ፓለቲካ
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፤
****
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ድርጅታዊ ኅልውና ባገኘባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የአማራ ህዝብ እውነተኛ ድምፅ በመሆን ህዝባችንን ከኅልውና ስጋት ለመታደግ፣ አንድነቱን ለማረጋገጥና ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ የተቀጣጠለውን ንቅናቄ ጠንካራና የማይቀለበስ መሰረት በማስያዝ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽዖ አድርጓል። የአማራውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጥያቄዎች ከፍ አድርጎ በመያዝና ለነፃነት፣ ለፍትኅና ለእኩልነት የሚደረገውን ትግል በመምራት ሕዝባዊ አመኔታን ለማትረፍ ችሏል፡፡
አብን ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ርእይ የሰነቀ ንቅናቄ በመሆኑ በአገራዊ የሽግግር ሂደት ውስጥ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ አማራው በታላቅ መስእዋትነት ያስገኘው ለውጥ መስመሩን እንዳይስት፣ በትግላችን የተንበረከኩ ጠላቶች መልሰው እንዳያንሰራሩ፣ የፈነጠቀው የለውጥ ተስፋ እንዳይጨነግፍና ዳግም የአገራችንና የሕዝባችን ኅልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ያላሰለሰ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ ጥረቶቻችን እንደሚጠበቀው ያህል ፍሬ ከማፍራት ይልቅ እየመከኑና የአገራዊው የፖለቲካ አውድ ከጊዜ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መምጣቱን የሚጠቁሙ በርካታ ምልክቶችን አስተውለናል፡፡ ንቅናቄያችን በዚህ ረገድ በአማራ ሕዝብና በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን ጽኑ አደጋ በሚያሳዩ ሦስት አበይት ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም በግልፅ ለማሳወቅ ይሻል፡፡
1. በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ በደሎችና የዘር ጥቃቶችን በተመለከተ፦
አብን በአገራችን በየትኛውም ክፍል፣ በማናቸውም ኃይልና በየትኛውም ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ የሽብርና የዘር ጥቃቶችን ያለማመንታት አውግዟል፡፡ የጋሞ ተወላጆች በቡራዩ በግፍ ሲጨፈጨፉ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ታፍሰው ወደ ጦር ካምፕ ሲጋዙ፣ የጌዴዖ ወገኖቻችን ሰብዓዊ እርዳታ ተነፍገው በርኃብ ሲረግፉ፣ ቤተ እምነቶች በእሳት ሲጋዩና አማኞች በጭካኔ ሲታረዱ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም ለዓለም ማኅበረሰብ በማሰማት ዜጎች ከጥቃት እንዲጠበቁና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብረው እንዲኖሩ ጥረት አድርገናል፡፡
በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ የተከሰቱትን ማንነትና እምነት ተኮር የዘር ማፅዳት፣ የዘር ፍጅትና ሰብዓዊ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለማስቆም ሰፊና ያላሰለሰ ትግል አድርገናል፡፡ ዜጎች በአማራነታቸው ተመርጠው ቤታቸው ሲፈርስና ሲፈናቀሉ፣ አማራ ተማሪዎች ከኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች በዘር ጥቃት ተገደው ሲለቁና እገታ ሲፈፀምባቸው፣ በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች በሚኖረው ሕዝባችን ላይ የዘር ማጽዳትና ሰብዓዊ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ከማውገዝና ማዕከላዊና ክልላዊ መንግሥታት ጥቃቶቹን በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ ግፊት ከማድረግ ባለፈ አደጋውን አስቀድሞ መከላከልና ማስቀረት በሚቻልበት መንገድ ላይ ሰፊና የተቀናጁ ጥረቶችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡
