Connect with us

ጠቅላይ ሚንስትሩ ምን እየሠሩ ነው?

ጠቅላይ ሚንስትሩ ምን እየሠሩ ነው?
Photo: Social Media

ትንታኔ

ጠቅላይ ሚንስትሩ ምን እየሠሩ ነው?

ጠቅላይ ሚንስትሩ ምን እየሠሩ ነው?
– ሰሎሞን ሹምዬ

ሰሞኑን በቴሌቪዥን ያየነው ‘አዲስን የማስዋብ ፕሮጀክት’ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ጠቅላይ ሚንስትሩም በተለመደው የብልጽግና እና የመደመር ዲስኩራቸው የተዋጣለት ቱሪስት ጋይድ ሆነው ገድላቸውን ተርከውልናል። ያንን ተከትሎም በማህበራዊ ሚዲያ ከ’የተባረከ መሪ’ እስከ ‘ሺህ ዓመት ንገስ’ ምርቃትና ውዳሴ ‘ከበለጸጉና ከተደመሩ’ ወይም ‘ብልጽግናን በተስፋ ከጠገቡ’ ደጋፊዎቻቸው ጎርፎላቸዋል።

ተቺዎቻቸው ወይም በእርሳቸውና በፕሮጀክቱ ላይ ጥያቄ ያነሱ በሙሉ ጥሩ ነገር ማየት የማይወዱ ‘ምቀኞች’፤ እንዲያውም የኢትዮጵያ ‘ጠላቶች’ ሆነው ተፈርጀዋል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በየትኛውም ወገን የተባለውን መልሶ ማስተጋባት ሳይሆን አንዳንድ ጉዳዮችን እያነሱ መንግስትም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለተሻለ አሠራር እንዲተጉ ማስገንዘብ ነው።

ቤተመንግስቱን በተመለከተ

ታላቁ የምኒልክና የኢዮቤልዩ ቤተመንግስታት ፀድተውና ታድሰው ለጉብኝትና መዝናኛ ክፍት እንደሚሆኑ መስማት ያስደስታል። በነገስታቱ የአኗኗር ዘዬ መነሻም ቢሆን ኢትዮጵያ እንደ አገር የነበራትን ታሪካዊ ከፍታ፤ በተለይ ገና እንደ አዲስ ካልተፈጠረች ብሎ በሃሰት ትርክት ግብ ግብ እየገጠመ ላለ የብሔር ፖለቲከኛ ብዙ ሊያስተምር ይችላል።

ይሁን እንጂ በተለይ የታላቁን ቤተመንግስት ስያሜ ‘አንድነት ፓርክ’ ወደሚል መቀየራቸውና በይዘትም ቀድሞ ያልነበረ ለውጥ አድርገው ከዘመኑ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አንጻር ለማስኬድ ያደረጉት ጥረት ስህተት ነው። ዛሬ ላይ ቆሞ በዘመናቸው የሠሩትን የሚያደንቅና የሚያንኳስስ ቢኖርም ቤተ መንግስቱ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መሆኑን መካድ አይቻልም። /በደርግም ሆነ በኢህአዲግ የመሪዎች መኖሪያ ሆኖ ማገልገሉ ምናልባት ሌላ መኖሪያና ጽሕፈት ቤት ለመገንባት ተቸግረው ነው ካልተባለ በቀር ከታሪካዊ ቅርስ አጠባበቅ አንጻር ተገቢ አልነበረም/። ቤተመንግስቱን ከነሙሉ ክብርና ማእረጉ በነበረበት ሁኔታ አጽድቶና በጥንቃቄ አድሶ ማቆየት ለምኒሊክ ወቃሾችም ሆነ አወዳሾች የታሪክ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል።

– እንደተባለውም ለቱሪስት መስሕብ ይሆናል። ከዚህ ውጪ የቱንም ያህል ቢያምር በቤተመንግስቱ ተጨማሪ ግንባታ ማድረግና በንጉሱ ስነልቦና ወይም በዚያ ዘመን ቦታ ያልነበራቸው ቁሳቁስና እንስሳት ማጎሪያ ማድረግ ታሪካዊ ዳራውን ለማጥፋት አለዚያም የቅርስነት ዋጋውን ለማሳነስ ካልሆነ በቀር ፋይዳ የለውም።

-ልክም አይደለም። (ሌላው ቢቀር የዩኔስኮን የቅርስ አጠባበቅ መመሪያ ማንበብ ምን እያልኩ እንደሆነ ለመረዳት ይጠቅማል) የአፄ ኃይለ ስላሴ (የእዮቤልዩ) ቤተመንግስትንም በዚያው ልክ ማሰብ ነው።

አዲስ አበባን እና ሌሎች አካባቢዎችን ማስዋብ ምን ክፋት አለው?

