቆለበት ጣቱ የአፍንጫውን ቀዳዳ ነክቶ ኑሯል፡፡ እናም ቀኑን ምራቁን በየጎዳናው ላይ ጢቅ እያደረገ ‹‹ይህቺ አገር ከመጠን በላይ ጠነባች›› እያለ ሲራገም ዋለ አሉ፡፡

ይሄን ቀልድ እስክሰማ ድረስ እኔም በማስክ ተሸፍኜ በነጭሽንኩርትና በዝንጅብል ያበዴ የራሴን ትንፋሽ እየማግሁ ‹‹አዲስ አበባ ተግማማች›› እያልኩ ከተማዋን ስወቅስ ሰንብቻለሁ፡፡

የሆነው ሆኖ ግን ‹‹በኮሮና ላለመታፈን በማስክ መታፈን መፍትሄ ነው›› ተብሏልና ነጭ ሽንኩርቱንም ሆነ ማስኩን መተው አያስፈልግም፡፡ ‹‹ላለመታፈን መታፈን›› የሚለውን ምክር አጠናክሮ መቀጠል ግድ ይላል፡፡

በቅርቡ ደግሞ ‹‹ኮሮና በመተንፈስና በማንጠስ ብቻ ሳይሆን በፈስም ልተላለፍ ይችላል ›› የሚል መረጃ ይፋ ሆኗል፡፡ ስለዚህ እንደ Face mask Ass mask ማስክ እስኪሰራ ድረስ ወፈር ያለ ፓንት መልበስ ይመከራል፡፡

ከዚህ ባለፈም ‹‹ተማክረው የፈሱት ፈስ አይሸትም›› እንደሚባለው ተነጥለው የፈሱት ደግሞ ኮሮና አያስይዝምና የምንተነፍስበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ እርቀትን ጠብቆ መፍሳትና ባቄላ አለመብላት ይጠበቅብናል፡፡

ሌላው ደግሞ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም ለማጎልበት ከአትክልትና ከነጭ ሽንኩርት በላይ ጭንቀትን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በሽታ መዳን የምንችለው በመጠንቀቅ እንጂ በመጨነቅ ስላልሆነ ቤታችን ስንውል በአዝናኝ ነገሮች እራሳችንን መጥመድ አለብን፡፡ ከሶሻል ሚዲያው ጎን በጎን ስፖርት መስራት፣ ፊልም መመልከት፣ መጽሐፍ ማንበብ፣ ሥራ መስራት ወዘተረፈ ያስፈልጋል፡፡

ኮሮና እንደሁ ከበሽታው ባልተናነሰ መልኩ መረጃውም ገዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ለሳንባችን ስናስብ በጭንቀት ተወጥረን ጭንቅላታችንን እንዳንጎዳ ከአንዳንድ መረጃዎች እራሳችንን ማራቅ አለብን፡፡ እንደኔ እንደኔ እንደውም መተላለፊያና መከላከያ መንገዶቹን ጠንቅቀን ካወቅን ሌላው እለታዊ መረጃ እንዲንሸበር ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የለውም እላለሁ፡፡ ይሄን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ ክፉ ክፉውን ብቻ ሳይሆን በጎ በጎውንም መመልከት ያስፈልጋል፡፡

ለምሳሌ ያህል በየቀኑ በዚህ ቫይረስ ከሚያዘውና ከሚሞተው ሕዝብ ይልቅ ያልተያዘውን እና አገግሞ የሚወጣውን መከታተል ይበጃል፡፡ ብሎም ያገኙትን ማንኛውንም ዜና ጥቅምና ጉዳቱን ሳይመዝኑ ሶሻል ሚዲያ ላይ ከሚለጥፉ ግድግዳዎች በመራቅ ጠቃሚ መረጃ የሚያጋሩንን ፎሎው ማድረግ ግድ ይላል፡፡

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top