Connect with us

መንግስት የንፁሃን ጥቃት በማንና እንዴት እንደተፈጸመ ግልጽ መረጃ

መንግስት የንፁሃን ጥቃት በማንና እንዴት እንደተፈጸመ ግልጽ መረጃ መስጠት አለበት - አቶ ኦባንግ ሜቶ
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

መንግስት የንፁሃን ጥቃት በማንና እንዴት እንደተፈጸመ ግልጽ መረጃ

መንግስት የንፁሃን ጥቃት በማንና እንዴት እንደተፈጸመ ግልጽ መረጃ መስጠት አለበት – አቶ ኦባንግ ሜቶ

በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በተቀነባበረ ሁኔታ የተፈጸመና ሊወገዝ የሚገባው የከፋ ድርጊት ነው ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ተናገሩ።

ድርጊቱ ከሰውነት፣ አብሮነትና ኢትዮጵያዊነት ይልቅ በሃሰተኛ ትርክትና በማንነት ጥላቻ ላይ ለበርካታ ዓመታት ሲሰራ የነበረ ስራ ውጤት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያዊነትና ሰብዓዊነት ላይ የሚሰሩ ድርጅችን በማቋቋም የሚንቀሳቀሱት የሰብዓዊ መብት ተማጋቹ አቶ አባንግ ሜቶ ከሰሞኑ በዝዋይና ሻሸመኔ ተዘዋውረው ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች አነጋግረዋል።

ከጉብኝታቸው መልስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታም ሰኔ 22 ሌሊት ጀምሮ በተፈጠረው ጥፋት የተጎዱ የ17 ግለሰቦችን ቃል መቀበላቸውን ተናግረዋል።

በተፈጸመው ድርጊት የደረሰው ጉዳት ልብ የሚነካ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ይደረጋል ተብሎ የማይጠበቅ አሰቃቂ አገዳድል የተፈጸመበት አሳዛኝ ክስተት ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የጉብኝታቸው ዓላማም ለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች መሬት ላይ ያለ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ብሎም ተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደነበር አውስተው፤ ድርጊቱ በተራ ግርግር የተፈጸመ እንዳልሆነ ማረጋገጣቸውን ገልፀጸዋል።

ከዛ ይልቅ በአርቲስት ሃጫሉ ሰበብ ሆነ ተብሎ በተደራጀ አካል ስም ዝርዝር የወጣባቸው ሰዎች እየተመረጡ ግድያ እንደተፈጸመ ቤት ንብረታቸውም ከጎረቤት በተለየ ተመርጠው እንዲወድሙ መደረጉን ተናግረዋል።

በተለይም ‘ነፍጠኛ’ በሚል ቃል የተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን እንዳረጋገጡ ነው የተናገሩት።

“ድርጊቱ የትናንት ውጤት ነው” ያሉት አቶ ኦባንግ፤ ትናንት ኢትዮጵያዊነት፣ አብሮነትና አንድነት ላይ ሳይሆን ‘ነፍጠኛ’ በሚል በአንድ ህዝብ ላይ ላይ ያነጣጠሩ ዘር ተኮር የጥላቻ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

“በተለይም ህወሃት የሐሰት ታሪክ በመፍጠር፣ ሰዎች ከሰውነት ወጥተው ማንነታቸው ብሔር ብቻ እንዲሆን መደረጉ፣ እኔና እነሱ በሚል ክልል በመፍጠር እርስ በርስ የጥላቻ ስራዎች መስራቱ ነው” ሲሉ ለአብነት አንስተዋል።

“የተዘራው ኢትዮጵያዊነት፣ ሕብረት፣ እኩልነት፣ ሰላም፣ መከባበር ሳይሆን ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና የሃሰት ትርክት” እንደሆነ ገልጸዋው፤ የተዘራው መጥፎ ዘርም መጥፎ ፍሬ አፍርቷል ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ አሰቃቂ ጥቃቶች በማስታወስም “ሰዎች ሰውነታቸውን እንዲረሱ፣ በትምህርት ስርዓቱም ጥላቻ ያነገቡ፣ የአገር ፍቅር የማያውቁ፣ ንቃተ ህሊና የሌላቸው ወጣቶች በማፍራት ለጥፋት መጠቀሚያ መሳሪያ ተደርገዋል” ሲሉም ያብራራሉ።

መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰቱ ድርጊቶች ትምህርት ሊወስድ እንደሚገባ መክረው፤ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ግጭት በሚል ሳይታለፉ፤ በጉዳዩ ላይ በግልጽ በመነጋገርምር ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግ ይገባል ይላሉ።

“ለሰው እንጂ ለብሔር አልወግንም” የሚሉት አቶ ኦባንግ ሰዎች በታዋቂነት ብቻ ሳይሆን በሰውነታቸው ሊከበሩ፣ ሲሞቱም እኩል እንዲታዘንና ክብር እንዲሰጥ፤ መላው ኢትዮጵያዊም ድርጊቱን በጋራ እንዲያወግዝ አሳስበዋል።

መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች መያዙን ቢገልጽም፤ ጥፋቱ ተራ ግጭት ባለመሆኑ በማንና እንዴት እንደተፈጸመ ግልጽ መረጃ መስጠት አለበት ብለዋል።

ይህ ካልሆነ ፍትህ ሊሰፍንም ሆነ የተጎጂዎች ህሊና ቁስል ሊሽር አይችልም ብለው ወደፊት ሌላ ተመሳሳይ ድርጊት ላለመፈጸሙ ዋስትና የለም ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል።

ድርጊቱ መላውን የኦሮሞ ህዝብና የእስልምና እምነት ተከታዮችን እንደማይወክል ገልጸው፤ በጥፋቱ ወቅት ስም ዝርዝር ወጥቶ ሲፈለጉ የነበሩ ተጠቂዎችን ህይወት እየደበቁ ያተረፉ ጎረቤቶች እንደነበሩ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

“የጥላቻው ምንጭ ከታችኛው ህዝብ ሳይሆን ስልጣን ላይ ለመውጣት በሚፈልጉ ፖለቲከኞች፣ ብሄርተኞች፣ የጥላቻ ሰለባዎችና ጽንፈኛ ቡድኖች የሚተፋት መርዝ ነው” ሲሉም አብራርተዋል።

ሰው ከመሆን ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ የሚገልጹት አቶ ኦባንግ፣ በየትኛውም ቦታ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያወግዘው እንደሚገባ አብራርተዋል።

መንግስት የችግሩን ምንጭ ከስሩ በመረዳት “ህገ መንግስት ከማሻሻል ጀምሮ፣ በዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን ማከም፣ ተደራጅተው ሰዎችን የገደሉ አካላትም በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ተጠያቂ ማድረግ ይገባዋል” ሲሉም አሳስበዋል።

ለአንድ ህዝብ ተለይተው የሚሰጡ ‘ነፍጠኛ’ የመሳሰሉ ቃላትም ሰዎችን ከሰውነታቸው የሚነጥሉና ለጥቃት የሚያጋልጡ መሆናቸውን በመግለጽ ሊወገዱ እንደሚገባ ነው አቶ ኦባነግ ሜቶ የተናገሩት ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top