Connect with us

«ታሞ ከመማቀቅ…» እንዲሉ!

«ታሞ ከመማቀቅ…» እንዲሉ!

ጤና

«ታሞ ከመማቀቅ…» እንዲሉ!

የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ገባ ተብሎ ሲጨናነቁ የሰማ አንድ ቀልደኛ «ኧረ ተረጋጉ፤ አትጨናነቁ ከኮሮና ቫይረስ ከሚብሱ አክቲቪስቶች ጋር እየኖርን አይደል?…» ብሎ አለ አሉ። አሁን ይሄ ቀልድ ነው ቁምነገር? ርግጥ ነው አክቲቪስቶቻችን እንደኮሮና ቫይረስ በቀናት ውስጥ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን አይቀጥፉም። ቀስ እያሉ ግን የጋራ የተባሉ መልካም እሴቶቻችንን፣ አንድነታችንንና ሰላማችንን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እየገዘገዙ እንዳይጥሉን ያሰጋል።

አገራችን አሁን ለገባችበት ውጥንቅጥ እያንዳንዱ ዜጋ ተጠያቂ ቢሆንም፤ በዘር፤ በሃይማኖት ለመከፋፈላችንና ለመጋጨታችን ግን አክቲቪስቶቻችን እና ፖለቲካችን ትልቅ ድርሻ አላቸው። እውነት ለመናገር ኅብረተሰባችን ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው፤ ሰብዓዊነትና የሕዝብ ፍቅር የሚሰማው፤ እንግዳ አክባሪ የሆነ ኩሩ ሕዝብ ነው። ይሁንና፤ አሁን አሁን ይህ ሁሉ በነበር ሊቀር ጫፍ የደረሰ ይመስላል። ዕድሜም፤ መጥኔም ለአክቲቪስቶቻችንና ለፖለቲካችን እያልኩ ወደ ኮሮና ቫይረስ ልመለስ።

እውነት ግን ይህ መነሻውን ቻይና ያደረገው የኮሮና ቫይረስ መድረሻውን የት ሊያደርግ እንዳሰበ የሚታወቅ ነገር አለ?… «ኧረ የለም» መልሳችሁ እንደሆነ አምናለሁ። እኔ የምለው ግን መድረሻው የትም ይሁን የት ቻይናውያንን በእጅጉ እየጎዳ ያለው ይህ ቫይረስ ከአክቲቪስቶቻችን በላይ የሚያስፈራና የሚያስጨንቅ ልንታገለው የማንችለው ክፉ ደንቃራ ይመስለኛል። እናንተስ ይህ አይሰማችሁም?

ቢመስላችሁ ጥሩ ነው! ምክንያቱም አያምጣው እንጂ ከመጣ እኮ እርግጠኛ ነኝ ለወሬ ነጋሪም ሳያተርፈን ጥርግርግ አድርጎ የውሃ ሽታ ያደርገናል። አክቲቪስቶቻችን ግን ምንም ቢሆን ዘርና ሃይማኖታችንን ለይተው እንጂ፤ እንደ ኮሮና ቫይረስ እያንዳንዳችንን ዋጥ ስልቅጥ አያደርጉም። ታዲያ ይህን ወረርሽኝ ቻይናውያኑ እየሰሩበትም እየታገሉትም ተቋቁመውታል። እኛ ብንሆንማ እንዳልኳችሁ ነው ለወሬ ነጋሪም አንተርፍም። ቻይናውያኑ ግን በአሁን ወቅት በሽታውን ለመቆጣጠር የማይፈነቅሉት ድንጋይ፤ የማይወጡት ተራራ፤ የማይወርዱት ቁልቁለት፤ የማይሻገሩት ድልድይ የለም።

አሁን በቅርቡ እንኳን ይህን አደገኛ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እና አደጋውን ለመቀነስ በሚል አንድ ሺህ የኮሮና ታካሚዎችን ማስተናገድ የሚችል ሆስፒታል በሁለት ቀናት ገንብተው ለአገልግሎት አብቅተዋል። ቻይናውያኑ ያጋጠማቸውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በሁዋንግ ጋንግ ከተማ የገነቡት ሆስፒታልም የውሃ፤ የኢንተርኔትና የተለያዩ ግብዓቶች ተሟልተውለት መሆኑ ደግሞ ይበልጥ የሚያስገርም ነበር።

ምን ይገርማል «እነሱ እኮ ያደጉ የተመነደጉ የበለፀጉ ሕዝቦች ናቸው» ብንልም ቅሉ፤ በእኛ አገር እኮ ከጉሮሯችን ቀንሰን በቆጠብነው ገንዘብ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ እያስቆጠርን የምንገኝ ተስፈኞች ነን። ታዲያ ይህም እጅግ መበልፀግንና ማደግ፤ መመንደግንም የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ ይሆን… ወይስ መጠበቅ፤ ወረፋ መያዝ፤ መሰለፍ ወዘተ… ዕጣ ፈንታችን ሆኖ ?…