በዚህ ረገድ ንቅናቄያችን ካደረጋቸው በርካታ ጥረቶች መካከል ለአብነት በታኅሣሥ 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የሽብር ኃይሎች ማንነት ተኮርና በተለይም አማራውን ዒላማ ያደረጉ የዘር ጥቃቶች ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ከሁኔታዎች ጥናት በመተንበይ ለዚህ ማዕከላዊ መንግስቱ ልዩ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ በአካል ለአገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች ከማስረዳት ባለፈ በመግለጫ ጭምር በአንክሮ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
1.1. ከሰኔ 29 – ሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የተደረገው የዘር ማጥፋት፦
መንግሥት ተቀዳሚ የሆነውን ሰላምና ደኅንነት የማሰከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ባለመቻሉ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ሽፋን በማድረግ ጽንፈኛ ኃይሎች ጥምረት ፈጥረውና ተዘጋጅተው በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ በዋነኝነት በአማሮች ላይ፣ በተጓዳኝም በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ከሰኔ 29 ሌሊት እስከ ሐምሌ 1፣2012 ዓ.ም ድረስ በሽፋኑም ባስከተለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመትም እስከዛሬ ከታየው እጅግ ሰፊና አሰቃቂ የዘር ጥቃት ፈፅመዋል፡፡
አብን ይህን መረን የለቀቀ የዘር ማጥፋት ድርጊት በወቅቱ ከማውገዝ ባሻገር ጭፍጨፋው በተፈፀመባቸው አካባቢዎች የጥናት ቡድን ልኮ በደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ላይ ዝርዝር መረጃዎችን በማሰባሰብና በማጠናቀር ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ ሰነዱ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው የአገር ውስጥና ዓለማቀፍ አካላት በተለይም ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ፣ ለሰብአዊ መብት ተቋማትና ለአማራ አደረጃጀቶች እየተሰራጨ ሲሆን ፣ ንቅናቄያችን የዘር ፍጅቱ እውቅናና ትኩረት እንዲያገኝና ፍትህ እንዲረጋገጥ ቀጣይ እርምጃዎችን የሚወስድ ይሆናል፡፡
ሀ. የጥፋቱ አድማስ፦
ንቅናቄያችን ያደረገው ጥናት በወቅቱ በኦሮሚያ ክልል ከተፈፀመው ሰፊ የዘር ጥቃት ውስጥ በስድስት ዞኖች በሚገኙ በ26 ከተሞችና አካባቢዎች የደረሰውን ያካትታል፡፡ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ደብረዘይት፣ ናዝሬት፣ መተሐራ፣ ዝዋይ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ቡልቡላ፣ መቂ ከተሞችን፤ በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ፣ አሳሳ፣ ዶዶላ ከተሞችን፤ በምሥራቅ ሃረርጌ ዞን ሃረማያ፣ ባቴ፣ ከምቦልቻ፣ ጉርሱም ከተሞችን፤ በሃረማያ ወረዳ ኦዳ በሊናና መልካ ገመቹ አካባቢዎችን፤ በጃርሶ ወረዳ አሌ ከተማን፣ ሚደጋ ቶላ ወረዳን፤ በባቢሌ ወረዳ የተለያዩ ስፍራዎችን፤ እንዲሁም በሃረሪ ክልል ሃረር ከተማን፤ በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ጭሮ ወይም አሰበ ተፈሪ፣ ሚኤሶ፣ አሰቦት ከተሞችና አካባቢዎችን፤ በምዕራብ ሸዋ ዞን በተለይም ወሊሶ፤ በጅማ ዞን በጅማ ከተማ የደረሱትን የዘር ጥቃቶች ያካትታል፡፡
በጥቃቱ ከወደመው ኃብትና ንብረት መካከል 378 መኖሪያ ቤቶች፣ 111 ከብቶችና በርካታ የእርሻ ማሳዎች፣ የእህልና የሸቀጣሸቀጥ ክምችቶች፤ ከ300 በላይ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የንግድ ድርጅቶችና ህንፃዎች፣ 189 ሆቴሎችና ፔንሲዮኖች፣ 5 ትምህርት ቤቶች፣ 15 መድሃኒት ቤቶችና የህክምና ተቋማት፣ 8 ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት፣ 117 የተለያዩ ተሸከርካሪዎች ተዘርፈዋል፤ ተሰባብረዋል፤ በእሳት ተቃጥለዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናት፣ የእምነት መገልገያዎችና ታሪካዊ ቅርሶች ሳይቀር የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። በተፈፀመው እጅግ ከፍተኛ ጥቃት በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ኃብትና ንብረት ወድሟል፡፡
