ቤልጀማዊ ህፃን ላዉረንት ሲመንስ ከትምህርት ቤት ዉጭ እንደማኛዉም የዘጠን ዓመት ልጅ ነዉ፡፡ የቪዲዮ ጌሞችን ይጫወታል ፤ ፊልሞችን ይመለከታል፤ ጉዞም አብዝቶ ይወዳል፡፡ ትምህርት ላይ የሚያሳየዉን ብቃት የተመለከተ ሰዉ ግን እድሜዉ ዘጠኝ አመት መሆኑን ይጠራጠራል፡፡ ከአስር ዓመት በላይ ከሚበልጡት ተማሪዎቸ ጋር ተቀላቅሎ ትምህርቱን ሲከታተል የነበረዉ ይህ የተለየ አዕምሮ የታደለ ህፃን በመጀመሪያ ዲግሪ ሊመረቅ የቀሩት ቀናት ብቻ ናቸዉ፡፡
በመጭዎቹ ቀናት የተለየ ነገር ካልተፈጠረና ላዉረንት ኔዘርላንድ በሚገኘዉ ኢንድሆቨን የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየሰራ ያለዉን የመመረቂያ ፕሮጀክት ማጠናቀቅ ከቻለ በመጪዉ የፈረንጆቹ ታህሳስ ወር በኤሌክትሪካ ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዉን ያገኛል፡፡ አብዘሀኛዉ ተማሪዎች ይህንን ፕሮግራም ለማጠናቀቅ ሦስት አመታት የሚፈጅባቸዉ ቢሆንም በሚያስገርም ሁኔታ ላዉረንት ትምርቱን ለመጨረስ የወሰደበት ጊዜ 10 ወራት ብቻ ነዉ፡፡
አጅግ አስደናቂ የሆነዉ የመረዳትና በአጭር ጊዜ ዉስጥ በርካታ መረጃዎችን መቀበል አቅሙን የተመለከቱት መምህራን የሚወስዳቸዉን ኮርሶች በእሱ ፍጥነት ልክ በማስኬዳቸዉ በርካታ የትምህርት ዓይነቶችን ከተመደበላቸዉ ሰዓት እጅግ ባነሰ ጊዜ ዉስጥ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡
“በጣም የተለየና አስደሳች ነበር” ፒተር ባልቱስ የተባለ የተቀናጀ ኤሌክትሮኒክስ አስተማሪ በዕድሜ ትንሽ የሆነዉ ተማሪዉን በማተማር ስላሳለፍዉ ጊዜ ሲጠየቅ፡፡ ” የላዉረንት የትምህርት አቀባበል ችሎታ በጣም ከፍተኛ ነዉ፡፡ ሁሉም ነገር በጣም በፍጥነት ነበር የሚሄደዉ፡፡ በአጭር ጊዜ ዉስጥ በርካታ ማቴሪሎችን ነዉ ማጠናቀቅ የቻልነዉ”
የላዉረንት ወላጆች ገና ከህፃንነቱ ጀምር የተለየ ችሎታ እንደነበረዉ አያቶቹ ይናገሩ እንደነበር አስታዉሰዉ እነሱ ግን ከዛ በፊት የልጃቸዉን ተለየ አቅም ትኩረት ሰጥተዉ አስተዉለዉት እንደማያዉቁ ይገልፃሉ፡፡ አራት አመት ሲሞላዉ ወደ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሄደዉ ላዉረንት በስድስት አመቱ እስከ ሀይስኩል ያለዉን የትምህርት እርከን ማጠናቀቅ እንደቻለ ይናገራሉ፡፡ ከዚያም ወደ ዩኒቨርሲቲ ካቀና በኋላ ሁሉም መምህራኖች ስለልጁ አስደናቂነት አዉርተዉ አይጠግቡም ነበር በማለት ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን ልጃቸዉ ያለዉን እጅግ የተለየ መረዳት ችለዋል፡፡
ይህ ብዙዎች “child genius” በማለት የሚጠሩት የዘጠን ዓመት ህፃን በቀጣይ ህክምና በማጥናት የሰዉነት አካላትን መተካት የሚችል ሰዉ ሠራሽ የሰዉነት ክፍል ( አርቲፊሻል ኦርጋን ) መስራት እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ ምንም እንኳን በርካታ ባለሙያዎች ይህ የትምህርት ዘርፍ በህክምናዉ ዓለም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ዘመኑ የደረሰበት ተመራጭ ዘዴ እንደሆነ ቢመሰክሩም ላዉረንት ይህንን የትምህርት ዘርፍ ለማጥናት የወሰነበት ግን የራሱ ግላዊ ምክኒያት ነዉ፡፡ እሱን ያሳደጉት አያቶቹ በልብ በሽታ እንደሚሰቃዩና እንዲህ ያሉ ሰዎችንም መርዳት እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