ፍርድ ቤቱ በወንጀል ድርጊት በተጠረጠሩት አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ 12 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቀደ።
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ጉዳያቸው ቀርቦ ታይቷል።
በወንጀል ድርጊት በተጠረጠሩት አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ባለፉት 13 ቀናት አከናወንኩ ያላቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርቧል።
በዚህ መሰረት በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ባደረገው ፍተሻ ኢትዮ-ቴሌኮም እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ላይ መገኘት ያለበት የሳተላይት መሳሪያ ከውጭ አገር ባለሙያ በማስመጣትና በማስገጠም የተለያዩ ሰዎችን ስልክ ለመጥለፍ አገልግሎት ላይ ውሎ ማግኘቱን ገልጿል።
በፍተሻ የተገኙ ሰባት ሽጉጦችን ለፎረንሲክ ምርመራ ልኮ ባደረገው ማጣራት ሽጉጦቹ የፋብሪካ ቁጥራቸው ተፍቆ በሌላ መተካቱን አረጋግጧል።
ተጠርጣሪው በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ ኤም ኤን) ላይ ባላቸው የአመራር ሚና በብሔሮች መካከል ግጭት እንዲፈጠር መልዕክት ማስተላለፋቸውንና በተለያዩ አካባቢዎች የሰው ህይወት መጥፋት፣ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን፣ የንብረት ውድመት ማጋጠሙን ገልጿል።
በተጨማሪም ሁለት ሃውልቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን፣ ሆቴሎች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማትና ፋብሪካዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ማረጋገጡን ለችሎቱ አስረድቷል።
የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ለምርመራ ልኮ ውጤት እንደደረሰውና የምስክሮችን ቃል መስማቱን ገልጿል።
ተጠርጣሪው ህገ ወጥ መንገድ ቡድን በማደራጀትና መሳሪያ በማስታጠቅ የተለያዩ ሰዎች እንዲገደሉ አድራሻ መስጠታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማሰባሰቡን ገልጿል።
በዚህም አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ እንዲገደል ከተደረገ በኋላ አስከሬኑን በአዲስ አበባ ከተማ ለ10 ቀናት በማቆየት ችግር የመፍጠር ዓላማ እንደነበራቸው ለችሎቱ አስረድቷል።
የአርቲስቱን ህልፈተ ህይወት ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት መድረሱን ማረጋገጡን ያስረዳው መርማሪ ፖሊስ፤ በአዲስ አበባ በሶስት ተቋማት ብቻ ከ166 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ውድመት ማጋጠሙን የሚገልጽ ማስረጃ እንደደረሰው አብራርቷል።
በቡራዩ ከተማም ሰባት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ጉዳት መድረሱን ማረጋገጡን አስረድቷል።
መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ እነዚህን ስራዎች ማከናወኑን ገልጾ፤ 17 ቡድን ተደራጅቶ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሰማራቱ የቡድኑን ውጤት እየጠበቀ እንደሚገኝ ገልጿል።
ከወንጀሉ ክብደትና ስፋት አንጻር ቀሪ የምርመራ ስራዎች እንዳሉት በመግለጽ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው የደንበኛቸው ህገ መንግስታዊና ሰብዓዊ መብት ተጠብቆ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል።
”መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በነበረው ቀጠሮ ካቀረበው የተለየ ነገር አላቀረበም” ያሉት ጠበቆች፤ የተለየና አሳማኝ የሆነ ስራ እንዳልተሰራ ተናግረዋል።
ወደ የተለያዩ አካባቢ ተሰማርቷል የተባለው መርማሪ ቡድን ስለመሰማራቱም ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ወደሙ የተባሉ ንብረቶችን አጣርቶ የጨረሰው መርማሪ የንብረት ግምት እንዳልጨረሰ መግለጹም ጊዜ ለመውሰድ እንደሆነ ጠበቆች ተናግረው፤ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ እንደማይገባ ተከራክረዋል።
ተጠርጣሪው በበኩላቸው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዳለ ገልጸው፤ የተጠረጠሩበት ወንጀል እንደማይመለከታቸው ተናግረዋል።
በተለይም የተያዙት የጦር መሳሪያዎች ህጋዊ እንደሆኑና የግል ጠባቂዎቻቸውም ታማኝ እንደሆኑ ገልጸዋል።
የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቹም በጉምሩክ በኩል የገቡና ህጋዊነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በችሎቱ እየታደሙ ያሉት መገናኛ ብዙሃን የመንግስት ብቻ እንደሆኑ የገለጹት ተጠርጣሪና ጠበቆች፤ ለግልም ሆነ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን መፈቀድ እንዳለበት በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ከጠበቆችና ከተጠርጣሪ በኩል ለተነሱ ጉዳዮች ማብራሪያ የሰጠው መርማሪ ፖሊስ ወደ የተለያዩ አካባቢ ተሰማርቷል የተባለው የመርማሪ ቡድን ያደረገውን ማጣራትና ያገኘውን ማስረጃ ከመዝገብ ጋር ማያያዙን ገልጿል።
የንብረት ውድመት ማወቅና የወደመ ንብረት ግምት ማጣራት የተለያዩ መሆናቸውን በመግለጽ፤ የወደመ ንብረት ግምት ጊዜ የሚወስድና የባለሙያ ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድቷል።
የወንጀሉ ጉዳይ ከባድና ውስብስብ በመሆኑ፣ ተጠርጣሪው ቢወጡ በምስክሮችና በሌሎች በሚፈለጉ ማስረጃዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ መሆናቸውን በመግለጽ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።
ግራ ቀኙን ያዳመጠው ችሎቱ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በተሰጠው ጊዜ በቂ ስራ መስራቱን የምርመራ መዝገቡን አይቶ እንደተገነዘበ ገልጿል።
ተጠርጣሪና ጠበቆች የክርክር ጉዳዮችን እንዳያቀርቡ ትዕዛዝ የሰጠው ችሎቱ፤ የመገናኛ ብዙሃን ችሎቱን ‘ይከታተሉና አይከታተሉ’ የሚለውን አቤቱታ ማቅረብ እንደማይመለከታቸው ገልጿል።
ችሎቱን እንዳይከታተል ስለመከልከሉ አቤቱታ ያቀረበ መገናኛ ብዙሃንን አለመኖሩን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፤ ችሎቱ ለሁሉም ክፍት ስለሆነ መከታተል እንደሚችሉ ተነግሯል።
አዳዲስ ማስረጃዎች እየቀረቡ በመሆኑ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሚያስፈልገው መሆኑን በመግለጽ 12 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመፍቀድ ለነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ሰጥቷል።
ምንጭ :- ኢዜአ