Connect with us

ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ

ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ
Photo Facebook

ጤና

ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ

ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ

ዕውን የኮሮና ቫይረስን ለመመከት የሚያስችል አደረጃጀትና ብቃት አለን?

በተቋርቋሪ የጤና ዘርፍ ሙያተኞች

ጉዳዩ:- የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አመራርና አደረጃጀት ማስተካከል አሳሳቢውን የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ የመከላከል አካል ተደርጎ እንዲሠራ ስለመጠየቅ፣

ክቡርነትዎ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተሾሙ ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ የተጠራቀመውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እያደረጉ ያሉትን አርአያነት ያለው ተግባር በከፍተኛ አድናቆት የምንመለከተው ነው። ይህን አበረታች ጅምር ዳር ለማድረስ እኛም እንደ አንድ የከተማው ነዋሪና ባለሙያ የበኩላችንን ማድረግ አለብን ብለን እናምናለን።

ክቡር ከንቲባ፣ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከተሰማ በኋላ መንግሥት ሥርጭቱን ለመግታት የሚያስችል መጠነ ሰፊ ጥረቶች በማድረግ ላይ መሆኑን የሥራው አካል በመሆናችን በቅርብ የምናውቀው ነው፡፡

ለክቡርነትዎ ይህን ግልፅ ደብዳቤ ለመጻፍ የተነሳንበት ዋናው ምክንያትም ይኸው ከቅን ሐሳብ፣ የሙያ ግዴታ፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን ቆራጥ አመራር አስፈላጊነትንና በእከክልኝ ልከክልህ ነገሮችን መሸፋፈን በሕዝባችን ላይ የሚያስከትለውን ችግር ግምት ውስጥ በመክተት እንደዚህ ቀደሙ በፍርኃት ዝም ማለት ስላልቻልን የራሳችንን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለን ሰው ለማዳን መሆኑ እንዲታወቅ እንፈልጋለን፡፡ እርስዎም ከዚህ በመነሳት አገርና ሕዝብ የጣለብዎትን አደራ እንደሚወጡ በሚገባ እናምናለን፡፡

ክቡርነትዎ፣ እኛ የጤና ባለሙያዎች በአያሌው ያሳሰበን ይህን ወረርሽኝ በበላይነት ለመምራት ከባድ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ተቋማት ግንባር ቀደሙ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ በአቅም ማነስና በአሠራር ችግሮች መተብተቡ ነው። በዚህ ምክንያት ቢሮው በዚህ ወቅት ይህን ከባድ ኃላፊነት እንደምን ይወጣል የሚለው በብርቱ አሳስቦናል፡፡

እርግጥ ነው ክቡርነትዎ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ የጤና ቢሮ ቁልፍ አመራሮችን ሹም ሽር አድርገዋል። ነገር ግን በአሁን ሰዓት የመጣብንን ከባድ የወረርሽኝ አደጋ ለማሸነፍ አሁን እየተወሰዱ ካሉ ተስፋ ሰጪ ዕርምጃዎች በተጨማሪ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አደረጃጀትና የሰው ኃይል ዝግጁነት መፈተሽ በሚከተሉት ምክንያቶች ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን፡፡

1ኛ. የተመደቡልን ነርስ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በዚህ አስፈላጊ ወቅት የት ነው ያሉት?

በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ወቅት ትልቅ የጤና ባለሙያዎች እጥረት ያጋጠመ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ በአገራችን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በትምህርትና በጡረታ ላይ ያሉትን የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በተጠንቀቅ ለአገር ግዳጅ ተዘጋጅታችሁ ተጠባበቁ ብለው ጥሪ ሲያደርጉ እያየን በአዲስ አበባ የጤና ቢሮ ሥር ከደሃ ማኅበረሰባችን ቀረጥ ተሰብስቦ ደመወዝ ተከፍሏቸው የሚሠሩትን ነርስ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ወደ ሥራ ማስገባት አለመቻሉ እንደ ባለሙያ እንደ ዜጋ እያየን ቸል ማለት የሙያ ሥነ ምግባራችን የሚፈቅድልን አይደለም፡፡