የሆነ ይሁንና አሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምን ያህል የኅብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳቃለሉ መገመት አያዳግትም። ይሁን እንጂ፤’ አሁን ድረስ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በመኖሪያ ቤት እጦት እየተሰቃዩ ነው። «የግፍ ግፍ አንገፍግፍ» እንዲሉ የቤት ባለቤት ለመሆንና ከአስጨናቂው የኪራይ ቤት ለመውጣት ለዓመታት ካለ ከሌላቸው ቆጥበው ዕድለኛ ያልሆኑቱ ምሬታቸው የእውነትም መሪር ነው። ታዲያ መንግሥት ሆይ ይህን መራራ ወደ ጣፋጭ የምትቀይረው መች ይሆን? መቼም እንደ ቻይናውያኑ በሁለት ቀን አድርስ አንልህም ባይሆን በሁለት ዓመት ታዳርሰን ይሆን?…

የዚህን ጥያቄ መልስ ለራሱ ለመንግሥት ተውኩትና ወደ ቀደመው ነገሬ ወደ ኮሮና ቫይረስ ተመለስኩ። አሁን ማን ይሙት ከቻይና የተነሳው ይህ ክፉ ወረርሽኝ ኢትዮጵያን አያሰጋትም ነው የምትሉኝ?… እኔ በበኩሌ አይመስለኝም። ምናልባት እንደእናቶቻችን «አሟሟቴን አሳምረው» ብሎ መፀለይ ያዋጣ ይሆናል እንጂ የአየር መንገዳችን ድፍረት እንኳን የሚያዛልቀን አልመሰለኝም። እንዴ እኛን እንኳን እሺ ተውን። አይበለውና ቫይረሱ ቢገባ እዚሁ አገራችን ውስጥ ምን ያህል ቻይናውያን እንደሚጠቁስ አስባችሁታል?

አሁን እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቻይናውያን ቁጥር ከኢትዮጵያውያኑ ቁጥር የሚተናነስ አልሆነም። ከመላመዳቸው የተነሳ ተዋልደው ያሉትስ ቢሆኑ ቀላል ቁጥር አላቸው!? ታዲያ ይህ በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው እየተላለፈና የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የዓለም ስጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዳይገባ ከመከላከል ባለፈ አየር መንገዳችን ሥራውን ቢያቆም ምን ይጎድልበታል?

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በሽታውን አስመልክቶ በጀኔቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ «የዓለም መሪዎች ቫይረሱን ለመዋጋት በብርቱ እንዲታገሉ» ጥሪ አቀረቡ እንጂ ችግር የለውም በሽታው ከተከሰተበት አካባቢ የሚመጡ መንገደኞችን በግድ አስተናግዱ አላሉም። ቢሉስ ደግሞ መንግሥት ለዜጎቹ ደህንነት ቅድሚያ መስጠት አለበት። ተረቱስ ቢሆን «ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ» አይደል፤

ታዲያ ቻይናውያኑ ሳይቀሩ የወረርሽኙ ተጠቂዎች ቁጥር በየዕለቱ እያሻቀበ መምጣቱን ተከትለው ወደ አገራቸው ለመግባትም ሆነ ለመውጣት ባልፈለጉበት በዚህ ፈታኝ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዬን አላቋርጥም፤ እበርራለሁ ማለቱ የአየር መንገዳችንን ብቃት የሚያረጋግጥልን ቢሆንም፤ ሳያጠራጥረን ግን አልቀረም።

ታዲያ አያድርገውና ይህ ቫይረስ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ ወደኢትዮጵያ ቢገባ አየር መንገዳችን ይቀጣ ይሆን? ምክንያቱም ቻይና በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ አንድ ሺህ ማሻቀቡን ተከትላ በተገቢው ደረጃ መከላከል አልቻሉም ያለቻቸውን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሥራ የማባረር ርምጃ ወስዳለች። በዚህ አጣብቂኝ ወቅት አየር መንገዳችን እያሳየ ያለው ቆራጥነትና በራስ መተማመን ቢደንቅም፤ ቢያስደንቅም፤ ጉዳዩ አሳሳቢና ከባድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዳያስተዛዝበን እፈራለሁ። በተረፈ ግን ፈጣሪ ቻይናን ይጎብኝ አሜን!

አዲስ ዘመን የካቲት 9/ 2012 ዓ.ም

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top