ምንም። ማስዋብና ማሳመር ምንም ክፋት የለውም። የራሱን የሥራ ሃላፊነት በሚገባ ባልተወጣና ለዜጎች ጥያቄና ችግሮች አጥጋቢ ምላሽ ባልሰጠ መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆን ግን ክፋት ብቻ ሳይሆን ጉዳትም አለው። ጠቅላይ ሚንስትሩኮ አገር የሚመሩት ዜጎች ከራሳቸው አልፈው አገራቸውን እንዲያበለጽጉ ምቹ የሆነና የሚያስችል ከባቢ ለመፍጠር እንጂ ሁሉን ‘እኔ ካልነካሁት አይሳካም’ በሚል አባዜ ተጠምደው ጧትና ማታ በፎቶና በቪዲዮ የተደገፈ ትናንሽ ገድላቸውን እንዲተርኩ አይደለም።

ምቹና የሚያስችል ከባቢ ለመፍጠር ደግሞ የዜጎችን ችግርና ፍላጎት አዳምጦ ፖሊሲ መቅረጽ፤ የማስፈፀሚያ ስትራተጂ ማዘጋጀትና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ ቢሮክራሲን መዘርጋት የመንግስት ዋነኛ ተግባራት ናቸው። በአገራችን ሁኔታ የተፈጥሯዊ ሞኖፖሊ ባህሪ ያላቸው እንደ መንገድ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ስልክና የባቡር አገልግሎት ያሉ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችም ለጊዜው በግሉ ዘርፍ የማይሸፈኑ የመንግስት የቤት ሥራዎች ናቸው። – ትምሕርትና የጤና አገልግሎትም ሳይረሳ። የዜጎችን ደሕንነትና ሰላም መጠበቅ ደግሞ ከሁሉም ቀዳሚ የሆነው መንግስታዊ ኃላፊነት ነው። አንድ መሪ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡበትና ወደየትኛውም ክልል ያለምንም ስጋት መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ሰላምና መረጋጋት ሳያሰፍን፤ ወርቅ በጆንያ ቢያድል እንኳ ‘ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ ነው’ ለማለት ያስቸግራል።

በዚህ ላይ ሰላምና መረጋጋት ቢሰፍን እንኳ ፓርክ፣ ሲኒማና ሌሎች የመዝናኛ ኢንቨስትመንቶች ላይ መሠማራት የመንግስት ድርሻ አይደለም። የከተማም ሆነ የገጠር ፅዳትና ውበት መጠበቅም መሠረታዊ የማዘጋጃ ቤት ተግባር እንጂ ‘ሜጋ ፕሮጀክት’ ተብሎ የፕሮፓጋንዳ ከበሮ የሚደለቅበት አይደለም። ከሁሉም በላይ ምጸት የሚሆነው ደግሞ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ኃላፊነት ከማይመጥኑ ትናንሽ ሥራዎች ጋር ፎቶ እየተነሱና ቪዲዮ እየተቀረጹ ሁሉም ሰው እንደርሳቸው እንዲሠራ የሚያስተላልፉት መልእክት ነው። ዜጎች በሚፈልጉትና በሚችሉት ልክ ሠርተው ራሳቸውንና አገራቸውን ለመጥቀም የሚችሉበት ሁኔታ ሳይፈጥሩ፤ እንዴት ነው ሁሉም ሰው ‘እንደርሳቸው’ እንዲሠራ የሚጠብቁት? መጀመሪያ ራሳቸው ኃላፊነታቸውን በሚገባ መቼ ተወጡ? – ከ14 ሚሊዮን በላይ ሥራ አጥ ያለባት አገር መሆኗን ልብ ይሏል።

እንዲሁም ሥራ ላይ ቢኖረውም ከአቅም በታች እየሠራ ያለውም (underemployed) ከጠቀስኩት ቁጥር እንደማያንስ ይገመታል። ይኼ እንግዲህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ተጽእኖ ከግምት ሳናስገባ ነው። እስከዛሬ ለተከማቸው የሥራ-አጥነት ችግር በሙሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በግል ተጠያቂ ባናደርግም፤ እርሳቸው ስሙንና መጠኑን ቀይረው የሚመሩት ፓርቲ ባለፉት ሃያ ዘጠኝ ዓመታት የነበረ በመሆኑ ግን ከተጠያቂነት አያመልጡም።

የችግኝ ተከላው ጉዳይ

ከዶክተር አብይ ‘ታላላቅ’ ፕሮጀክቶች አንዱ ሆኖ ጠዋት ማታ በመንግስት ሚዲያ የሚንቆለጳጰሰው የችግኝ ተከላ ነው። ችግኝ ተክሎ ደን የማልማት ጥቅም እና አስፈላጊነት ምንም ጥያቄ የለበትም። መንግስት በኢኮኖሚ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲው ውስጥ አካትቶ ሊተገብራቸው ከሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱም ነው። በየትኛውም ሁኔታ ችግኝ ካለመትከል፤ መትከል የሚበረታታ ተግባር ነው።

