Connect with us

ከመጪው ምርጫ ማን ምን ያተርፋል?

ከመጪው ምርጫ ማን ምን ያተርፋል?
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ከመጪው ምርጫ ማን ምን ያተርፋል?

ከመጪው ምርጫ ማን ምን ያተርፋል? (ጫሊ በላይነህ)

መጪው ምርጫ በእርግጠኝነት እንደሚካሄድ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መግለጻቸው የዛሬ ማለዳ ዜና ነበር፡፡ ለነገሩ እሳቸው ቢገልጹም ባይገልጹትም ምርጫ በአስገዳጅ መልኩ የሚካሄደው ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ በመሆኑ ነው፡፡ ግን ወ/ት ብርቱካን ይኸን ለመናገር የተገደዱት ምርጫው ላይካሄድ ይችላል የሚሉ ሥጋቶች እዚህም እዚያም ስለሚነሱ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡

እርግጥ ነው፤የሥጋት ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንዱና ዋናው የራሱ የምርጫ ቦርድ ዝግጅትን ይመለከታል፡፡ የዘንድሮ ምርጫ ቢበዛ መካሄድ የሚኖርበት በመጪው ግንቦት ወር ውስጥ ነው፡፡ ከግንቦት ወር ዘልሎ በክረምት ወራት ሊካሄድ የሚችልበት ዕድል ከመቶ 10 እጅ አይሆንም፡፡ ለዚህ ብቸኛ ምክንያቱ የክረምት ጊዜ ምርጫ ለማካሄድ አመቺ ባለመሆኑ ነው፡፡ እናም በዚህ የጊዜ ስሌት እና ያለፈውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ግምት ውስጥ ከትተን ነገሩን ስናየው በዚህ ወቅት ምርጫ ቦርድ ምርጫው የሚከናወንበት የጊዜ ሰሌዳ እንኳን ይፋ አለማድረጉ በቂ ዝግጅት ስለመኖሩ ጥርጣሬ ያስነሳል፡፡ የጊዜ ሰሌዳውን ተከትሎ የመራጮች እና እጩዎች ምዝገባዎች ቢበዛ እስከ መጪው ጥር ወር መጨረሻ መጠናቀቅ ነበረባቸው፡፡ ለዚህም ዝግጅት ስለመኖሩ ምንም ምልክት የለም፡፡

በፓርቲዎች በኩል ስንመለከት ኢህአዴግ ፈርሶ በብልጽግና ፓርቲ የተተካበት ሁኔታና እሱን የተከተለው የውዝግብ ዶሴ ገና መቋጫ አላገኘም፡፡ አዲሱ ፓርቲ እስካሁን በቦርዱ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ ተረጋግቶ ወደሥራ አልገባም፡፡

በተጨማሪም የህወሓት እና የኦሮሞ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች ውህደቱን መቃወማቸው በመጪው ምርጫ ሒደት ላይ ተጽዕኖ ይኑረው/ አይኑረው በአግባቡ አልተተነተነም፡፡

በሌላ በኩል ወደ 70 የሚጠጉ ፓርቲዎች ደግሞ በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ደስተኛ አይደሉም ብቻ ሳይሆን ካልተቀየረ ሞተን እንገኛለን በማለት የቦርዱን ስብሰባ ረግጠው እስከመውጣት ደርሰዋል፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች እያሰቡ ያሉት ስለመጪው ምርጫ አለመሆኑ በራሱ ያሳስባል፡፡ እነዚህ ተደማምረው ሲታዩ መጪው ምርጫ የመካሄዱን ነገር ጥያቄ ውስጥ የሚጥሉ ናቸው፡፡

ፈልገውም ይሁን ሳይፈልጉ በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ጀዋር መሐመድ እና አቶ ለማ መገርሳ የማታ ማታ የሚያቆራኛቸው አንድ አስተሳስብ አግኝተዋል፡፡ አቶ ለማ በግልጽ ውህደቱን በመቃወማቸው በቀጣይ የራሳቸውን ሚና እንዲለዩ የሚገደዱበት ሁኔታ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ምናልባት ከተደራጁ የኦሮሞ ፓርቲዎች አንዱን በመቀላቀል ተቃዋሚ ሆነው ሊመጡ እንደሚችሉ ወይንም ከመሰሎቻቸው ጋር አዲስ ፓርቲ ሊመሰርቱ ይችለሉ የሚሉ ቅድመ ግምቶች አሉ፡፡ ይህም ሆኖ የምርጫው ጊዜ ከመድረሱ አኳያ ሁለተኛው አማራጭ የመሳካቱ ነገር ጠባብ ይመስላል፡፡

ጀዋርን በተመለከተ በግል ያራመደው አቋም እርስ በርስ የተምታታ ነው፡፡ ከወራት በፊት ባደረገው የተከብቤያለሁ ጥሪ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ምርጫው መራዘም አለበት የሚል አቋም ሲያራምድ ነበር፡፡ በቅርብ ሳምንታት ወደአሜሪካን ሀገር ሄዶ ደግሞ ሀሳቡን በመቀየር በምርጫ በመወዳደር አብላጫ ወንበር እንደሚያገኝ በሙሉ መተማመን ሲናገር ተደምጧል፡፡ ግን እንዴት ለሚለው ዝርዝር መልስ ስለመስጠቱ የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ መረጃ የለውም፡፡ ጀዋር በምርጫ ለመሳተፍ በዜግነት አሜሪካዊ በመሆኑ ከዚያ አስቀድሞ ዜግነቱን የመመለስ ጣጣ ማጠናቀቅ አለበት፡፡ እሱን አጠናቆ አዲስ ፓርቲ መስርቶ ወደምርጫ ለመግባት ግዜው አጭር ሊሆን ስለሚችል እሱም ካሉት የኦሮሞ ፓርቲዎች በአንዱ ለመግባት ሊገደድ ይችላል፡፡ እነዚህ ጊዜ የሚፈልጉ ያልተጠናቀቁ መሬት የረገጡ እውነቶች ምርጫው በወቅቱ እንዳይካሄድ ገፊ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ የብዙዎች ግምት ሆኗል፡፡

ምናልባት ፓርቲዎች ተመካክረው ምርጫውን ለማራዘም ቢስማሙ እንኳን ሕገመንግሥታዊ ድጋፍ አያገኙም፡፡ አጣብቂኙ ነገር የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ በማንና በምን ማንዴት መንግሥት በሥልጣን ላይ ሊቆይ ይችላል የሚለው ማንም ሊመልሰው አይችልም፤ የፓርቲዎች ስምምነትም ቢሆን፡፡ ምናልባት እስከመጪው ምርጫ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ካልተቻለ በስተቀር አሁን ያለው መንግሥት ሥልጣን ዘንድሮ የሚያበቃ ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ያለው ብቸኛ አማራጭ ምርጫውን ማካሄድ ብቻ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡

ምናልባትም ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ትላንት በኦስሎ ሽልማታቸውን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር ላይ የምርጫውን መካሄድ ማረጋገጣቸው ዘንድሮ ምርጫው የማይቀር ለመሆኑ ትልቅ ማረጋገጫ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ እናም በአሁን ሰዓት ወሳኙ ጥያቄ በቀሪው አጭር ጊዜ በጥድፊያ በሚካሄድ ምርጫ ማን ሊያተርፍ ይችላል? እንዴትስ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ እና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ የሆነ ምርጫ ማከናወን ይችላል የሚለው ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ/ መንግሥት ለዚህ ጥያቄ የሚተገበር፣ ተአማኒ የሆነ መልስ ሊሰጡ ይገባል፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top