በአዲስ አበባ ደረጃ በሽታን አስቀድሞ መከላከልን ቅድሚያ የሚሰጠው የጤና ፖሊሲያችንን መሠረት በማድረግ ለ500 አባወራ ቤተሰብ፣ አንድ ነርስ የጤና ኤክስቴንሽን ተመድቦ የቤተሰቡን አጠቃላይ የጤና ሁኔታ እንዲከታተል መደረጉና ጅምር ላይ አኩሪ ሥራ መሠራቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ይህን አደረጃጀት በንዑስ የሥራ ዘርፍም በቅርቡም በዳይሬክተር ደረጃ የሚመሩት አካላት የጤና ኤክስቴንሽን ክፍልን መምራት ከጀመሩበት ሰዓት ጀምሮ ሥራውን በተገቢው ደረጃ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴርና አጋር ድርጅቶች የሚደረጉትን ድጋፍና ግብዓቶች በአግባቡ ተጠቅሞ ሥራ እንዳይሠራ በማድረጋቸው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የነርስ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያ (የቤተሰብ የጤና ቡድን) በየቤታችን በር አንኳኩተው የማስተማር፣ የመለየት ብሎም የመከላከል ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ሆኗል፡፡ ስለሆነም በዚህ ወቅት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተመደበ ነርስ (የቤተሰብ የጤና ቡድን) ካየናቸው፣ ካነጋገርናቸውና ካወያየናቸው ስንት ጊዜ እንደሆነ እርስዎ ከታች ያለውን ሕዝብ ወርዶ የማነጋገር የተለየ አመራር የሚከተሉ በመሆኑ ሄደው አይተው እንዲመሰክሩና ይህ ሥራ ምን ያህል ሆን ተብሎ የተኮላሸ መሆኑን እንዲረዱት እንጠይቃለን፡፡

በከተማ ጤና ቢሮ ደረጃ ይህን ሥራ የሚመራው ዘርፍ ለሥራው የሚያስፈልገውን ግብዓትና ተልዕኮ ሰጥቶ የማሰማራት ውስንነቶች የተነሳ ሕዝቡ የሚገባውንና መብቱ የሆነውን አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ የቢሮው ከፍተኛ አመራር ይህንን ሥራ ያለበትን ክፍተት ተረድቶ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ በተለያዩ ወቅቶች ችግሮቹን ያመላከትን ቢሆንም በማናውቀው ምክንያት ተገቢውን የማስተካከያ ዕርምጃ አልተወሰደም፡፡

2ኛ. የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በከተማችን በዋናነት የሚመለከተው የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ተቋም የት ገባ?

ማንኛውም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች በዓለም ደረጃና በየትኛውም አገሮች ከመከሰታቸው በፊትና ከተከሰቱ በኋላ በቀጥታ ሥራውን ወስደው የሚሠሩ የሚመለከታቸው አካላት አሉ፡፡ ለምሳሌ የዓለም ጤና ድርጅት በዚህን ወቅት የኮሮና ወረርሽኝን በዓለም ደረጃ በመምራትና ሥራዎችን በማስተባበር የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ በአሜሪካ፣ በቻይና፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እንዲሁም በሌሎች አገሮች ይህንን የሚመራ ተቋም ሲዲሲ (የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል) ይባላል፡፡ ወደ አገራችን ስንመጣ ይህ ዓለም አቀፋዊ የአሠራር ሒደትን ተከትሎ በፌዴራልና በክልሎች (አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣…) የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተቋቁሞ ለኅብረተሰቡ እስከታች ድረስ የመረጃ ፍሰቱንና የሥራውን ሒደቱን እያቀላጠፈ፣ እየመራና እያስተባበረ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን የዓለም የዲፕሎማቶች መቀመጫ፣ የአፍሪካ መዲናና መግቢያ በር የሆነችው ከተማችን አዲስ አበባ ሆን ተብሎ ይህ ተቋም እንዳይኖራት ተደርጓል፡፡