አብን በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ባጠናቀረው ዘገባ ግኝት መሰረት ከሰኔ 29 እስከ ሃምሌ 1/2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የተፈፀመው ጥቃት ዓለምአቀፍ የዘር ማጥፋት መስፈርቶችን የሚያሟላና የማያሻማ የዘር ማጥፋት ድርጊት መሆኑን ያምናል፡፡
ጥቃቱ በዘርና በእምነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ‹‹ነፍጠኛ›› እና ‹‹የነፍጠኛ ኃይማኖት›› በሚል የዘር ፍጅት መለያ በዋነኝነት በተጠቀሱት ዞኖች የሚኖሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማሮችን ዒላማ ያደረገ ነው፡፡ ሙስሊም አማሮችም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታይ ኦሮሞዎችና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ለጥቃት ተዳርገዋል፡፡
በዚህ የዘር ማጥፋት ጥቃት ከ200 በላይ አማሮች በአሰቃቂ ሁኔታ በሜንጫ፣ በዱላና በድንጋይ እየተጨፈጨፉ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የጥቃቱ ሰለባዎች ከቀላል እስከ ፅኑ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በጥቂቱ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ወገኖችም አስቸኳይ የእለት እርዳታ ፈላጊ ሆነው ሜዳ ላይ ተጥለዋል፡፡
የአማሮች ሀብትና ንብረቶች እየተመረጡ በመውደማቸው ጥቃቱ በተፈፀመባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሆን ተብሎ የህይወት ዋስትና እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ ችግሩ በነዚህ አካባቢዎች ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በመላው ኦሮሚያ የሚኖሩ ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ አማሮችና ኦርቶዶክስ አማኞችን ለከፍተኛ የኅልውና ስጋትና ሥነ-ልቡናዊ ጉዳት ዳርጓቸዋል፡፡
ለ. የጥፋቱ ተዋንያን፦
በሁሉም አካባቢዎች ጥቃቱን በተቀናጀ ሁኔታ በመምራት፣ በማስተባበርና በመፈፀም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡ በተለይ በኦሮሞ ፅንፈኛ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ሳይቀር ‹‹ቄሮ›› በሚል ስም የተደራጁ ወጣቶች ዋነኛ የጥቃት ኃይሎች ነበሩ፡፡
እነዚህ ቡድኖች ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው አቅራቢያ ከተማ ወይም ከገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ እየተሰማሩ የሚያጠቁ ፣ በከተማው የሚገኙ ዒላማ የተደረጉ ሰዎችን ቤቶችና ንብረቶችን ዝርዝር የያዙ ጠቋሚዎች በቅንጅት የሚሰሩበት ነው፡፡ ለንብረቶች ማቃጠያ ቤንዚንና መሰል ግብአቶችንም የሚያቀርቡ ነበሩበት፡፡
በተለያዩ ደረጃ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር አመራሮችና አባላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጥቃቱ ከመሳተፋቸውም በላይ ጭፍጨፋውን ለማስቆም ፍላጎት አጥተው ቆመው መመልከታቸውንም ከፍጅቱ የተረፉ እማኞች አስረድተዋል፡፡ የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት አመራሮችም እንደ ሻሸመኔና አርሲ ነገሌ ባሉ አካባቢዎች ለቀረበላቸው የድረሱልን ጥያቄ ‹‹ከበላይ ትዕዛዝ አልተሰጠንም›› በሚል ለእርዳታ አልተገኙም፡፡
የዘር ፍጅቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌዴራሉ መንግስት ወንጀሉን በስሙ በመጥራት ወንጀለኞችን ለሕግ ከማቅረብ ይልቅ ድርጊቱን ተራ ግጭት በማስመል ወደ ማስተባበል ገብተዋል፡፡ ከዘር ፍጅቱ የተረፉ ተጠቂ ወገኖችንም በተገቢው ሁኔታ በማቋቋም ረገድ ዳተኝነት ይስተዋላል፡፡
1.2. የአብን አቋም፦
