Connect with us

የኦሮሚያ ክልል የሚከሰው እነማንን ነው?

የኦሮሚያ ክልል የሚከሰው እነማንን ነው?
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

የኦሮሚያ ክልል የሚከሰው እነማንን ነው?

የኦሮሚያ ክልል የሚከሰው እነማንን ነው? | (ከ- ጫሊ በላይነህ)

የኦሮሚያ ክልልዊ መንግሥት በ”ግጭት” የተሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ አደርጋለሁ አለ የሚል ዜና በጠዋት ስሰማ ለብቻዬ ስቄያለሁ፡፡ እንግዲህ የክልሉ ሹማምንት መደበኛ ሥራቸውን ስለሠሩ እንድናጨበጭብላቸው ሳይፈልጉ አልቀረም፡፡ የዜናው ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡፡

“በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ በተከሰተው ግጭት እጃቸው ያለበት አካላትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ የክልሉ መንግስት ገልጷል።
የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ እንደተናገሩት፤በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን የሠላም መደፍረስ ተከትሎ በቀጥታ ለክልሉ ተጠሪ በሆኑ 19 ዋና ዋና ከተሞች ላይ በተካሄደው የሠላም ኮንፈራንስ የህዝቡ አቋም በግጭቱ እጁ ያለበት አካል ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆን የሚል ነው። የክልሉ መንግስትም ከሕዝብ የተለየ አቋም የለውምና ይህን ፍላጎት ይተገብራል…”ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

ለዚህም ደርሰናል፡፡ መንግሥት ሕዝብን ከማናቸውም ጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነቱ የሚወጣው “እባክህሥራህን ሥራ” እየተባለ መሆኑ ያስገርማል፡፡

አዎ!…ጠ/ሚኒስትራችን ሰሞኑን በሰጡት የአስከሬን የዘር ቆጠራ ውጤት መሠረት በኦሮሚያ በተለኮሰ የዱርዬዎች ጥቃት በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ኦሮሞዎች ሞተዋል፡፡ ጥያቄው የእገሌ ብሔር በብዛት ሞቷል በሚል ቀመር መቆራቆስ አይደለም፡፡ አንድም ኦሮሞ፣ አንድም፣ አማራ፣ አንድም ጋሞ፣ አንድም ሀዲያ፣ አንድም ስልጤ፣ አንድም አርጎባ፣ አንድም ኢትዮጵያዊ ለምን ይሞታል ነው፡፡ “የፖለቲካ ነጋዴዎች” ተከፋን ባሉ ቁጥር ንጹህ ወገናችን የደም ዋጋ ለምን ይከፍላል?

ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ጉዳይ ከትግዕስትና ከሆደ ሰፊነት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ገለጻ ተራ ተረት ነው፡፡ ክብር ጠ/ሚኒስትሩ በአዲስአበባ መሰል ጥቃት ቢነሳ ስለትግዕስት የሚያስቡበት ጊዜ እንደሌላቸው በተግባር አሳይተውናል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የቡራዩ ጥቃትን ለመቃወም ሰልፍ የወጣ የአዲስአበባ ወጣት ላይ ቃታ ተስቦ አይተነዋል፡፡ ሰልፍ መውጣቱ ብቻ እንደወንጀል ተወስዶ ለእስር መጋዙንም አንረሳውም፡፡ በሠላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሰው እስክንድር ነጋ “ጦርነት እንገባለን” የሚል ዛቻ የተሰነዘረበት በክቡር ጠ/ሚኒስትራችን መሆኑን አንዘነጋውም፡፡

እሳቸው ግን የሾርት ሚሞሪ ነገር ሆኖባቸው፣ ይህን ሁሉ ረስተው ዛሬ ሕግና ሥርዓት ስለማስከበር ሲነሳባቸው በተቃራኒው ስለበዛ ትግዕስት ጠቀሜታ ሊሰብኩን ይሞክራሉ፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትራችን በተለይ ጥቃቱ በተስፋፋበት በኦሮሚያ እስከዛሬ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ያልተቻለው የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ሆደ ሰፊ በመሆናቸው እንደሆነ ሰሞኑን ነግረውናል፡፡

ከሀይልና ከጉልበት ይልቅ ምክክር ይሻላል ተብሎ በመታሰቡ መሆኑን አክለዋል፡፡ ይህ የሳቸው ሀሳብ ነው፡፡፡ በእኔ አረዳድ ግን አንድ ሀገር ሕግና ሥርዓትን የሚጥሱ ሀይሎችን በማስታመም አይጠበቅም፡፡ የፖለቲካ ምህዳርና ዴሞክራሲ የሚገነባው ሥርዓት አልበኞችን እሹሩሩ በማለት ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ መልክ የተገነባ ሀገርም አላየንም፤ አልሰማንም፡፡

እናም የመንግሥት መለሳለስ ሄዶ ሄዶ ሥርዓት አልበኞችን በወጉ ለመቆንጠጥ እንኳን አላስቻለም፡፡ እየተገነባ ያለው ሥርዓት ዜጎችን እንኳን ከኢ- ሰብዓዊ ጥቃት መጠበቅ የማያስችል፣ ደካማ ሆኖ በገቢር እየታየ ነው፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ አጥቶ “የፍትሕ ያለህ” ብሎ በየአቅጣጫው በሚጮህበት በዚህ ወቅት እንኳን “ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን” በሚል መለሳለስ አድበስብሶ ለማለፍ መሞከር በሕዝብ ደምና እንባ እንደመነገድ ይቆጠራል፡፡

አሁን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጥቃት አድራሾችን ለሕግ አቀርባለሁ ማለቱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ጥያቄው ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሒደቱ ግጭቱን ያስነሱ፣ ያቀጣጠሉ ሀይሎች እንዲሁም በራሱ በኦዴፓ መዋቅር ውስጥ ከላይ እስከታች የተሰገሰጉትን ቅጥረኞችን መንጥሮ ለፍርድ ማቅረብ የሚያስችል ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ላኪውን ትቶ ተላላኪውን በማሳደድ የሕግ የበላይነት አስከብራለሁ ማለት በከንቱ ጉንጭን ማልፋት ነው፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top