Connect with us

የአብን አስቸኳይ የህልውና ማረጋገጫ ህዝባዊ ጥሪ!!

የአብን አስቸኳይ የህልውና ማረጋገጫ ህዝባዊ ጥሪ!!
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ

ነፃ ሃሳብ

የአብን አስቸኳይ የህልውና ማረጋገጫ ህዝባዊ ጥሪ!!

የአብን አስቸኳይ የህልውና ማረጋገጫ ህዝባዊ ጥሪ!!

ለመላው የአማራ ህዝብ ፣

ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች ፣

ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣

መስከረም 7፣ ቀን 2014 ዓ.ም

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አስቸኳይ የህልውና ማረጋገጫ ህዝባዊ ጥሪ፣

የአማራና የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላት የሆነው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ትህነግ) ከሐምሌ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የከፈተብንን መጠነ ሰፊ ወረራ ለመመከትና የሀገራችንንና የህዝባችንን ህልውና ለመታደግ መላው የአማራ ህዝብ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን እየተፋለመ ይገኛል፡፡

አሸባሪው የትህነግ ሠራዊት በዕብሪት በለኮሰው የተስፋፊነት ጦርነት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ፣ በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በዋግህምራና በአፋር በህዝባችን ላይ በህይወት ፣ በአካልና በንብረት እጅግ አሰቃቂ የሆነ ግፍና ጉዳት አድርሷል፡፡

ዛሬም በኃይል በተቆጣጠራቸው  አካባቢዎች ግልፅ የዘር ማጥፋት፣ የአስገድዶ መድፈር ፣ የዝርፊያና የጅምላ ውድመት እያደረሰ ይገኛል፡፡

የአማራ ህዝብ የክልሉ መንግስት ሐምሌ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ያወጀውን የህልውና ዘመቻ የክተት ጥሪ ተከትሎ ባደረገው ሁለገብ ፍልሚያ የጠላት ጦር እጅግ ከፍተኛ የሠራዊትና የቁስ ኪሳራ እንዲደርስበት በማድረግ ግስጋሴውን ለመግታት ችሏል፡፡ በዚህ  ህዝባዊ ተጋድሎው  የትህነግን ህዝባችን በሀይል አንበርክኮ  ሀገር ለማፍረስ የነበረውን ህልም እስከ ወዲያኛው አክሽፎበታል፡፡

ይሁን እንጂ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ኃይሎች በጠላት ላይ ያገኙትን ወታደራዊ ብልጫ በማጠናከር አስተማማኝ ወደ ሆነ  ድል ለመለወጥ በመንግሥት በኩል የታየው ከልክ ያለፈ ዳተኝነት እንዲሁም የአመራር ክፍተት በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ከመሆኑም በላይ የመከዳት ስሜት ፈጥሮበት ይገኛል፡፡

የጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም የትህነግ የክህደት ጥቃትን ተከትሎ ለስምንት ወራት ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ዛሬም ወራሪው ሀይል ዳግም እንዲያንሰራራ እድል ማግኘቱን አስተውለናል። በዚህ ረገድ በወገን ሀይል በኩል ባለው አሰላለፍና ስልት ረገድ የተሻሻለ ነገር ባለመታየቱ ፣ ተስፋ ቆርጦ የነበረው ወራሪ ጦር የልብ ልብ አግኝቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በተለይ በደቡብና በሰሜን ወሎ ግንባሮች የሚስተዋሉ የአመራር ክፍተቶችንና ደካማ ጎኖችን በመጠቀም ደሴና ከምቦልቻን ጨምሮ አካባቢውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

የተከበርከው የአማራ ህዝብ ሆይ!

ግንባር ቀደም የወረራው ገፈት ቀማሽ የሆንከው አንተ ነህ ፤ ጦርነቱም በዋነኝነት የራስህ መሆኑን ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብህም፡፡ እስካሁንም ጉዳዩ በሀገራዊ ማዕቀፍ ተይዟል በሚል ማናቸውንም እገዛ ስትጠብቅ ቆይተሀል፡፡ ከእንግዲህ ወገኖችህ በአረመኔው የትህነግ ጦር ለጅምላ ሞትና ስቃይ ተዳርገው ፣ ሚሊዮኖች በስደት ለረሃብና እርዛት ተጋልጠው ባለበት ሁኔታ ተጨማሪ መዘናጋት ካሳየህ  ውርደቱ ለልጅና ለልጅ ልጆችህ የሚተርፍ ይሆናል፡፡

