Connect with us

ለሕዝብ እሰራለሁ እያሉ “ሕዝብማ ይሳሳታል” ማለት ነውር ነው

ለሕዝብ እሰራለሁ እያሉ "ሕዝብማ ይሳሳታል" ማለት ነውር ነው፤ የሚሳሳት መጀመሪያውኑ "ምረጠኝ" አይባልም!!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ለሕዝብ እሰራለሁ እያሉ “ሕዝብማ ይሳሳታል” ማለት ነውር ነው

ለሕዝብ እሰራለሁ እያሉ “ሕዝብማ ይሳሳታል” ማለት ነውር ነው፤ የሚሳሳት መጀመሪያውኑ “ምረጠኝ” አይባልም!!

(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬ ቲዩብ)

“ህዝብ አይሳሳትም!” በሚለው ካልተስማማን ህዝብን ምረጠኝ ብሎ ድምጹን መጠበቅ በአንድ ምላስ ሁለት ቃል ነው፡፡ የሚሳሳት ሲመርጠን ልክ ሲተወን የተሳሳተ እያልን መራቀቁ ደርዛችንን ቢያጋልጥ እንጂ ብቃታችንን አይመሰክርም፡፡

የዘንድሮ ምርጫ በብዙ መልኩ ጥሩ ሂደት ነበረው፡፡ በተለይም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሌብነት የማይታማ፣ ለሆዳቸው የተገዙ የሥራ ሃላፊዎች ያልታጎሩበት፤ ሁሉንም በእኩል የሚመለከት ለመሆኑ ጥርጥር የለንም፡፡

 ከዚያ ሲያልፍ የብልጽግናው መሪ በአደባባይ “ድምጽም ይከፋፈላል፣ ለማኔጅመንትም ያስቸግራል፤ እኛም ለፉክክር አይመቸንምና ሰብሰብ በሉ” ሲሉ ከርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ከመሰብሰብ መበተንን መምረጥ ቀጥለው አሁንም ብዙ ናቸው፡፡ ወረቀት ዘርግተን እያገላበጥን የምንመርጥ ምርጫ ብዙ ዜጎች ሆነናል፡፡ እውነት ለመናገር ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ አሜባ ለመራባት ምክንያት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ሁሉም ሰው ሊቀመንበር መሆንን ስለሚሻ ፓርላማ እንዳማረው ይቀራል፡፡

በአዲስ አበባ አብን ከባልደራስ በጋራ በመስራቱ ውጤቱ ታይቷል፡፡ በተቃራኒው ግን የከተማዋ ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብዙ በመሆናቸው ብዙ ሰው ያልመረጠው ገዢው ፓርቲ በአብላጫ ድምጽ ብሂል ድል አድርጓል፡፡

ህዝብ የፈለገውን መምረጥ ይችላል፡፡ ምረጠኝ ያሉትን ህዝብ ውጤት አይተው መሳሳት ጠባይህ ነው እያሉ ማሽሟጠጥ ዲሞክራሲያችንን በእንፉቅቅ ያስኬደዋል እንጂ ለድልና ለስኬት አያበቃውም፡፡

ደሴ ምን የመሰለውን ፓርላማ ልናየው የሚገባ ሰው አልመረጠችም፤ የመረጠችው ግን ችግር አለበት ማለት አይደለም፡፡ የደሴ ህዝብ የቱ ጋር ምን ማድረግ እንዳለበት በአግባቡ ያውቃል፡፡ ህዝብም ነው፤ ለራሱ የሚያስፈልገውን እኛ ከነገርነው ምርጫ ብሎ ነገርስ ቀድሞውኑ ምን ያደርጋል?

በተመሳሳይ እንደ ጣሂር ያሉ ትንታግ ወጣቶች፣ እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ እንደ አንዱአለም ያሉ በመስዋዕትነት የተገለጡ ጀግኖች ያገኙት ድምጽ ለፓርላማ አላበቃቸውም፤ ይሄ ማለት የመረጣቸው ህዝብ ተሳስቷል ማለት ግን አይደለም፡፡ እንደ ፖለቲከኛ ምን ጎድሎን ድምጹ ከእኛ ራቀ ማለትን ይሻል፡፡ 

እንደ ደጋፊ የእኔ ድጋፍ ወይስ የምደግፈው ጉድለት ወይስ ሌላ ምክንያት ብሎ መጠየቅን ይፈልጋል፡፡

“ህዝብ ይሳሳታል” የተሳሳተ ሀሳብ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እኮ ልክ መሆን ወይም አለመሆን አይደለም፤ መፈለግ እና አለመፈለግ መምረጥ እና አለመምረጥ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ያን መፈለግ አለመፈለግ ለማረጋገጥ ያለው አውድ እንጂ የቡድን የግል ወይም የስብስብ መሻት መሆን አለመሆን አይደለም፡፡

ገና ብዙ መንገድ ይቀረናል፡፡ “ከተማ እየተቃጠለ ምርጫ ምን ያደርጋል?” ብሎ ቀስቅሶ ምርጫ ካርድ እንዳይወሰድ ሳንካ የሆነው አካል ዛሬ “ለምን ፓርቲዬ ተሸነፈ?” ብሎ “ህዝብ ድሮስ ምን ያውቃል?” ቢል አለማወቁን እናውቃለን እንጂ ውጤት አያመጣም፡፡

ገና ብዙ ምርጫ ይቀረናል፡፡ የምርጫ ማግስት የሚከስሙ ፓርቲዎች ቢያንስ ከዚህ ምርጫ በኋላ እንዲህ ያለ ስሸነፍ “ቢሮዬን ልዝጋ” ባይነትን አስወግደው አምስት አመት ተዘጋጅተው የጎደላቸውን ሞልተው፤ ህዝብ ምን እንደሚፈልግና ሀገር ምን እንደሚያስፈልጋት አስበው ከመጡ ድል ነገ ነው፡፡ ምክንያቱም ህዝብ አይሳሳትምና፤

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top