ከተማችን እንደ ኮሮና ላሉ ወረርሽኞች ተጋላጭነቷ ከፍተኛ ይሆናል በሚል ታሳቢ ተደርጎ ከሌሎቹ የአገራችን ክልሎች በተለየ ለአፍሪካውያን ብሎም ለዓለም ሞዴል በሚሆን መንገድ የአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የማuuሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀደም ሲል ለነበረው የአስተዳደሩ ካቢኔ እንደቀረበ ይታወሳል፡፡ ራሱን ችሎ እንዲደራጅ ብዙ ከተራመደ በኋላ ዕውን ያልሆነው በቢሮው ውስጥ ይህ አደረጃጀት ከእኛ እጅ ከወጣ ጥቅማችን ይቀርብናል ከሚል አግባብ ካልሆነ አስተሳሰብ በመነሳት በሠሩት ሥራ ነው። ይህ ተቋም ራሱን ችሎ ተደራጅቶ ቢሆን ኖሮ እንዲህ እንደኮሮና ዓይነት ወረርሽኝ ሲከሰት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ትልቅ አቅም መሆን በቻለ ነበር። ይህንን ማረጋገጥ ይችሉ ዘንድ በእርሶ ጽሕፈት ቤት የተቋሙን ማቋቋሚያ ሰነድ አስወጥተው ሊያዩት እንደሚችሉ እናስታውሳለን፡፡ በዚህም አጋጣሚ መልካም ፈቃድዎ ከሆነ ከተማዋ የሚገባትን የተደራጀና የተቀናጀ ብሎም ራሱን የቻለ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲያuቁሙልን እንጠይቃለን፡፡

በተጨማሪም በተለያየ ወቅት የተከሰቱትን ወረርሽኞች እንደነአተት ወረርሽኝ ላይ በተግባር ተፈትኖ ውጤታማ የሆነና ልምድ ያለውን የድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች እስከ ወረዳ የሚወርደውን መዋቅር ለሕዝብ ግድ የሌላቸው ስዎች ምክንያት ሆን ብለው በወረዳ ብሎም በክፍለ ከተማ ደረጃ አደረጃጀቱን ራሳቸው ወደሚመሩት ክፍል ስር በመውሰድ ትኩረት ተነፍጎት እንዲዳከም ተደርጎ ወረርሽኝ በመከላከልና በመቆጣጠር ልምድ ያካበተውን ባለሙያ እንዲበተን አድርገውታል፡፡ ይህም ድርጊት የሚያስከትለውን የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቀድመው የተረዱት እነዚህ ባለሙያዎቹ እስከ ጤና ሚኒስቴር ድረስ ሄደው በአስቸኳይ ይህ ችግር እንዲስተካከል በጠየቁት መሠረት በወቅቱ የነበሩት የጤና ሚኒስትር የተቋሙ መታጠፍ አደጋ እንዳለው ተገንዝበው የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ ደብዳቤ የጻፉ ቢሆንም በተገቢውና በሚገባው መንገድ ሳይስተካከል ልምድ ያለው ሠራተኛ እንደተበተነ ሆኗል፡፡

