በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን የቤጊ እና ቆንዳላ ወረዳዎች በታጠቁ ኃይሎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ውጊያ እየተካሄደ እንደሚገኝ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ ውጊያውን እያካሄዱ ያሉት የታጠቁ ኃይሎች የኦነግ ወታደራዊ ክንፍ አባላት ናቸው ብለዋል። በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ በመከላከያ ሰራዊት እና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች መካከል ውጊያ መቀስቀሱን የዓይን እማኞች ተናገሩ።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የቤጊ ወረዳ ነዋሪ በአካባቢው ውጊያ የተቀሰቀሰው ከአራት ቀን በፊት እንደሆነ ተናግረዋል። ከቀናት በፊት የመንግስት ወታደሮች የኦነግ ታጣቂዎችን በመክበብ ለመማረክ ሙከራ ማድረጋቸውን የተናገሩት እኚሁ ነዋሪ ሆኖም “ታጣቂዎቹ ሰብረው በመውጣታቸው ከበባው ወደ ውጊያ ተቀይሯል” ብለዋል። በውጊያው አንድ ሰላማዊ ሰው መገደሉን ማረጋገጣቸውን ለዶይቼ ቨለ ተናግረዋል።
“የመንግስት ወታደሮች የኦነግ ሀይሎችን ለመማረክ ፈልገው እንደ መጡ እና በእጅ ሊይዟቸው እንደሞከሩ ነው የሰማሁት ነገር ግን ያን ማድረግ ስላልቻሉ ይመስለኛል በቀጥታ ወደ ውጊያ ገቡ። ይህንኑ ተከትሎ ህዝቡ ችግር ውስጥ ነው ያለው። አንድ አብዲ የሚባል ልጅ ጋርጀላ የሚባል ስፍራ ላይ ገድለውት ሜዳ ላይ ጥለውታል። ማን እንዳደረገው የታወቀ ነገር የለም። ከቤጊ ዝቅ ብሎ የሚገኝ ስፍራ ነው ይህ የሆነው። አሁን እውነት ለመናገር ያለው ነገር እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል። ምክንያቱም ገንዘብ ያለው ልጆቹን ይዞ ከአካባቢው ሸሽቶ ወጥቷል። እየተጠቃ የሚገኘው ወደ የትም መሸሽ ያልቻለው ደሃው ነው” ሲሉ ነዋሪው በአካባቢው ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ኮቦር በምትሰኝ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው ሃሮ ዲማ በተባለ አካባቢ በመከላከያ ሰራዊት አባላት እና በኦነግ የታጠቁ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ መስማታቸውን ተናግረዋል። ውጊያው አሁንም ድረስ አለመቆሙንም ጭምር እኚሁ የአይን እማኝ ምስክርነታቸውን ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል።
“በወቅቱ የነበረው ነገር ሃሮ ዲማ የተባለ አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ነበር። እኔ ራሴ እዚያ ነበርኩ። የመንግስት ሀይሎች የኦነግ ታጋዮችን ለመክበብ ሙከራ አድርገው ነበር። ነገር ግን የኦነግ ታጋዮች ሰብረው መውጣታቸውን ነው የሰማሁት። ባለፈው ሀሙስ ምሽት ከሁለት እስከ ሶስት ሰዓት ድረስ ያለማቋረጥ ተኩስ ነበር። ቅዳሜ እና እሁድም እንዲሁ ሲዋጉ ነበር። አሁን ባለበት ሁኔታ መረጋጋት ብሎ ነገር አይታሰብም” ሲሉ የሁኔታውን አሳሳቢነት ገልጸዋል።
ምንጭ:-ዶይቼ ቨለ