በአጠቃላይ አብን በጥናቱ ባረጋገጠው መሰረት በኦሮሚያ ክልል የተደረገው የዘር ማጥፋት ተገቢውን ትኩረት ያለማግኘቱና ችግሩን በአጭር ጊዜም ይሁን በዘለቄታ ለመፍታት የሚታየው ዳተኝነት ፓርቲያችንን ክፉኛ ያሳስበዋል፡፡ ስለሆነም፦
ሀ) የተፈፀመው ወንጀል የዘር ማጥፋት መሆኑ ታምኖበት በስሙ እንዲጠራና ለተፈፀመው ወንጀልም ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠየቅ፤
ለ) መንግሥት የተፈፀመውን የዘር ፍጅት የሚያጣራና የሚመረምር ልዩ የምርመራ ኮሚሽንና አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት እንዲያቋቁምና ወንጀለኞች የሚዳኙበት ልዩ ችሎት እንዲሰይም፤
ሐ) መንግሥት በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ወንጀል የሚዘክር ቋሚ መታሰቢያ እንዲያቆም፤
መ) ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት በክልሉ በሚኖሩ የተለያዩ ማህበረሰቦችና ህዝቦች መካከል የእርቅና የመግባባት ስራዎች እንዲጀመሩ ፤
ሠ) የኦሮሚያ ክልልም በክልሉ ለሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ማህበረሰቦችና ህዝቦች ሰብአዊና ህገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው የሚከበሩበት ዋስትና እንዲሰጥ ፤
ረ) መንግሥት የዘር ፍጅቱን በመዘገባቸው ምክንያት ያሰራቸውን የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቅ አብን ይጠይቃል፡፡
2. በአዲስ አበባ የሚፈፀሙ ወንጀሎችና ብክነቶችን በተመለከተ፦
ፓርቲያችን አብን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፌዴራል መንግስቱ በከተማዋ ውስጥ የሚፈፅሙትን ወንጀሎች ፣ ሙስናና ብክነቶች የሚመረምር ቡድን በማቋቋም ሰፊ ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጥናት የተገኘ መረጃን መሰረት በማድረግ በከተማዋ ከፍተኛ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣ ተቋማትን በአንድ ብሔር ተወላጆች የመሙላት፣ ሕገ-ወጥ የመታወቂያ እደላና በርካታ ተያያዥ ወንጀሎች እንደተፈፀሙ አረጋግጧል፡፡ ይህም በተለይ ከሰኔ 2011 ወዲህ እጅግ የተባባሰ እንደነበር ተገንዝቧል፡፡
2.1. ሕገ-ወጥ ወረራ፣ ሰፈራና ማፈናቀል
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአንጡራ ሃብታቸው ያቆሙት ጎጇቸውና ድርጅቶቻቸው ያለርህራሄና ያለሕግ አግባብ የሚፈርሱባትና ዜጎች ሜዳ ላይ የሚወረወሩበት፤ ከፊሎች ደግሞ በዘር፣ በፖለቲካ ወገንተኝነትና በጥቅም ትስስር በገፍ መሬት የሚቸራቸው፤ የከተማዋ ነዋሪ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ የገነባው የጋራ መኖሪያ ቤት በልዩ መብት የሚታደላቸው ከተማ ሆናለች፡፡
አብን በከተማዋ የሚፈፅሙትን ሕገወጥነቶች ከማውገዝና በተለያዩ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ከማጋለጥ ባሻገር አቅም በፈቀደ መጠን የሰብአዊ ርዳታዎችን በማቅረብ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን ለመታደግ ጥረት አድርጓል፡፡ መላው ሕዝባችን በተለይም ለህዝብና ለአገር ጥቅሞች ፣ መብቶችና ፍላጎቶች ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ከንቅናቄያችን አገርን የማዳን ታሪካዊ ጥሪ ጎን እንዲቆሙ ወትውተናል፡፡
ከዚህም ባለፈ ንቅናቄያችን ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ በማጥናት ለአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ አቤት ብሏል፡፡ ታኅሣሥ 2 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተመንግስት በመገኘት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጋር እስከመወያየት ደርሷል፡፡ በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮች መኖራቸውን በማመን አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚበጅላቸው ቃል ቢገቡም አንዳችም ሳይደረግ አሁን ካለንበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል፡፡