አሁን በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በቀጥታ ሥራውን ተረክቦ መሥራት፣ ማስተባበርና ማቀናጀት ብሎም መምራት የነበረበት ይህ አደረጃጀት በመዳከሙ ሥራዎችን በየአካባቢው በተቀናጀና በተሰናሰለ ሁኔታ እንዳይካሄዱ እየሆነ ነው፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ቤት ለቤት የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችን አስሶ የማግኘትና (active surevilance) ተጠርጣሪውን ከኅብረተሰቡ እንዲለይ እየተደረገ አይደለም፡፡ ለዚህም ማሳያ በሌሎች ዓለማት እንደምናየው የቤት ለቤት የሙቀት መለካትንና ኅብረተሰቡን በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሙቀት ልየታ ጣቢያዎችን በማቋቋም ሥራ አለመሠራቱ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ በየወረዳው የበለጠ ተጋላጭ ቦታዎች (Vulnerability assessment and risk mapping) ተለይተው የመከላከል ሥራ ሲከናወንም አይስተዋልም፡፡ ለምሳሌ ለዚህ ወረርሽኝ ተጋላጭ የሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ የኅብረተሰብ በአንድነት ተከማችቶ የሚገኝበት ቦታዎች እንደ ኮንዶሚኒየምና የተጠጋጉ የመኖርያ ቤቶች እንዲሁም የንጹህ ውኃ እጥረት ያለባቸው ቦታዎች ከብዙ በጥቂቱ እንደሆኑ ቢታወቅም፣ እስከ ዛሬ ድረስ በግልጽ በሰነድ በተደገፈ መሠረት ለዚህ ወረርሽኝ የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችና የመከላከያ መንገዶች (ለምሳሌ የውኃ እጥረት ያለባቸው ቦታዎች ላይ በቦቴ ውኃ እንዲቀርብ የማስተባበር ሥራ ሲሠራ አይታይም) ተለይተው ተገቢው ሥራ አለመከናወኑ የዚህ ተቋም እንዲዳከም መደረግ አንድ መገለጫ ነው፡፡

በተጨማሪም በእግር ኳስ ደጋፊዎችና ከተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች በሚገርም ሁኔታ የሚያሳዩትን ተነሳሽነትና በጎ ተግባር አቀናጅቶና በሙያ ደረጃ ያለሙለትን የበሽታ መከላከል ጥረታቸውን አስተባብሮና አቀናጅቶ ሐሳባቸው ከግብ እንዲደርስ የሚመራው ተቋምና ተገቢው ባለሙያ ባለመኖሩ ወይም ሥራውን ባለመሥራቱ ምክንያት በጎ ፈቃደኞቹ በገባቸው ልክ የሠሩት ሥራ ራሳቸውን ብሎም ኅብረተሰቡን ለበሽታው የመጋለጥ አደጋ ውስጥ እንዳይከት ሥጋት አለን፡፡ ይህንን ስንል የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮቻችንን ጥረትና ተነሳሽነት ተገቢው ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን ሳንዘነጋ ለወደፊቱ ለሚደረጉ ሥራዎች ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ቢታከልበት የበለጠ ወደ ጋራ ግባችን ያደርሰናል ከሚል ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ተነስተን ነው፡፡

በአገራችን ውስጥ ያሉ ክልሎችና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የየራሳቸው የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ ስልክ (Hot line) ያላቸው ሲሆን ይህን ማድረጋቸው በክልላቸው የሚከሰቱ የበሽታ የመጋለጥ ጥርጣሬዎችንና ጥቆማዎችን በአፋጣኝ ለጥሪው መልስ ለመስጠትና የበሽታውን መስፋፋት በጊዜው የበሽታ መተላለፍን ለማቋረጥ እንዲያስችላቸው ነው፡፡ ከሁሉም ክልሎች የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ብቻ የራሱ የሆነ የአስቸኳይ ጥሪ ስልክ የሌለውና በዚህም ምክንያት በአሁን ሰዓት እንደሚታየው የክልሉን በሽታ የመለየት ሥራውን በራስ አቅም መሥራት አለመቻል በፌዴራሉ የስልክ መስመር ላይ የተደራሽነት ችግር እንዲባባስ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

ክቡርነትዎ፣ አሁን በዚህ ሰዓት በጠረጴዛዎ ላይ ለዚህ በሽታ ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦች፣ አካባቢዎች፣ በሽታን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶች የሰው ኃይልንና መፍትሔዎችን ጨምሮ የትና መቼ እንዴት የሚሉት የከተማችን የኮሮና ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ዝርዝር ዕቅድ አግኝተዋል ወይ? በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት የተገመተ ለበሽታው ሊጋለጡ የሚችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቁጥርና እነሱን የምናስተናግድበት የለይቶ ማቆያ ሥፍራዎች፣ የአልጋ ብዛት፣ በተለይ ሕሙማንን የምንታደግበት ቬንትሌተር በምን ያህል ደረጃ ዓይነትና ጥራት ተዘጋጅተው በተጠንቀቅ ላይ እንዳሉ የሚያሳይ ሰነድ አልዎት ወይ?

