በጠቅላዬ ተስፋ አልቆርጥም – እኔ
(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)
ርዕሱን ግጥም አደረኩት? “የእነጸጋዬ ገብረመድህን ቆሌ ይድፋህ!” የሚል ርግማን ከመቀበሌ በፊት ስድ ንባብ መሆኑን እናዘዛለሁ፡፡ ወደገደለው ስገባ፤ ትላንት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጥሩ እና መናኛ ዜናዎች መካከል የክቡር ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድን የሚመለከተው አንዱ ነበር፡፡ ጠቅላዬ ትላንት በዕቅድና በድንገት ሁለት የመንግስት ተቋማት ከች ብለው ጎብኝተዋቸዋል፡፡ መ/ቤቶቹ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና የገንዘብ ሚኒስቴር ናቸው፡፡ ከዜናው እንደተረዳሁት ጉብኝቱ ያተኮረው የመ/ቤቶቹ ገጽታ ግንባታ አንድ አካል የሆነው የቢሮ እድሳትና ማስዋብ ጉዳይ ነው፡፡ ስለመልካም ገጽታ፣ ስለውበት የሚጨነቅ ጠ/ሚኒስትር የሰጠን አምላክ ይመስገን!
በጠ/ሚኒስትሬ ትልቅ ተስፋ ያለኝ እኔ በፍጹም ቅንነት እጠይቃለሁ፡፡ አሁንም እጅግ ቢረፍድም የኦሮሚያ ቀውስ ተጎጂዎችና ተፈናቃዮችን አንድ ቀን በድንገት ከች ብለው ያጽናናሉ የሚለው ተስፋዬ በውስጤ አልመከነም፡፡
እጅግ ቢዘገይም ሰሞኑን የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ እርቃናቸውን ያስቀራቸውን የደጉ የአፋር ህዝብ እና የምእራብ ሸዋ ወንድሞችና እህቶቻችንን አንድ ቀን ጎራ ብለው “አይዟችሁ!” እንደሚሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሰው በእህልና በውሃ ብቻ አይኖርም፤ በተስፋም እንጂ፡፡ ያደላቸው አገራት መሪዎች እንዲህ ሕዝብ ሲቸገር፣ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲጎዳ በርረው ቦታው ለመድረስ የሚቀድማቸው የለም፡፡ መሪዎቹ በቦታው መገኘታቸው ብቻ ተጎጂዎች የከፋ ጉዳታቸውን ጭምር ያስረሱታል፡፡ መሄዳቸው የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ይስባል፡፡ የአገር ውስጥ የውጭ ረጂ ድርጅቶች ርብርብ ፈጣን ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በግሌ የማምነው እንዲህ የህዝብን ችግር ተካፍሎ ተስፋ የሚሰጥ መሪ እንዳለን ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ ባተሌ ናቸው፡፡ በስራ ተወጥረው ብዙ ነገር ሊዘነጉ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ ይህቺ ማስታወሻም እንደንቃት ደውል ትወሰድልኝ፡፡ ጠቅላዬ እጅግ ከተጣበበው ጊዜያቸው ሰውተው የፖለቲካ ቀውሱ የፈጠረውን ምስቅልቅል በአይናቸው በብረቱ የሚያዩበት ጊዜ ብዙ ሩቅ እንደማይሆን አምናለሁ፡፡
ክቡርነትዎ ደጋግመው “ኢትዮጽያ አትፈርስም” ብለዋል፡፡ ጠቅላዬ ኢትዮጵያ ሲሉ እኔ የምረዳዎት ስለጋራና ሸንተረሩን ሳይሆን ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች ማለትዎ እንደሆነ ነው፡፡ እና ወደሻሸመኔ፣ ባቱ፣ አርሲ፣ ምስራቅ ሐረርጌ…አንድ ቀን ሲመጡ ኢትዮጵያ እንዴት እንደፈረሰች በአይንዎ በብረቱ ማየት ይችላሉ፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው፣ በገዛ ቀዬአቸው፣ ወልደው በከበሩበት ቤታቸው እየተጎተቱ እንደከብት ከመታረድ፣ ከመዋረድ፣ ንብረታቸው ከመቃጠልና ከመዘረፍ እንዲሁም አስከሬናቸው መቅበር ካለመቻል በላይ የአገር መፍረስ ምን መገለጫ ሊኖረው ይችላል?
ክብርነትዎ አሁንም በእርስዎ ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡ ይኸን ክፉ የጭለማ ጊዜ በጥበብ ለመሻገር በቅንነት አቅምዎን ሁሉ እንደሚጠቀሙ፣ ብብትዎ ስር የተጠለሉ አጥፊዎችንም ጭምር ቆርጠው በመጣል ኢትዮጵያን ወደፊት እንደሚያራምዱ አሁንም አምናለሁ፡፡ ግን እንዲህ አይነት የሰው ደም የፈሰሰባቸው ቀውሶችን በዝምታ በማለፍ፣ አንዳንዴ በማሳነስ አንዳንዴ ትኩረት በመንፈግ ለመጓዝ መሞከር ቁስለኛውን ይበልጥ ከማቁሰልና በትውልድ ውስጥ ቂምና ጥላቻን ከማስቀመጥ ያለፈ ቁምነገር እንደሌለው ለእርስዎ ማስረዳት ከንቱ ድፍረት እንዳይሆንብኝ እሰጋለሁ፡፡
ክቡርነትዎ አሁንም አምናለሁ፡፡ በጣም በቅርቡ ተጎጂ ሕዝብዎን በአካል መጥተው እንደሚጎበኙ፣ እንደሚያጽናኑ አሁንም ተስፋ አደርጋለሁ፤ ክቡርነትዎ በተስፋ እጠብቃለኹ፡፡
—