ሰው በሰው ሞት ማትረፍ በሚፈልግበት የዓመፃ ዘመን፤
ሕይወትን ለወገን የሚሰጥ ሙያ፤
የሕክምና ባለሙያዎቻችን ከትናንቱ ይበልጥ ክብር ይገባችኋል፡፡
ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ
ብዙ ደጋግ ሰዎችን አይተናል፡፡ የደጋግ ሰዎቻችን መልካም ስራ ክፉዎችን እስከመርሳት አድርሶናል፡፡ ዛሬ ያ ሳኒታይዘር በአስር እጥፍ የሸጠውን ገብጋባ ሐጢአት ብዙ እጥፍ ጊዜ የሚያስተሰርዮ ልበ ቀና የህክምና ባለሙያዎችን እያየን ነው፡፡ እንዲህ ባለው ጊዜ ብዙ ሰዎች በሰው ሞትን መነገድ ብልጠት ቢያደርጉትም በዚህ የዐመፃ ዘመን ሕይወትን ለወገን የሚሰጥ ሙያ ባለቤት የኾኑ ወገኖቻችን ስለ እኛ እንቅልፍ አጥተዋል፡፡
ዛሬ ሁሉም ሰው ቤትህ ሆነህ አምልጥ ሲባል አደባባይ ውጡ፤ ከወረርሽኙ ጋር ተገናኙ፤ ተፋለሙና ድል አድርጉት ብሎ ሃገር ግዳጅ የሰጣቸው ባለሙያዎች ተጋድሎ ላይ ናቸው፡፡ ኮተቤ የካ የሚባለው ሆስፒታል ስለሚሰሩ ባለሙያዎች አሰብኩ፤ ይኼን እንቅልፍ አልባ ናቸው፡፡ ይኼኔ እንደ እኛ ጭፈራውና ሁካታው ሳይኾን እኛ ሰለቸን ያልነው ቤታችን የናፈቃቸው ናቸው፡፡
ከልጆቹ መጫወት ስላልቻለ የህክምና ባለሙያ አስባለሁ፡፡ እሱ ማቆያ የገባን ዜጋ ያኽል ለዜጋው ደህንነት ራሱን በሙያው ያቆየ ሻማ ነው፡፡ እነኚህ ሻማዎች አብርተው የሚበሩ እንጂ በርተው የሚቀልጡ እንዳይኾኑ ከጎናቸው ልንቆም ይገባል፡፡ ከእነሱ ጎን ስንቆም ስጋቱ ድል ይመታል፡፡ እርግጥ ነው ነገም ለእነሱ ሌላ አውደ ውጊያ አለ፡፡
በደሃ ሀገር የሚባትል የህክምና ባለሙያ እረፍት የለውም፤ ህይወት ዘመኑ የትግል ነው፡፡ ድህነት በሚወልዳቸው ደዌዎች ፋታ የለሽ ኑሮ ይገፋል፡፡ ራሱን መጠበቂያ ቁሳቁስ ቅንጦት ነው፡፡ አድነኝ ብቻ ብሎ የሚማጸን ታማሚ እንጂ የታመመ የሚድንበት መድሃኒትና ቁሳቁስ የሌለው ነው፡፡
በኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያ መሆን ዘመንን ለወገን አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ አንዱ ሲባል ሌላው ይተካል፡፡ በብላሽ ሰው ለማዳን ክህሎትና ፈጣሪን ተማምኖ ወደ ስራ ከመግባት በላይ ከባድ ሃላፊነት የለም፡፡ የዓለም ህክምና ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ጥበቡ የተሟላ ቁሳቁሱ የተረፈ ነው፡፡ የእኛ ግን አልቋልና የለም በሚባሉት የታጀበ ሲሆን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለወገን መቆም ያኮራል፡፡
ትናንት ህክምና ክቡር ሙያ ነው፡፡ ትናንት የሀገሬ ሰው ሀኪሙን ያከብራል፡፡ እንነግራችኋለን፤ ከትናንቱ ይበልጥ ክብር ይገባችኋል፡፡ ከትናንቱ ይበልጥ የምትከፍሉት የመስዋዕትነት ዋጋ ቃል ለገባችሁለት ሙያ ስለመኖራችሁ ማረጋገጫ ነው፡፡ ክብር ይገባችኋል፡፡ ፍቅርም ጭምር፤