በአጠቃላይ ሲታይ በአሁኑ ሰዓት ከወረርሽኝ ጋር የተያያዙ ቴክኒካል ሥራዎች እየተሠሩ ያለው በፌዴራል ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሙያተኞች ነው፡፡ በከተማ ደረጃ በዚህ ተቋም መሠራት ያለበትን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በተደራቢነት እየሠሩ ያሉት ጤና ቢሮው ሳይሆን እነዚህ አካላት ናቸው፡፡ ይህ ተክቶ መሥራት በሽታው በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ እየተሠራጨ ከሄደ ቀጣይነት የሌለው በመሆኑ ይህንን ተቋም ማጠናከርና በተገቢው ሁኔታ ራሱን ችሎ ወደ ሥራ በአስቸኳይ ማስገባት በተለይ በዚህ ወቅት በይደር የሚተው ተግባር መሆን የለበትም፡፡

3ኛ. የጤና ቢሮው አሳሳቢ ገጽታ

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮው ረዘም ካለ ጊዜ ጀምሮ በችግር ውስጥ መኖሩ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በኮሮና ወረርሽኝ ሕዝብ ከባድ ሥጋት ውስጥ በወደቀበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የጤና ቢሮው አካሄድን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

ለአብነት ያህል እንደ አገር ለዚህ በሽታ የሚውል የገንዘብ ዕርዳታ በአንድ ቋት ውስጥ ብቻ እንዲሰበሰብ የወጣ አቅጣጫ የወረደ ቢሆንም ይህ ቡድን ግን በሥሩ ያሉትን መንግሥታዊ ያልሆኑ በጤና ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች (NGO) ፕሮግራማቸውን አጥፈው ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ገንዘባቸውን ገቢ እንዲያደርጉ አዟል፡፡ ይህ በመሠረቱ በአስተሳሰብ ደረጃ ተገቢ ነው አይደለም የሚለውን ትተን በተለምዶ ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ በከተማችን በተከሰቱ ወረርሽኞች እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ትዕዛዝ እየተላለፈ በዚሁ አካል ገንዘቡ ለታሰበለት ዓላማ አለመዋሉን መታዘብ ችለናል (በተደጋጋሚ ተከስቶ የነበረ የአተት ወረርሽኝን መጥቀሱ ብቻ በቂ ነው)፡፡

ክቡር ከንቲባ ሆይ፣ ከዚህ ቀደም በተከሰቱ ወረርሽኞች በጤና ተuማት ወረርሽኙን በመከላከልና በማከም ለተሳተፉ ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያዎች ማስፈጸሚያ የተበጀተውን በጀት ተገቢውን ሥራ ሠርተው ክፍያ ባላገኙ ሠራተኞች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታና አለመተማመን መፍጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ ይህም ጉዳይ የሚመለከተው ሠራተኛ ኮሚቴ አዋቅሮ እስከ ጤና ሚኒስቴርና ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ድረስ ቅሬታ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይህንን የፈጠረው አመራር አሁንም በቦታው ላይ በመሆኑ ቀጣይ በዚህ ወረርሽኝ ላይ የባለሙያውን ሙሉ እምነትና የአመራር ተቀባይነትን አግኝቶ ለመምራትና ለማስተባበር የሞራል ብቃት ይኖረዋል ወይ?

