Connect with us

ገዳ ስርዓትን እንተዋወቅ

ገዳ ስርዓትን እንተዋወቅ
Photo: Social Media

ባህልና ታሪክ

ገዳ ስርዓትን እንተዋወቅ

ገዳ ስርዓትን እንተዋወቅ
መተዋወቅ ያቀራርባል!
(ታዬ ደንደአ)

ቦረና ጉሚ ላይ ነዉ! ጉሚ ማለት ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ነዉ! በስብሰባዉ ላይ ትላልቅ ዉሳኔዎች ይተላለፋሉ! ህጎች ሊሻሻሉ ወይም ሊቀየሩ ይችላሉ። የገዳ ባለስልጣናትም ይገመገማሉ! በገዳ ስርዓት ጉሚ ትልቁ የፖለቲካ ስልጣን አካል ነዉ። ስልጣን የህዝብ መሆኑን በተጨባጭ ያሳያል።

ስለገዳ ብዙ መናገር ይቻላል። ለአሁኑ አምስት ነጥቦችን ብቻ ማንሳቱ ይበቃል። አንደኛዉ ዴሞክራሲያዊነቱ ነዉ። ይህ በሶስት ምሰሶዎች ላይ ይቆማል። በአንድ በኩል ሙሉ የንግግር ነፃነት ይሰጣል። በገዳ የዜጎች የመናገር መብት አይከለከልም። ሁሉም ድምፆች ይደመጣሉ። ህግን በመተላለፍ የሌሎችን መብት የሚነኩ ደግሞ ኃላፊነት ይወስዳሉ። በሌላ በኩል ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለየ ጥበቃ ያደርጋል። አንድ ህፃን ተወልዶ ስምንት ዓመት እስክሞለዉ መብት ብቻ ይኖሯል። ሁሉም እንክብካቤ ይደረግለታል። ምንም ግዴታ አይጣልበትም። ቢያጠፋም አይጠየቅም። ከሰማንያ ዓመት በላይ የሆኑ አረጋዊያን ደግሞ የጡረታ መብት አላቸዉ! ሌላዉ ስልጣን የተገደበና የህዝብ መሆኑ ነዉ። አባ ገዳ በህዝብ ይሁንታ ስልጣን ይይዛል። ስልጣን ላይ ለስምንት ዓመት ብቻ ይቆያል። በመሃል ኃላፊነቱን ካልተወጣ ህዝብ ሊያነሳዉ ይችላል።

ሁለተኛዉ የኢኮኖሚ ስርዓቱን ይመለከታል። ገዳ ቅይጥ የኢኮኖሚ ስርዓትን ይከተላል። ዉሃ እና ግጦሽ የጋራ ናቸዉ። ቤት እና የቤት እንስሳት ደግሞ የጋራ ናቸዉ። ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በዉድድር እና በትብብር መሀል ሚዛኑን ጠብቆ ይካሄዳል። ዜጎች ያለገደብ ሀብት የማፍራት ሙሉ ነፃነት አላቸዉ። ተወዳድሮ ማሸነፍ ይቻላል። ነገር ግን ሀብቱ የግላቸዉ ብቻ አይሆንም። የቡሳ-ጎኖፋ ወይም የህርጳ ህግ አለ። በዚህ ህግ መሠረት ሀብት ያለዉ ሁሉ በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋ ንብረት የጠፋበትን ወገን የመርዳት ግዴታ አለዉ። በስንፍናዉ የተቸገረ መብት የለዉ። በአንፃሩ ደግሞ የአንድ ሰዉ ከብቶች ቢጠፉ የመፈለግና ዉሀ ቢጠማቸዉ የማጠጣት ግዴታ የሁሉም ዜጋ ነዉ። ያን ያላደረገ ይጠየቃል።

ሦስተኛዉ ሠላማዊነቱ ነዉ። በመሠረቱ ገዳ በሠላም ለሠላም የሆነ ሠላማዊ ስርዓት ነዉ ማለት ይቻላል። አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩ ስራዎች በመግባባት ይከወናሉ። አለመግባባት ከተፈጠረ ግጭት ሳይፈጠር ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ ይደረጋል። በድንገት ግጭት ተፈጥሮ የሰዉ ህይወት ካለፈ ደግሞ ተከታታይ መገዳደል እንዳይኖር በጉማ ህግ እርቅ ወርዶ በሟች እና በገዳይ ዘመዶች መሀከል ወዳጅነት ይፈጠራል።

አራተኛዉ ሰበአዊነትን ማዕከል ማድረጉ ነዉ። ገዳ ለሰበአዊነት እና ለወንድማማችነት ትልቅ ስፍራ አለዉ። ጉዲፈቻ በዚህ ላይ የተመሠረተ ነዉ። ልጅ ያለዉ መርቆ ለሌለዉ ይሰጣል። ወድቆ የተገኘ ህፃን ኢልመ-ምጢ ተብሎ ልጅ ይሆናል። በጦርነት የተማረከ ህፃንም ኢልመ-ቦጁ ተብሎ ከአብረክ ልጆች ጋር እኩል መብት ይጋራል። ገዳ ለግለሰብም ሆነ ለቡድን በችግር ጊዜ ጥገኝነት ይሰጣል። ለፈለገዉ ደግሞ በሞጋሳ ህግ መሠረት ሙሉ ዜግነትን ያጎናፅፋል። አሁን ላይ ጥቂት ግሪሳዎች የሚያሳዩት ኢ-ሰበአዊ ባህሪ በምንም ሂሳብ የኦሮሞን ማንነት አይወክልም!

አምስተኛዉ በህግ የበላይነት ላይ መመስረቱ ነዉ። በገዳ ሁሉም ከህግ በታች ነዉ። መብቱ የተደፈረ ያለልዩነት ይካሳል። ህግን ተላልፎ ጉዳት ያደረሰ ደግሞ ተጠያቂነት ይወስዳል። እስከ አባባሉም “ኦሮሞ አስሬ መክሮ፥ አስሬ ታግሶ፥ አስሬ ደብቆ፥ የጉልበተኞችን እጅ ይጠመዝዛል” ይባላል።

ሌላዉ ጉዳይ ሌላ ጊዜ ይታያል። ከምንም በላይ ግን ገዳ ብቻ ሳይሆን ቅኔዉ እና ምሳሌዉም የጋራ ሀብቶቻችን መሆናቸዉን ማሰቡ ጥሩ ይሆናል።

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top