“ህገ-መንግስቱ ራስን የማጥፋት ስምምነት አይደለም።” – አብረሃም ሊንከን
(በታዬ ደንደአ~ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር)
የአሜሪካ ህገ-መንግስት በየአራት ዓመቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መካሄድ እንዳለበት ያስቀምጣል። ሆኖም በ1864 ዓም በህጉ መሠረት ምርጫ ማካሄድ ሳይቻል ቀረ። ምክንያቱ ደግሞ ሀገሪቷ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ መሆኗ ነበር። አንዳንዶች ግን በህገ-መንግስቱ መሠረት ምርጫ መካሄድ እንደነበረበት ሽንጣቸዉን ገትረዉ ተከራከሩ። አብረሃም ሊንከን “ህገ-መንግስቱ ራስን የማጥፋት ስምምነት አይደለም” ሲል የተናገረዉ ያኔ ነበር። እዉነቱን ነበር። የማንኛዉም ህገ-መንግስት ቀዳሚ ዓላማ የሀገርን እና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ነዉ። ምርጫ ያንን ግብ ለማሳለጥ እንጂ ለማሰናከል አይደረግም።
በኢትዮጵ ሰሞኑን አንድ ትልቅ ጭቅጭቅ አለ። ጭቅጭቁ በምርጫ ዙሪያ ይሽከረከራል። የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀፅ 58/3 ጠቅላላ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መካሄድ እንዳለበት ደንግጓል። በዝያ ስሌት የገዢዉ ፓርቲ ስልጣን መስከረም 2013 ላይ ያበቃል። ይህ ሁኔታ ቢያንስ ከመስከረም አንድ ወር ቀደም ብሎ ምርጫ ማካሄድን ይጠይቃል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የፌዴራልና የክልል ም/ቤቶችን ምርጫ ለማድረግ ለነሓሴ 20/ 2012 ቀጠሮ ይዞ ነበር። ነገር ግን ተጨባጭ ሁኔታዉ ድንገት ተቀይሯል። ኮቪድ-19 ከባድ አለም አቀፍ አደጋ መደቀኑን የሚክድ የለም። ለአለም በሙሉ የህልዉና ስጋት ሆና እጅግ ብዙ ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ መረሀ-ግብሮችን እንዳልነበሩ አድርጓል። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ስጋት ፈጥሯል። በዝህ ሁኔታ ዉስጥ ምርጫ ማካሄድ አይታሰብም። ስለዝህ ሁነኛ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል። ጭቅጭቁ የመፍትሔዉን ምንነትና አተገባበር ይመለከታል።
አንዳንዶች “ምርጫዉ የግድ መደረግ አለበት” ሲሉ ይደመጣሉ። በተለይ ወያኔ በፌዴራል ምርጫ ባይደረግ እንኳን በክልል ደረጃ ምርጫዉን እንደሚያካሄድ ይፎክራል። የባህሪ ወዳጁ የሆነዉ ኦነግ ሸኔም ተመሳሳይ አቋም ይዞ ይደግፏል። ይህ በሁለት ምክንያቶች ያሳዝናል። አንደኛዉ ስልጣንን እንጂ ህዝብን አለማየታቸዉ ነዉ። ለወያኔ እና ለጓዶቹ ስልጣን የመጨረሻዉ ግብ ነዉ። እነሱን ለስልጣን ኮርቻ እስከ አበቃ ድረስ ማንኛዉም ተግባር ትክክል ነዉ። ለህዝብ እና ለሀገር ደህንነት ግድ የላቸዉም። ይህ የወያኔ እና የኦነግ ሸኔ ዘላቂ አቋም ነዉ። የነዝህ ቋሚ ፍላጎት ህዝብን መጥቀም ሳይሆን በህዝብ መጠቀም እንደሆነ ታሪካቸዉ ይመሰክራል። የኮሮና አደጋ በህዝብ ላይ በተደቀነበት አስቸጋሪ ወቅት የህዝብን ደህንነት ዘንግተዉ ስለምርጫ መጮሃቸዉም ይህንኑ በግልፅ ያረጋግጣል። አንድም ቀን ስለኢትዮጵያ ሳያስብ በኢትዮጵያ “ጄኔራል” የሆነ ሰዉ ከወያኔ ሰፈር መገኘቱም ተጨማሪ ማሳያ ነዉ።
ሁለተኛዉ ምክንያት ህገ-መንግስቱን ጨርሶ አለማወቃቸዉ ነዉ። ወያኔ እና ጓዶቹ ህገ-መንግስቱን ሳያዉቁት “ለማስከበር” ይሰራሉ። ይህ ባይሆን ኖሮ ምርጫ ቦርድ ህገ-መንግስቱ ባስቀመጠዉ ጊዜ ዉስጥ ምርጫን ማካሄድ እንደማይችል እያሳወቀ ክልል ላይ ምርጫ አይሉም ነበር። በየትኛዉም ደረጃ ቢሆን ህዝባዊ ምርጫ የሚካሄደዉ በምርጫ ቦርድ አስፈፃሚነት ነዉ። ምርጫ ቦርድ ደግሞ የፌዴራል ተቋም ነዉ። ክልል የራሱ የምርጫ አስፈፃሚ አካል የለዉም። ስለዝህ አንድ ክልል ከፌዴራሉ መንግስት ተለይቶ ለብቻዉ ህዝባዊ ምርጫ ማካሄድ አይችልም። ያለህጋዊ አስፈፃሚና ታዛቢ የሚደረግ ምርጫ ትርጉም የለዉም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማያዉቀዉ ምርጫ በኢትዮጵያ አይደረግም ማለት ነዉ። ወያኔ ያለምርጫ ቦርድ ዕዉቅና የራሱን ድርጅታዊ ጉባኤ አድርጎ አመራሮቹን መቀየር እንኳን አይችልም። ምርጫ የፍላጎት እና የጉልበት ሳይሆን ህጋዊ ህደት ነዉ። ይህንን ቀላል ጉዳይ ሳያዉቁ በህገ-መንግስት ስም መማልና መገዘት ያሳፍራል!
አሁን እንደሀገር አጣብቅኝ ዉስጥ ነን። ህገ-መንግስታችን ከመስከረም በፊት አጠቃላይ ምርጫ እንድናደርግ ይጠይቃል። ኮቪድ-19 ደግሞ ምርጫ ማካሄድ እንዳንችል አድርጎናል። ስለዝህ ተጨባጭ መፍትሔ መስጠት ይኖርብናል። ዋናዉ ጉዳይ አደጋዉን መከላከል ይሆናል። ምርጫ በራሱ ግብ ስላልሆነ የግድ ማራዘም ያስፈልጋል። ለሀገር እና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ህገ-መንግስታዊ ክፍተቱ መፍትሔ ያስፈልጓል። መፍትሔዉ ደግሞ የሌሎችን ልምድ የቀመረ እና ተጨባጭ ሁኔታችንን ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል። ከምንም በላይ ደግሞ በህገ-መንግስቱ መንፈስ የተቀኘ ሆኗ የኢትዮጵያን ህገ-መንግስታዊነት ይበልጥ የሚያዳብር መሆን አለበት። ህገ-መንግስቱ በዓላማና በተግባር ሳይጣስ አደጋዉን ለመከላከል የሚያስችል መፍትሔ ይጠበቃል። “የትኛዉም ህገ-መንግስት ራስን የማጥፋት ስምምነት አይደለም!” የሚለዉን መርህ በመተከተል ህገ-መንግስቱን በአዎንታዊ መንገድ መተርጎም አሁን ግድ ይላል!