Connect with us

በኦሮሚያ ለጥቃት ተጋላጭ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አሁንም የጥቃት ማስፈራሪያ

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ለጥቃት ተጋላጭ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አሁንም የጥቃት ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰባቸው ነው አለ
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

በኦሮሚያ ለጥቃት ተጋላጭ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አሁንም የጥቃት ማስፈራሪያ

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ለጥቃት ተጋላጭ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አሁንም የጥቃት ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰባቸው ነው አለ

– ተጎጂዎችን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑንም ተችቷል፣

(ሙሉ መግለጫው እነሆ)

(አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የተከሰተውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታ ላይ ፈጣን ምርመራ ማድረግ መጀመሩን በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ኮሚሽኑ ባለፉት ሁለት ሳምንታትም ከ40 በላይ ችግሩ ተከስቶባቸዋል በተባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ የምርመራ ቡድኖችን በማሰማራት ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ምስክሮችን እና የመንግስት አካላትን በማነጋገር መረጃ ለማሰባሰብ እና አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ጥረት አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ የሰበሰበውን መረጃ ከሰብዓዊ መብት መርሆዎች አንፃር በመተንተን ዝርዝር የምርመራውን ግኝቶች እና የመፍትሄ ሀሳቦች በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚያሳውቅ መሆኑን እየገለጸ በምርመራው ወቅት የታዩና በአፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ያሰባቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስጋቶችን ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በይፋ በማሳወቅ ተገቢ እርምጃ አንዲወሰድ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ይህንን መግለጫ አውጥቷል፡፡

1. አሁንም የጥቃት ስጋት ያለባቸው ነዋሪዎች በተመለከተ

የምርመራ ቡድኖች በተጓዙባቸው በአብዛኛው አካባቢዎች በአሁኑ ሰዓት የተሻለ መረጋጋት ያለ መሆኑን ለመረዳት ቢቻልም በአንዳንድ አካባቢዎች በሰዎች ህይወት፣ አካላዊ ደህንነት እና ንብረት ላይ የጥቃት ስጋት እንዳለ ኮሚሽኑ ለመገንዘብ ችሏል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ተጎጂዎች እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ቡድኖች የጥቃት ማስፈራሪያ እና ዛቻዎች እየደረሳቸው እንደሆነ ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም፡-

● በዶዶላ ከተማ የሚገኙ የጉዳቱ ተጠቂዎች እንዳስረዱት ከግጭቱ በኋላ ማለትም በሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ከ60 ሰዎች በላይ ስማቸውን በመዘርዘር ከተማውን ለቀው ካልወጡ እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ያዘለ ወረቀት መሰራጨቱን፣

● በባቱ ከተማ ተጎጂዎች አሁንም ከተማውን ለቃችሁ ውጡ የሚል ማስፋራሪያ በስልክና በአካል እየደረሳቸው መሆኑን፣

● ሻሸመኔ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ቤት ለቤት እየሄዱ ከ5 እስከ 10 ሺህ ብር ካላመጣችሁ አሁንም ንብረታችሁን እናቃጥላለን እንዲሁም እንገላችኋለን በማለት ማስፈራሪያ የሚደርሳቸው ሰዎች እንዳሉ እና፣

● በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ በመንግስት የፀጥታ አካላት ሳይቀር ሰዎች እየተደበደቡና ዛቻ እየተፈፀመባቸው መሆኑን (ለምሳሌ፡ በቡራዩ ከተማ በተለይ ከታ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ እንዲሁም በጉና ወረዳ ነገሌ ከተማ) ለማወቅ ተችሏል፡፡

ምክረ ሀሳቦች:-

በኢፌዴሪ ሕገመንግስት እና በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እንደተቀመጠው መንግስት የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች አክብሮ የመንቀሳቀስ እና በሌሎች መንግስታዊ ባልሆኑ አካላትም ጥሰት እንዳይከሰት የመከላከል እና ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ በተለይም በተፈጠረው ችግር ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከጉዳታቸው ሳያገግሙ ለሌላ ጥቃት እንዳይዳረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ስለዚህም የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሰት አስተዳደር እና የፀጥታ አካላት፡-