ሰለዚህም አብን ይህ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በአስቸኳይ መፍትሄ ካላገኘ ፅኑ ብሔራዊ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ፦
ሀ) አዲስ አበባ ላይ የተፈፀመውን ሁሉንአቀፍ ወረራ በተመለከተ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያካተተ አንድ አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም፤
ለ) ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረውን የመሬት አስተዳደርና ማስተላለፍ፣ የመታወቂያ አወጣጥ፣ የቅጥርና ዝውውር እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲያጣራ/ኦዲት እንዲደረግ፤
ሐ) በኦዲት ግኝቱ በሚመጣው መሰረት ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ሁሉም አካላት ለፍትኅ እንዲቀርቡ፤
መ) በኦዲት ግኝቱ ለተለዩ ጉድለቶች አጣሪ ኮሚቴው በሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ መሰረት የማስተካከያ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ፤ እንዲሁም
ሠ) ምርጫ ተካሂዶ ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ የከተማ አስተዳደር ምክርቤትና ካቢኔ እስኪዋቀር ድረስ አሁን ያለው የሽግግር አስተዳደር ዘላቂ ውጤት ሊኖራቸው ከሚችሉ ውሳኔዎች እንዲታቀብ፤ አብን ጥሪውን ያቀርባል፡፡
2.2. ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ፦
ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤትና በከተማ አስተዳደሩም በኩል የሚሰሩ ዋና ዋና 15 ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሁኔታ በንቃት በመከታተል ስለፕሮጀክቶቹ ዝርዝር መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል፡፡
በዚህም መሰረት በጀታቸው/ወጪያቸው የታወቁ ፕሮጀክቶች የገንዘብ መጠን በአጠቃላይ 5.737 ቢሊዮን ዶላር (ወቅታዊ ምንዛሪው ከ212 ቢሊዮን ብር በላይ) እና ተጨማሪ 59.2 ቢሊዮን ብር በአንድ ላይ ወደ 271 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ እንደሆነ ተረድቷል፡፡ በጀታቸው ካልታወቁ ጋር ሲደመር ከዚህ ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
አዲስ አበባ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ እንድትሆን የሚደረገውን መንግስታዊ እንቅስቃሴ በመርኅ ደረጃ አብን ይደግፋል፡፡
ይሁንና የሜጋ ፕሮጀክቶቹ እጅግ የተጋነነ ወጭ የሚወጡባቸው በመሆናቸው (White Elephant Projects)፤ ይኸው ከፍተኛ በጀት አገራችን በብድርና እርዳታ የምታገኘው በመሆኑ፤ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር የቅደም ተከተል ችግር ያለባቸው መሆናቸው ፤ ከአዋጭነት፣ ባለድርሻዎችን ከማሳተፍ፣ ከዲዛይንና ግንባታ አካሄድ፣ ከብክነትና ሙስናን ከማስቀረት፣ በግልጽ ጨረታ የግንባታ ኮንትራክተሮችን ከመለየት እንዲሁም በየጊዜው ስለፕሮጀክቶቹ ለሕዝብ ግልጽ መረጃ ከመስጠት አንፃር ክፍተቶች ያሉባቸው መሆናቸውን አብን ያምናል፡፡
መንግስት ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ግልጽነት ባልተሞላበትና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች ባላስቀመጠ መልኩ ማዋሉ ፓርቲያችንን ክፉኛ ያሳስበዋል፡፡ ስለሆነም፦
ሀ) መንግስት ስለፕሮጀክቶቹ ለህዝብ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጥ፤
ለ) በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአገራችን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተደቆሰ በመሆኑ ቀውሱ አገርን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ማኅበራዊ ቀውስ ከማደጉ በፊት አስፈላጊ የኢኮኖሚ ድጋፍ ማእቀፎችን ቀርፆ ወደ ሥራ እንዲገባ፤