ይሁን እንጂ የችግኝ ተከላው የአፈፃፀም ስትራተጂ፤ ፕሮጀክቱን ከመንግስት ትከሻ አውርዶ የጠቅላዩ የግል ጉዳይ አስመስሎታል። እሳቸው አትክልተኛ መስለው ለመታየት የሚያደርጉት ጥረት በአንዳንድ የዋሃን ዜጎች ታታሪና ኢትዮጵያን ‘ለማበልጸግ’ የማይሆኑት እንደሌለ ተደርጎ ቢወሰድም፤ ከጊዜያዊ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ባለፈ ዘላቂ አገራዊ ፋይዳ የለውም። ይልቁንም በዘመቻ ስም የመንግስታቸውን ኃላፊነት የመወጣት ብቃት ማነስ ለመሸፈንና በሚመሩት ሕዝብ ላይ ተገቢ ያልሆነ የሞራል ግዴታ ጥለው፤ እቅዳቸው ካልተሳካ ከተጠያቂነት ለማምለጥ፤ ከተሳካም ውለታ ለማስቆጠር የሚጠቀሙበት አካሄድ ነው የሚመስለው። በነገራችን ላይ ይኽን ዓይነት አካሄድ በሌሎችም ጉዳዮች ይጠቀማሉ። የኮቪድ – 19፣ ማእድ ማጋራት፣ አዲስን የማስዋብ ፕሮጀክት፣ የሰላም ማስከበር ሂደት፣ የተፈናቃዮች ማቋቋሚያን . . . ማስታወስ ይቻላል።

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ከ14 ሚሊዮን በላይ ሥራ አጥ ባለበት አገር ጠቅላይ ማኒስትሩ ሥራ ፈትተው፤ ሥራ ላይ ያሉ ሰዎችን ሥራ በማስፈታት የችግኝ ተከላ ዘመቻ ለማድረግ የሚያስገድድ ነባራዊ ሁኔታ የለም። ችግኝ ተክሎ መንከባከብና ደን ማልማት በራሱ ለሚሊዮኖች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል ዘርፍ ነው። ‘እንዴት?’ የሚል ካለ በሰፊውና በዝርዝር ማብራራት ይቻላል። ለጊዜው ጥቂት ልበል።

ከወጪው እንጀምርና የዚህ ዓመቱን ብቻ በምሳሌ ላንሳ። የአንድ ችግኝ ዋጋ ከ12 ብር ጀምሮ እስከ መቶዎችና ሺዎች በቴሌቪዥን ሲዘገብ ሰምቻለሁ። መቶና ሺዎቹን ትተን የአንዱን አማካይ ዋጋ /ከአማካዩ በእጅጉ እንደሚያንስ ብናውቅም/ በሰላሳ ብር ብናሰላው 150 ቢሊዮን ብር ይመጣል። ጉድጓዱ ደግሞ ያለፈው ዓመት በነበረኝ መረጃ /ዘንድሮ ይጨምራል ካልሆነ የሚቀንስበት ሁኔታ የለም/ አንዱ ከሶስት እስከ አምስት ብር ዋጋ ነው የሚቆፈረው። በአማካይ አራት ብር ብንይዝለት 20 ቢሊዮን ብር ይመጣል። የችግኙና የጉድጓድ ማስቆፈሪያው ዋጋ በድምሩ 170 ቢሊዮን ብር ይሆናል። ይኼ እንግዲህ በአንዳንድ መ/ቤቶች ችግኝ ለተከሉ ሠራተኞች የተከፈለውን የውሎ አበል /እኔ የሰማሁት በሰው ሁለት መቶ ብር ነው/ እና የመጓጓዣ ወጪ ሳይጨምር ነው። በደንብ እናስላ ካልን ቢያንስ ተካዮቹ በመደበኛ ሥራቸው ላይ ሳይገኙ የተከፈላቸውን ደመወዝም ወጪው ላይ መደመር አለብን። – የፕሮሞሽን እና የስብሰባ ወጪዎችንም እንዲሁ።

