ሥልጣን በብቃት የሚሰጥ ኃላፊነት እንጂ በዘር የሚወረስ ርስት አይደለም
(ዮሐንስ መኮንን)
በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ የኢትዮጵያ ቆንስላ የነበሩት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል አበበ ሰኚ ከሹመታቸው መነሳታቸውን ተከሎ አንደተለመደው ብሔርተኞቹ ሠፈር አቧራው ተነስቷል።
ሰውየው ምንም እንኳን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በአሜሪካ ሎስአንጀለስ እንዲወክሉ ቢሾሙም በየወቅቱ በአደባባይ የሚያቀርቧቸው ንግግሮች ሲደመጡ የብሔር እንጂ በፍጹም የሀገር ተወካይ አይመስሉም።
ለምሳሌ ከሥልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ባለሁለት ክፍል እና 16 አንቀጽ ረዥም ጽሑፉቸው እንደ አንድ ዲፕሎማት ወቅታዊ ሀገራዊ ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩት አባ ባህሬይ ከተባሉ መነኩሴ እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ አጼ ምኒሊክ ተጠያቂ አድርገዋል።
እርሳቸው ቢረሱትም በ Jan23-19 Arts TV ላይ ቀርበው ሲናገሩ “ለውጡ በእርግጠኝነት በጽኑእ መሠረት ላይ የቆመ ነው” ብለውን ነበር። በ Jan28-19 ደግሞ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ላይ “በሀገሪቱ የእኩልነት እንጂ ነጻ የመውጣት ጥያቄ አልነበረም” የሚለው አቋማቸው ታትሞ ነበር። ይህንን ሁሉ ረስተው ዛሬ ላይ የለውጡን ሂደት ወቃሽ እና ከሳሽ ሆነዋል።
ዶክተሩ የኋላ ታሪካቸው እንደሚነግረን ከለውጡ በፊት የውጭ ጉዳይ ሠራተኛ ነበሩ። ሀገሪቱ ለትምህርት አሜሪካ ሜኒሶታ እንደላከቻቸው በዚያው ከድተው ቀሩ። ውጪ ሀገር በቀሩባቸው ዘመናት አክራሪ ብሔርተኛ አክቲቪስት በመሆናቸው የሚታወቁ ሲሆን አስቂኙ ነገር በጽሑፋቸው 5ኛው ቁጥር ላይ ሌሎችን “ሀገር ጥለው የፈረጠጡ” ሲሉ “አሀዳውያን” የሚሏቸውን ወገኖች ይወቅሳሉ።
ለውጡን ተከትሎ አንዳንድ ፖለቲከኞች (ስማቸው ለጊዜው ይቆየን እና) ዶክተሩን “የተሻለ ሥራ ለመሥራት ያግዙናል” ብለው ድጋፍ አድርገውላቸው ስለነበር በቆንስላነት ተሾሙ። በወቅቱ ከራሳቸው ብሔር የሆኑ የውጭ ጉዳይ ሰዎች ሳይቀሩ በሹመታቸው ላይ ቅሬታ እንደነበራቸው ተሰምቶ ነበር። የቅሬታቸው መነሻ ደግሞ “ኃላፊነቱን ትቶ ሀገራዊ አደራውን ጥሎ የኮበለለ ሰው መሾም የለበትም። ለዲፕሎማሲ ሥራም ጥሩ ምሳሌ አይደለም” የሚል ነበር።
ሰውዬው እንደ አንድ ተራ አክቲቪስት ከኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለቀሩቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸውን መልሶች ብቻ ሚናቸው የተምታታ እንደነበር ያሳያል።
—————————–
– አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች የኦሮሞ ስለሆኑ መተዳደር ያለባቸው በኦሮሞ ነው።
– የከተሞች ፓሊሲ ሲዘጋጅ በእኘኚህ ከተሞች (በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ) ኦሮሞን መልሶ ለማስፈር መሠራት አለበት።
– በአዲስ አበባ በአራት ኪሎ እና በሌሎች አከባቢዎች የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ከ40 እስከ 50 በመቶ ኦሮሞን ማስፈር ያስፈልጋል።
– በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተሞች የንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ቅድሚያ ለኦሮሞ መሰጠት አለበት ወዘተ ሲሉ ተደምጠዋል።
– የኦሮሞ መስጊድ እና የኦሮሞ ቤተክርስቲያን (ለብቻ) ያስፈልገናል።
—————————–
በግሌ እንደ አንድ ግብር ከፋይ ዜጋ ሀገሬን እና ህዝቦቿን በዓለም አቀፍ መድረክ የሚወክል ዲፕሎማትም ይሁን ሹመኛ በግሉ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ቢኖረው በአደባባይ ግን ከሀገሪቱ መንግሥት ኦፊሴላዊ አቋም እንዲያንጸባርቅ እጠብቃለሁ።
ከሀገሪቱ መንግሥት የተለየ አቋም የሚያንጸባርቅ ከሆነ ግን እንኳንስ ቆንስላ እና አምባሳደር ሚንስትርም ቢሆን ሥልጣኑን ማስረከብ እና ምርጫውን መከተል አለበት እላለሁ።
ማንም ሹመኛ የግሉንም ሆነ የቡድኑን የተለዩ ፍላጎቶች በመንግሥት ቢሮ ሆኖ በህዝብ ገንዘብ በሚመደብ በጀት ሳይሆን በራሱ ቢሮ ሆኖ የሀሳቡ ደጋፊዎች እና የዓላማው ተጋሪዎች በሚሰበሰብ መዋጮ ሀሳቡን ለገበያ (ለውድድር) ቢያቀርብ ችግር የለውም።
ሁሉንም ዜጋ በእኩል ለማገልገል የመንግስት ሥልጣን (ሹመት) ከተቀበሉ በኋላ ግን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ከመሥራት ይልቅ እንደ ዶ/ር ብርሃነ መስቀል እንደጀማሪ አክቲቪስት አድልኦ እና መለያየትን በዚህ መልኩ በአደባባይ መስበክ የተረከቡትን ኃላፊነት፣ የትምህርት ደረጃቸውንም ሆነ ዘመኑን የሚመጥን አይመስለኝም፡፡
የማንም ሥልጣን ርስት አይደለም። ብቃት ያላቸው፣ ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን ያለመድሎ የሚያገለግሉ ከኦሮሞ ሆኑ ከጋሞ ከትግሬም ሆኑ ከአደሬ … ሺህ ዓመት ቢነገሱ በግሌ ብሔራቸውም ሆነ የመጡበት መንደር ጉዳዬ አይደለም።
የተጣለባቸውን ብሔራዊ ኃላፊነት መሸከም ከብዷቸው ሀገራዊ ሥራን ከመንደር ፓለቲካ ጋር በማምታታት በብቃት ማነስ ከሥልጣን ሲሻሩ “በእኔ እና በብሔሬ ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ነው” ብሎ ማጯጯህ ሥልጣን በብቃት የሚሰጥ ኃላፊነት እንጂ በዘር የሚወረስ ርስት አለመሆኑን አለመረዳት ነው።
———————————-
በመጨረሻም …
ኮሮና ከፍቷልና ለክፉም ለደጉም …
#ወደ_ፈጣሪ_እንጸልይ
#ር_ቀ_ታ_ች_ን_ን_እንጠብቅ
#እጆቻችንን_በሳሙና_እንታጠብ
#አፍና_አፍንጫችንን_እንሸፍን