ጠቅላዬ አሳዘኑኝ፤ ለመሆኑ አገሪቷ የኮምኒኬሽን ባለሙያ አላት እንዴ?
(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ “ከኮምኒኬሽን ባለሙያዎች” ጋር ትላንት ምክክር እንደነበራቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ነግረውናል፡፡ መቼም ምክክር አይጠላም፡፡ ነገርግን የመንግሥት ተቋማት የኮምኒኬሽን ባለሙያዎች (የጤና ዘርፉን ጨምሮ) አብዛኛዎቹ ከዘርፉ ጋር ትውውቅ የሌላቸው፣ ከሙያው ይልቅ ካድሬነታቸው የሚያመዝንባቸው መሆናቸውን ጠቅላዬ መዘንጋታቸው ግርም ቢለኝ ይህችን ማስታወሻ ልጭር ተነሳሁ፡፡
በቅድሚያ ጠቅላዬ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ባነጋገሩበት ወቅት ያስተላለፉትን ንግግር ላስቀድም፡፡ “አንድ ወታደር ህይወቱን ሰውቶ አገር እንዳስቀጠለው ሁሉ የኮምንኬሽን ሙያተኞችም ስለ ኮሮና ቫይረስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለህዝቡ ትክክለኛና የሚያስፈልገውን መረጃ በመስጠት ህዝቡን ከቫይረሱ መታደግ ይችላሉ” ነበር ያሉት፡፡ በእኔ ምልከታ አባባሉ እንከን የማይወጣለትና ትክክለኛ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ “ከኮምኒኬሽን ባለሙያዎች” ጋር ትላንት ምክክር እንደነበራቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ነግረውናል፡፡ መቼም ምክክር አይጠላም፡፡ ነገርግን የመንግሥት ተቋማት የኮምኒኬሽን ባለሙያዎች (የጤና ዘርፉን ጨምሮ) አብዛኛዎቹ ከዘርፉ ጋር ትውውቅ የሌላቸው፣ ከሙያው ይልቅ ካድሬነታቸው የሚያመዝንባቸው መሆናቸውን ጠቅላዬ መዘንጋታቸው ግርም ቢለኝ ይህችን ማስታወሻ ልጭር ተነሳሁ፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር ሆይ፤ መሬት ያለውን፣ ተጨባጩን እውነታ መመዘን ካልቻልን ስለሕዝብ ግንኙነት እና ባለሙያዎቹ ማውራት አንችልም፡፡ ለድፍረቴ ከፍተኛ ይቅርታ እየጠየኩኝ ከእርስዎ ቢሮ ጀምሮ የኮምኒኬሽን እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራው ባለሙያ የራቀው ነው፡፡ እርስዎም እንደሚያስታውሱት በአንድ ወቅት እነአቶ በረከት ሰምኦን “ለገጽታ ግንባታ ትኩረት መስጠት አለብን” በሚል ካድሬዎችን ከገጠር ወረዳዎች ጭምር እየሰበሰቡ በለብለብ ሥልጠና “ከዛሬ ጀምሮ የኮምኒኬሽን ባለሙያዎች ሆናችሃል” እያሉ በፌደራል ተቋማት መደቡ፡፡
ብዙዎቹ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች እንዴት መረጃ መሰብሰብ፣ እንዴት መረጃን መተንተንና መጻፍ፣ እንዴት ከሚዲያ ጋር ግንኙነት አድርጎ ማሰራጨት፣ ፕሬስ ኮንፈረስ መቼና እንዴት ማዘጋጀት፣ ከሚዲያዎች የሚቀርቡ የማያቋርጡ የመረጃ ፍላጎቶችን በምን መልክ ማስተናገድ እንዳለባቸው ዕውቀትና ክህሎቱ አልነበራቸውም፡፡ ችግሩ እነዚህ ወገኖች ትልቅ ትምህርት፣ ክህሎት፣ ልምድ የሚጠይቀው ሙያ ላይ መመደባቸው ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹ የተመደቡበትን የሥራ ዘርፍ እንግዳ መሆናቸው፣ በሒደትም በገጠማቸው ቻሌንጅ ብዙዎቹ እጃቸውን ሰብስበው መቀመጣቸው በጥቅሉ የመንግሥትን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አፈር አብልቶታል፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር ሆይ እነዚህን ካድሬነታቸው የሚያመዝንባቸው የሕዝብ ግንኙነት ወይንም የኮምኒኬሽን ባለሙያዎች ይዞ እንደወታደር ማገልገል እንደምን ይታሰባል?
ክቡርነትዎ ያው እርስዎም እንደሚታዘቡት በኮሮና ቀርቶ በህዳሴ ግድብ ከግብጽ ጋር ከገባነው አተካሮ ጋር ተያይዞ የግል አስተያየቱን አንኳን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ወጥቶ የሚሰጥ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የለንም፡፡ ይኸም ቅንጦት ነው ይቅር፤ በአገር ውስጥ ቋንቋዎች በሚታተሙ ጋዜጦች፣ የብሮድካስት ሚዲያዎች እንዲሁም ማህበራዊ ድረገጾች ላይ ፊት ለፊት ወጥቶ በሳል ትንታኔዎችን በመስጠት የወገኑን ንቃተ ሕሊና እንኳን ለማዳበር የበቃ የሕዝብ ግኙነት ባለሙያ ስለመኖሩ ሰምተው ያውቃሉን? እንዲህ ዓይነት ብቃት ያለው፣ መረጃን አስቀድሞ በመስጠት የአጥቂነት ሚና የሚጫወት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አገሪቷ የላትም፡፡
በተቃራኒው ጥቂት ከሚዲያ ጋር ቀረቤታ ያላቸው እና ጋዜጠኛ የሆኑ ግለሰቦች ብቻ በራሳቸው ተነሳሽነት ደጋግመው ስለኮሮና ቫይረስ እንዲሁም ኢትዮጵያ ሳትፈልግ ከግብጾች ጋር ፍልሚያ ስለገባችበት ሁኔታ አስረጂ ሆነው ሲባዝኑ ደጋግመን እያየን ነው፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎቻችንን በትምህርትና ክህሎት ያደጉ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ ቢሆኑ ኖሮ እርስዎ እንዳሉት የአባይ ጉዳይንም ጨምሮ በኮሮና ቫይረስ ጉዳይ እጅግ የላቀ ሚና መጫወት በቻሉ ነበር፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር ሆይ እንደወታደር አገርን መከላከል የሚችሉ ብቃት ያላቸው የኮምኒኬሽን ባለሙያዎች ማፍሪያ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ከራስዎ ቢሮ ጀምሮ ለካድሬዎች ተገቢውን ሌላ ምደባ በመስጠት የኮምኒኬሽን ቦታዎችን ለባለሙያዎች ክፍት ያድርጉ፡፡ በመንግሥት ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሥራ ከካድሬ ሥራ በመለየት በሜሪት ብቻ ቅጥርና ምደባ ያካሂዱ፡፡ ያኔ እንደተመኙት እንደወታደር አገርን መከላከል የሚችል ባለሙያ ማፍራት ይችላሉ፡፡