ስለሆነም አማራ ነኝ የምትል ሁሉ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ቆርጠህ ተነሳ፡፡ መዋጋት የምትችል ሁሉ ወደ ጦር ግንባር ዘምተህ ወራሪውን የጠላት ሀይል በመተናነቅ ታላቅ የነፃነት ታሪክ አካል የመሆን አደራ ወድቆብሀል፡፡ በተለያዩ አሳማኝ ምክንያቶች ውጊያ መግባት የማትችል ደግሞ በደጀንነት ሀብትህን ፣ ንብረትህን ፣ ጉልበትህን ፣ እውቀትህን ለወራሪው የጠላት ሀይል አሳልፈህ የዘረፋ ግብአት ከማድረግህ በፊት ለወገንህ መድህንነት ያለስስት አውለው፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በተለይ በአሁኑ ሰዓት በወሎ በኩል አጠቃላይ ለዘረፋ፣ ለውድመትና ለጭፍጨፋ ያሰፈሰፈውን የጠላት ሀይል ቅስም ለመስበር የሚያስችል ምሉዕ የመከላከል ስምሪት መወሰድ አለበት በሚል ህዝባችን ማናቸውንም የአዘቦት ሥራና የትምህርት እንቅስቃሴዎች ከወድሁ በማቆም በሙሉ ኃይሉ ወረራውን ለመቀልበስ እንዲረባረብ ጥሪ ያደርጋል፡፡

አብን በሌሎቹም የአማራ አካባቢዎች ወራሪው ሀይል ጥቃት በከፈተባቸው ግንባሮች ህዝባችን ለአፍታ ሳይዘናጋ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከአማራ ኃይሎች ጋር በንቃት ተባብሮ በመቆም በወራሪው ላይ የማያዳግም ርምጃ እንዲወስድና አካባቢውን ከአሸባሪው ርዝራዦች ፍፁም እንዲያፀዳ ጥሪ ያደርጋል፡፡

መንግስት በፍላጎት፣ በውሳኔ ሰጭነት፣ በትጥቅና ስንቅ አቅርቦት እንዲሁም በማስተባበር ረገድ የታዩበትን ጉልህ ክፍተቶች በማረም፣ በማስተካከል፣ በብቃትና በቁርጠኝነት በመሰለፍ፣ ህዝብንና ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ የሚያስችሉ ጠንካራና ፈጣን ርምጃዎችን ወስዶ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲያረጋግጥ በአፅንኦት እናሳስባለን።

በዚህ ረገድ በአንድ በኩል ያለው ነባራዊ ሁኔታ፣ በተለይም እስካሁን በቀጠለው ወረራ ምክንያት የደረሱት በርካታ ቁሳዊና ሰብዓዊ ውድመቶች እንዲሁም የተፈጠረውን ሰፊ ማህበራዊ ምስቅልቅል፣ በሌላ በኩል ወረራውን ለመከላከልና ለመቀልበስ የተደረጉ መንግስታዊ ጥረቶችን ሚዛን ላይ በማስቀመጥ የሚፈጥሩትን ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድምታዎች ማስተባበል አዳጋች እንደሚሆን ለመጠቆም እንወዳለን።

በጦርነት ውስጥ ያሉ ታሳቢዎች፣ እቅዶችና የዘመቻ ስምሪቶች ባብዛኛው በወታደራዊ ምስጢርነት በጥብቅ ተይዘው የሚተገበሩ ጉዳዬች መሆናቸው አይሳትም። ከዚህ አኳያ በዘመቻ አመራርና በግንባር አወሳሰን ረገድ የስትራቴጂ ቅደም ተከተል እንደሚኖር ግምት ይወሰዳል። ነገር ግን በሰፊ ቀጠናዎች የሚኖረውን ትልቅ ማህበረሰብ ለተከታታይና ላልተቋረጠ ወረራ ተጋላጭ የሚያደርግ እቅድና አመራር ማህበረሰብን ከስሌት ውጭ ያደረገ በመሆኑ ስሁት ከመሆን አያልፍም።

የአማራ ክልል መንግሥት የተጀመረውን የዘመቻ ህልውና ሂደት ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ በማጠናከር ፣ አሸባሪውን የትህነግ ሠራዊት በአጭር ጊዜ ከህዝባችን ላይ ለማስወገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ይጠይቃል፡፡

የፌዴራል መንግሥቱም ከእንግዲህ የህዝብ ሰቆቃ ሞልቶ እንደፈሰሰ በውል እንዲገነዘብ ፣ ከእንግዲህ ህዝብን ለጥቃት፣ ሀገርን ለውርደትና ለመበታተን የሚዳርግ ማናቸውንም አይነት አካሄድ በአስቸኳይ በማረም የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲፈፅም ንቅናቄያችን ይጠይቃል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ትህነግን ለማስወገድ የሚደረገውን ማናቸውም ሀገራዊና ክልላዊ ጥረት በሙሉ ልብ ያለማመንታት እንደሚደግፍ እየገለፀ ፣ በዚህ የመጨረሻው ምሽግ ፍልሚያ ላይ መላው የድርጅቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ደጋፊዎች በግንባር ቀደምትነት እንዲሰለፉ ታሪካዊና ትውልዳዊ ጥሪ ያስተላልፋል፡፡ አፈፃፀሙን በተመለከተ ከወድሁ የእቅድና የተግባራዊ ስምሪት መመሪያዎችን የሚያስተላልፍ ይሆናል።

ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር !

መስከረም 7፣ ቀን 2014 ዓ.ም

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top