ሌሎቹን አስረን (ceteris paribus እንደማለት) ስለ 170 ቢሊዮን ብሩ እንነጋገር። ይሄ ገንዘብ መንግስት የጨነቀው ጊዜ /በ2008 ዓ.ም. ይመስለኛል/ ‘ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ’ በሚል ይዞት ከነበረውና ውጤታማነቱ ከሚያጠያይቀው የ10 ቢልዮን ብር በጀት አሥራ ሰባት እጅ ይበልጣል፤ ለ10 ሚሊዮን ሥራ አጦች በነፍስ ወከፍ አስራ ሰባት ሺህ ብር ይደርሳል። ልብ አድርጉ-የአንድ ዓመቱ ብቻ ነው። ፕሮጀክቱ በአራት ዓመት ሃያ ቢልዮን ችግኝ የመትከል እንደሆነ ስለሰማን ዋጋውን ባለበት ይዘን እንኳን ብናሰላው በጀቱ 680 ቢሊዮን ብር ይሆናል። ለ10 ሚሊዮን ወጣቶችም በአራት ዓመት ውስጥ በነብስ ወከፍ 68 ሺህ ብር ይደርሳል።

በቁጥር ለመጫወት አይደለም። አዲስ አበባን ከከበቧት ተራሮች ጀምሮ በየክልሉ የተራቆተ እና ለእርሻ አገልግሎት የማይውል መሬት ተሸንሽኖ ለ10 ሚሊዮኑ ሥራ አጦች በግልና በጋራ አልምተው እንዲጠቀሙበት፤ ከዚህ በጀት ጋር /በሪቮልቪንግ ፈንድ/ ቢታደል ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። አንደኛ፣ የሥራ አጥነትን ችግር በከፍተኛ ደረጃ ይቀርፋል፤ ሁለተኛ፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ጤናማነትን ለመመለስ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፤ ሶስተኛ፣ ከማገዶ ጀምሮ ለእንጨት ሥራ ውጤቶች ግብአት በማምረት የውጭ ምንዛሪ ለማዳንና ከኤክስፖርት ገቢ ለማግኘትም ይጠቅማል። ሌሎች ተያያዥ ትሩፋቶችንም ማሰብ ይቻላል።

አሁን ባለው ሁሉን በዘመቻና በልመና ለመሥራት የሚደረግ አካሄድ ከምርጫ በፊት ድምጽ ለመግዛትና ባለራእይ መስሎ ለመሸወድ ካልሆነ በቀር፤ ዘላቂ ብልጽግናን የሚያመጣ አይደለም። መንግስታዊ ባሕሪም አይደለም። የመንግስት ዋነኛ ተግባር ዜጎች ራሳቸውንና አገራቸውን ለማሳደግ የፈለጉትንና አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ያለእንቅፋት እንዲሠሩ የሚያስችል ከባቢ መፍጠር ነው። እናም ተመጣጣኝ ታክስና ቀረጥ ሰብስቦ፤ በራሱ በጀት ስልትና ሥርአት ዘርግቶ ያቀደውን መፈጸም። ዘመቻ ሳይታሰብ የሚከሰት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ድንገተኛ አደጋን ለመቋቋም አቅም የማሰባሰቢያ መንገድ እንጂ፤ መደበኛ የመንግስት ሥራ ሊሆን አይገባም።

ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹፌር፤ አትክልተኛ፣ አስጎብኚ . . . ሆነው በአርአያነት ሊደነቁና ሊሞገሱ ከፈለጉ፤ መጀመሪያ የራሳቸውን ግዳጅ ጥንቅቅ አድርገው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ሥራቸው ደግሞ፤ በዋናነት በየደረጃው ብቁ፣ ቀልጣፋና ለዜጎች ምቹ የሆነ የሥራና የኑሮ ከባቢን የሚፈጥር ጠንካራ ካቢኔ መመሥረት፤ እንዲሁም በሚከለክል፣ በሚያደናቅፍ እና በሚያሸማቅቅ ሕግና መመሪያ የተቀፈደደውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማሕበራዊ ፖሊሲ ማሻሻል ነው። በተናገሩ ቁጥር ከአፋቸው የማይጠፋው ብልጽግና የሚመጣው ለዜጎች ያለልዩነት የተመቻቸ የሥራ ከባቢ በመፍጠር እንጂ ቆፋሪም መሪም እራሳቸው በመሆን አይደለም። አገር ማልማትና ማበልጸግም በፖለቲካ ዲስኩር ብቻ አይሰምርም። ፕሮፓጋንዳም ምሳ እና እራት ሆኖ አውሎ-አያሳድርም። የአብዛኛው ዜጋ የኑሮ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ለትናንሽ ውጤቶች መገናኛ ብዙኃንን በብዛት ተቆጣጥሮ ‘ብልጽግና ብልጽግና’ ማለት ለጊዜው ከማዘናጋት ባለፈ፤ የሚሰበከውን ብልጽግናን አያመጣም። ‘ሆድን በጎመን ቢደልሉት፤ ጉልበት በዳገት ይለግማል’።

ኢትዮጵያችን ለእኛ፤ በእኛ ለዘለዓለም ትኑር!
(ምንጭ:- ፍትሕ)

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top