በዚህ አጋጣሚ ለአገራችንና ሕዝባችን በአሁን ሰዓት ያጋጠመንን የኮሮና ወረርሽኝ ከሕዝባችን ጋር በመሆን እስከ ሕይወት መክፈል ድረስ በነፃ ለማገልገል ያለንን ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

በጤና ቢሮ ያለውን ገጽታ ሌሎች የሴክተሩ ሠራተኞች በራሳቸው አንደበት ስለሚገልጽልዎት እኛ አሁን ትኩረት ያደረግነው ከፊታችን የተደቀነውን የሞት ሽረት ትግል የሆነውን አደጋ ለመወጣት በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዴት ልንገባ እንደምንችል አመላካች መንገዶችን መጠቆም ላይ ብቻ መሆኑ ይታወቅልን፡፡

4ኛ. የጤናው ሴክተር አመራር እውነታ፣

ክቡር ከንቲባ፣ የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል በዋነኝነት የሚመለከታቸው በአዲስ አበባ ጤና ቢሮው ሁለት ዳይሬክቶሬቶች አሉ። እነሱም የጤና ማበልጸግና በሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬትና የኅብረተሰብ ጤና ምርምርና ድንገተኛ አደጋዎች ዳይሬክቶሬት ይባላሉ። እነዚህ ሁለት ቦታዎች እንደተለመደው እስከ አሁን በከተማችን እንዲሁም በሴክተራችን እንደምናየውና እንደምንታዘበው አቀናጅቶና አደራጅቶ የመምራት ችግር እንዳለ ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከአቅም በታች በሆነ የአመራር መንገድ እንዲጓዙ መፍቀድ እስከዛሬም ድረስ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ለወደፊቱም ከፍተኛ ዋጋ እንዳያስከፍለን የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፡፡

በተጨማሪም በአሥሩም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የጤና ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ያሉ አንዳንድ አመራሮች ከጤናው ሴክተር ጋር ግንኙነት የሌለው ሙያ ያላቸው በመሆኑ በዚህ ፈታኝ ወቅት ይህን ወረርሽኝ ለመምራት አሉታዊ ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ዋጋ ስለሚያስከፍሉ የሠራተኛውን ቅሬታ በመፍታት ማስተካከያ ዕርምጃ መወሰድ አለበት ብለን እናምናለን፡፡

ከቻይና ተሞክሮ እንደምናየው ወረርሽኙ በተከሰተበት ሁቤ ግዛት ላይ የአመራር ማስተካከል ዕርምጃ በመውሰዷ የተነሳ በአሁን ሰዓት በሽታውን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መቆጣጠር የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ስለሆነም ሁሉም አደረጃጀት ተፈትሾ በጤና ሙያተኞች ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባር ታማኝነትን ያተረፉና ወረርሽኝን መምራት የሚያስችል የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸው አመራሮች ወደፊት ማምጣት በበሽታው የሚመጣውን አደጋ ለመቀልበስ አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን አጥብቀን እንመክራለን፡፡ ይህንን ማድረግም ከአገር ወዳድና ለሕዝብ አለኝታ ከሆነ መሪ የሚጠበቅ ነው፡፡

በአጠቃላይ ስናየው አሁን ያለው ክፍተት የመጣው በአገራችን ብሎም በከተማችን የተጀመረው ሪፎርም ገና ጅምር በመሆኑና ዳር ለማድረስ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሴክተሩ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ከጅምሩ የተጠለፉ በመሆናቸው ሪፎርሙን የማዳን እንደአንድ ተግባር ተደርጎ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፡፡

አሁን በሥራ ላይ የሚገኘውና አገራዊ ለውጡ ያልጎበኘው፣ የከተማ አስተዳደሩ ኮሮናን ለመከላከል የሚያደርገውን መጠነ ሰፊ ጥረት የሚያመክን ነውና ጉዳዩን በጥንቃቄ በማየትና ተገቢውን ምልከታ በማድረግ የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወስዱ ምክራችንን እንለግሳለን።

ይህን በማስተካከል የጤና ባለሙያው ለከተማው ኅብረተሰብ ቤት ለቤት ድረስ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላትና ከሕዝባችን ጋር በጋራ በመሆን የሚታይና ተጨባጭ የሆነ ሥራ እንድናደርስ ያስችለናል፡፡

መልካሙን ሁሉ ለከተማችን፣ ለአገራችን ብሎም ለዓለማችን ሕዝቦች እንመኛለን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡(ምንጭ:-ሪፖርተር ጋዜጣ)

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top