● ከላይ በተጠቀሱት ስፍራዎች የደረሱ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎችን በፍጥነት በመመርመር የመከላከል እና አጥፊዎችን የመቆጣጠር ስራ እንዲሰራ፣

● የሕግ አስከባሪ እና የፀጥታ አካላት ኃላፊነታቸውን በሚወጡበት ወቅት የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች በማክበር እንዲንቀሳቀሱ ቁጥጥር በማድረግ እና ችግሮች በተከሰቱባቸው ቦታዎችም በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንዲሰሩ፣ እና

● ከላይ በተጠቀሱት ስፍራዎች እና የፀጥታ ስጋት ይኖርባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ ሌሎች ስፍራዎችን በመለየት ተጨማሪ ጥበቃ እንዲደረግ ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳብ ያቀርባል፡፡

2. ሰብዓዊ እርዳታ፣ ድጋፍ እና የተፈናቀሉ ተጎጂዎች ሁኔታ

ምርመራ በተደረገባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ የተቻለ ቢሆንም ተጎጂዎችን ወደ ነበሩባቸው ቦታዎች ለመመለስ እና መልሶ ለማቋቋም መጠነ ሰፊ ስራ እና ጊዜ የሚያስፈልግ እንደሆነ ኮሚሽኑ ይገነዘባል፡፡ ይሁንና ተጎጂዎቹ ለዕለቱ በህይወት ለመቆየት የሚያስፈልጋቸውን ሰብዓዊ እና ሌሎች ድጋፎችን ማቅረብ እና ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ጊዜ የማይሰጥ ከመሆኑ አንፃር የሚከተሉት ጉዳዮች ፈጣን ትኩረት የሚሹ እንደሆኑ ኮሚሽኑ ተገንዝቧል፡፡

● በተለይም የመኖሪያ ቤታቸው እና ንብረታቸው የወደመባቸው ተጎጂዎች አሁንም በሰው ቤት፣ በኃይማኖት ተቋማት እና በሌሎች ስፍራዎች (ለአብነትም በዶዶላ ከተማ በገብረክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፣ በአሳሳ ከተማ ገብርኤል ቤተክርስቲያን፣ በሻሸመኔ ከተማ ተክለ ሀይማኖት፣ ቅዱስ ሚካኤል፣ ጊዮርጊስ እና ኡራኤል አብያተክርስትያናት፣ በአጋርፋ እርሻ ኮሌጅ) ተጠልለው የሚገኙ ቢሆንም እነዚህን ዜጎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑን፣

● በአብዛኛው አካባቢዎች ተፈናቅለው ለሚገኙ ተጎጂዎች በመንግስት አካላት እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ቢደረግላቸውም፤ የሚሰጣቸው የዕለት ምግብ እርዳታና ድጋፍ (ለምሳሌ አጋርፋ፣ ወሊሶ ከተማ፣ ሻሸመኔ ከተማ)፣ የህክምና አገልግሎት (ለምሳሌ አርሲ ነገሌ ከተማ) እንዲሁም መልሶ የማቋቋም እንቅስቃሴው በቂ አለመሆኑን ፣

● በተወሰኑ አካባቢዎች በተለይም በአብያተክርስትያናትና ሌሎች ቦታዎች የተጠለሉ ሰዎችን ለደህንነታቸው ማረጋገጫ ባልተሰጠበት ሁኔታ የመንግስት ኃላፊዎች ወደ ቤታችሁ ካልተመለሳችሁ እርዳታ አታገኙም የሚል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ መጫናቸው (ለምሳሌ በሻሸመኔ እና አጋርፋ) ተገቢ አለመሆኑን ለማየት ተችሏል፡፡