ሐ) የተጋነኑና አንገብጋቢ ያልሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠፍ በጀቱን የነፍስ አድን ርዳታ ለሚፈልጉ ወደ 18 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እንዲያውለው፤
መ) በአገራችን ያለው የሥራ አጥነት በአስከፊ ሁኔታ ላይ መገኘቱን በማጤን መንግስት ጊዜውንና አቅሙን ለወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያውል አብን ጥሪውን ያቀርባል፡፡
3. ብሔራዊ ውይይትና መግባባትን በተመለከተ፦
አብን የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ በምርጫ ብቻ እልባት ያገኛል የሚል አቋም የለውም፡፡ ስለዚህም ከምርጫ በፊት እንደ አገር መደማመጥ፣ መከባበርና መተማመን እንዲቻልና አሁን የተፈጠረው የሽግግር ጊዜም እንዳለፉት ዘመናት እድሎች እንዳይከሽፍ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የሰለጠነ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር እንዲዘጋጅ፤ ለዚህም ግልጽ ማእቀፍ እንዲኖርና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የብሔራዊ ውይይት መድረክ እንዲከፈት ወትውቷል፡፡
መንግሥት ለእውነተኛ የፖለቲካ ድርድርና ብሄራዊ መግባባት ዳተኝነት በማሳየቱ ምክንያት ፅንፈኛ ኃይሎች አገር አፍራሽ ድርጊታቸውን በማናለብኝነት እንዲቀጥሉ እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ትሕነግ የሚዘጋጅበት ሕገ-ወጥ ምርጫ በወረራ በተያዙ የአማራ መሬቶች በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ የሚኖረው ህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ፅኑ አፈናና ግፍ መንግሥት እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት ዘግይቶም ቢሆን የወሰነውን ውሳኔ የፌዴራል መንግሥቱ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርግና ትህነግ በህገወጥ ምርጫ በወልቃይትና ራያ ህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ሰብአዊ ቀውስ እንዲያስቆም አብን ጥሪ ያቀርባል፡፡
በተጨማሪም ፡-
ሀ) አገርን ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የማይተካ ሚና እንዳላቸው በማመን መላው የፖለቲካ ኃይሎች የአገራችን አደገኛ ወቅታዊ ሁኔታ ባጤነ መልኩ በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ፤
ለ) መንግስት በውል የታወቀና የታቀደ ሁሉንአቀፍ ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር የማስተባበርና የማመቻቸት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤
ሐ) ሁሉም ዜጎች በተለይም ሲቪክ አደረጃጀቶች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ምኁራን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ባለኃብቶች ለሚደረገው ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር ውጤታማነት የየድርሻቸውን አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው፤
መ) የዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡ የሁሉንአቀፍ ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር ሂደት እንዲደግፍና መንግስት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ጫና እንዲፈጥር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ታሪካዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
‹‹አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!››
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)፤
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ!
ጳጉሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም