ከእሳትነት ወደ አመድነት የተቀየረ መሽረፍትን እንዴት ይንቃል? (ከአሳዬ ደርቤ)
ከወራት በፊት ከሽሮዋና ከቡናዋ በተጨማሪ ዋይፋይ ፍለጋ በሚመጡ ደንበኞቿ የሚጨናነቀው፣ የሮፍናንን እና የዝሩባቤልን ሙዚቃ በሞንታርቦ ሲያደባልቅ የሚውለው ቤቷ በኮሮና የተነሳ ልክ እንደ ገበያው ሁሉ ሙዚቃውም ቀዝቃዛ ሆኖ የእነ ጸጋዬ እሸቱና ኬኔዲ መንገሻ መራር ሙዚቃዎች የሚሰሙበት ከሆነ ሰነበተ፡፡ ትልቁ ጀበናዋም ቡና ከጠማው ቆየ፡፡
በእርግጥ በእነዚያ ጊዜያት ሞባይልና ላፕቶፓቸውን ይዘው ወደ ቤቷ የሚመጡ ጎረምሶች ሄሉን ሊከልሙ እንጂ ዋይ ፋይ ሊጠቀሙ አስበው የሚመጡ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ያስገባችው ዋይፋይ ፓስወርድ ከመቀበል ውጭ ሌላ ነገር ለማውረድ የሚያስችል አልነበረም፡፡ እናም የይለፍ ቃሉን አስገብተህ ብሮውዘርህን ስትከፍተው Loading ይልህና ዳታውን ትቶ ደቂቃውን መቁጠር ይጀምራል፡፡ በመሆኑም ከረዥም ድካም በኋላ ‹‹unable to connect›› የሚል መረጃ ያወረድክበትንና የሄሉን ዳሌ ያየህበትን ሒሳብ በደቂቃ አስበህ ትከፍልና ‹‹ዋይ ዋይ›› እያልክ ትወጣለህ፡፡
በዚህም የተነሳ ‹‹አለ›› እንዳይባል ምንም አይነት መረጃ የማያወርደውን፣ ‹‹የለም›› እንዳይባል ‹‹አለሁ›› የሚል ምልክት የሚያሳየውን የሄሉ ዋይፋይ ‹‹ዶሮ ፋንታ›› የሚል ቅጽል ሥም ሊሰጠው ችሏል፡፡
የሆነ ጊዜ ታዲያ ‹‹እስኪ ፓሰወርዱን ቀይሪው›› በማለት አንዱ ደንበኛዋ የሰጣትን ምክር ተቀብላ ለብዙ ወራት የይለፍ ቃል ሆኖ ያገለገለውን ሥሜን ሰርዛ የራሷን ሥም ስታስገባው አዝጋሚ የነበረው ዋይፋይ በተወሰነ መልኩ መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር፡፡ ይሄንንም ሁኔታ ያስተዋሉ አንዳንድ ምርኮኞቿ ‹‹የዚህን ገገማ ሰውዬ ሥም ስትሰርዢው የዋይፋይ ዳታው እንደፈጠነው ሁሉ ሰውዬውን ደግሞ ከቤትሽ ብታባርሪው ገባያሽ ይደራ ነበር›› እያሉ ሲያቃጥሩ ሰንብተዋል፡፡
በዚህ መሃከል ግን ኮሮና የሚባል በሽታ መጣና ደንበኞቿን በሙሉ ጠራርጎ በማባረር የይለፍ ቃል ሳይሆን ባል አድርጎ ተከርቼም ሊያስገባኝ አንድ ሃሙስ ቀርቶኛል፡፡
እናም ተከርቼም ለመግባት ካሰብኩበት ቤት የተከርቼም መጽሐፍ ደራሲ የሆነው ይስማእከ አልፎ አልፎ ቡና ሊጠጣ ይመጣል፡፡ ‹‹ምን ይምጣልህ?›› ተብሎ ሲጠየቅም ‹‹ቡና›› ከማለት ይልቅ ወደ ጀበናው አቅጣጫ ጣቱን በመቀሰር በምልክት መናገር ይቀለዋል፡፡ ዝምታው ደግሞ ወደ ሌሎች የሚተላለፍ በመሆኑ ልክ እሱ ሲመጣ ሲንተከተክና ሲፈናጠር የቆየው ሽሮ ጸጥ ይላል፡፡ ሲገነፍል የነበረው ጀበና መፍላት ይሳነዋል፡፡
ያም ሆኖ ታዲያ መጀመሪያ አካባቢ ዝምታውን ሰብሬ ላጫውተው እሞክር ነበር፡፡ ከብዙ ሙከራ በኋላም ደራሲው የመስማት እንጂ የማውራት ፍላጎት እንደሌለው ብገነዘብም ‹‹መናገር ይሄን ያህል የሚደብርህ ከሆነ ውጭ አገር ድረስ ሄደህ መታከም ለምን አስፈለገህ?›› እያልኩ ስጨቀጭቀው ሰንብቻለሁ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይስማእከ የቀድሞ ዝምታውን ትቶ ማውራት ብቻ ሳይሆን ማብራራት ጀምሯል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ምን ይምጣልህ?›› ብላ ሄሉ ስትጠይቀው ማስኩን እያስተካከለ ‹‹ከቻልሽ ስኒና ማንኪያውን ቀቅለሽ፣ ካልሆነ ደግሞ በአጃክስ በደንብ አጥበሽ አንድ ቡና አምጪልኝ›› ይላታል፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ከተጠቃሚው ብዛት ጋር ተያይዞ ሲንቀረፈፍ የከረመው የሄሉ ዋይፋይ ደንበኞቹ ሲጠፉ በጣም ፈጣን ሆኗል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደውም ፍጥነቱን ሳስበው ዳታ ብቻ ሳይሆን ዲኤታ የሚያወርድ ይመስለኛል፡፡
ሄሉም ይሄን አጋጣሚ በመጠቀም ፖለቲካ የምትተነትንበት የፌስቡክ አካውንትና የዪቲዩብ ቻናል ከፍታ ጀበናና ድስት በመጣድ ፈንታ ኦንላይን መጣድ ጀምራለች፡፡ ትናንት እንደውም ‹‹ግልገል አምባገነን›› እና ‹‹ጠባብ ጥቅመኞች›› በሚሉ ስድቦች ለተሞላው የህውሓት መግለጫ መልስ መስጠት አለብኝ›› በማለት ኦን ላይን ገብታ ነበር፡፡
ከዚያም ጀበና ከተጣደበት ፌርሜሎ አጠገብ ተቀምጣ ‹‹በህውሓትና በዚህ እሳት መሃከል ያለውን አንድነት አሳያችኋለሁ›› ካለች በኋላ እሳተ ገሞራ የመሰለውን ፍም በመሽረፈት ታራግበው ጀመር፡፡ በዚህም ሒደት የጣደችው ጀበና እሳት በዛብኝ ብሎ ባገኘው ቀዳዳ ሁሉ መገንፈል ሲጀምር ‹‹እንደ ጌታቸው ረዳ እራስህ ላይ አትገንፍል›› ብላ ውሃ ጨመረችበት፡፡ ይሄንንም ስታደርግ ላይቭ ገብተው የሚመለከቷት ተከታዮቿ ‹‹ማራገቡን ትታ ዳሌዋን እንዲታሳያቸው›› ቢማጸኗትም እሷ ግን በህውሓት የመሰለችውን ፍም እሳት በመሽረፈት ማራገቧን ቀጠለች፡፡
ከዚያም ፌርሜሎውን ብድግ በማድረግ የተቀጣጠለው እሳት ወደ አመድነት መቀየሩን ለተመልካቾቿ ካሳየች በኋላ እንዲህ በማለት ፕሮግራሟን አጠናቀቀች፡፡
‹‹በዚህች መሽረፈት የተነሳ ትናንት እሳት የነበሩት ሰዎች ዛሬ ወደ አመድነት ተቀይረዋል››