ምክረ ሀሳቦች:-

ኮሚሽኑ የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት የሚረዳ ቢሆንም መንግስት ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች አፋጣኝ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት ስላለበትና በተለይም አሁን ያለንበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የክረምት ወቅት ስለሆነ ተጎጂዎች ለተጨማሪ ጉዳት እንዳይዳረጉ ማድረግ እጅግ የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ስለዚህም፡-

●የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሰት አካላት፣ ከላይ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ዝርዝር መረጃ በማጠናከር፣ ተገቢውን ጥበቃ እና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ በፍጥነት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ በማድረግ ስራ ላይ እንዲረባረቡ፣

● የፌዴራል እና የክልሉ መንግሰታት ሕብረተሰቡን እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ እና ሀገር አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር የዕለት ምግብ እርዳታ፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶች፣ ከኮቪድ-19 ቫይረስ ለመጠበቅ ወይም ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶች፣ የህክምናና የስነልቦና አገልግሎት እና ሌሎች ድጋፎችን ችግሩ በሚስተዋልባቸዉ አከባቢዎች ለሚገኙ ተጎጂዎች በፍጥነት እንዲያቀርቡ ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳብ ያቀርባል፡፡

3. የእስረኞች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ

ኮሚሽኑ ምርመራ ባካሄደባቸው አካባቢዎች ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ በእስር ላይ እንደሚገኙ ለመገንዘብ የቻለ ሲሆን እስከ አሁን በጎበኛቸው በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የእስር ቦታዎች የሚከተሉት አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ችግሮች ተስተውለዋል ፡፡

● በብዙ አከባቢዎች ተጠርጣሪዎች በአነስተኛ ቦታና ክፍሎች ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ መታሰራቸውን ተከትሎ የኮቪድ-19 ቫይረስ ተጋላጭነትን መጨመሩ ፣

● የምግብ እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦት አነስተኛ መሆኑ፣

● የተወሰኑ ታሳሪዎች ድብደባና ኢሰብዓዊ አያያዝ እንደተፈጸመባቸውና ይህም ድርጊት በተገቢው ሁኔታ አለመጣራቱ እና ተጠያቂነት ያለመኖሩ፣

● በአንዳንድ አካባቢዎች ሕፃናት እና አዋቂዎች አንድ ላይ መታሰራቸው፣

● ፍርድ ቤት በዋስትና የለቀቃቸውን እስረኞች የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት በእስር ማቆየት፣

● የተወሰኑ ታሳሪዎች በአፋጣኝ ወደ ፍርድ ቤት አለማቅረብ ናቸው፡፡

ምክረ ሀሳቦች:-

ከተከሰተው የሰላም መደፍረስ ችግር ስፋት አንፃር የእስር ሁኔታን በሚመለከት የመንግስት አቅም ውስንነት እንዳለ ኮሚሽኑ ቢገነዘብም በቁጥጥር ስር የሚውሉ ሰዎች የአያያዝና ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ችላ ሊባል አይገባም፡፡

ስለዚህም የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት አካላት፡-

● የእስረኛ ቁጥርን ለመቀነስ የወንጀል ምርመራ ስራውን በፍጥነት ማካሄድና በነፃ እና በዋስ መለቀቅ ያለባቸውን እስረኞች በአፋጣኝ በመለየት መልቀቅ፣

● እስከ አሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ታሳሪዎችን በአፋጣኝ ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ እና የዋስትና መብት የተረጋገጠላቸውን እስረኞች ዋስትናውን አክብሮ ከእስር መልቀቅ፣

● የኢሰብዓዊ አያያዝ እና ድብደባ አቤቱታዎችን በአፋጣኝ በማጣራት የጥፋተኞችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣

● በብዙ እስር ቦታዎች የሚታየውን መጨናነቅ ለመቀነስ ሌሎች ጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎችን ማመቻቸት፣ ለሕፃናት ልጆች የተለየ ማቆያ ስፍራ ማዘጋጀት እና የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦት የሚሻሻልበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል ፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top