ከዐረብ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ግለሰብ ትናንት በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሲመረመር ትኩሳት ታይቶበት ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ ጥርጣሬ ያደረበት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ግለሰቡ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግ ወስኗል፡፡
ይሁን እንጂ ግለሰቡ ትናንት ምርመራውን ሳያደርግ አምልጦ ዛሬ ወደ ደቡብ ወሎ በመጓዝ ላይ እያለ ነው ደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ የተያዘው፡፡ ግለሰቡ በቫይረሱ ስለመጠቃቱ ወይም ከቫይረሱ ነፃ ስለመሆኑ በሕክምና አልተረጋገጠም፡፡
ይህንን ለማረጋገጥ ምርመራ እንዲያደርግ በተፈለገበት ጊዜ አምልጦ ነው በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ወደ ቤተሰቦቹ ሲሄድ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዞኑ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ፈጣን ክትትልና የመረጃ ልውውጥ የተያዘው፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ፈንታነሽ ታመነ ለአብመድ በስልክ እንዳስታወቁት በአውቶቡሱ አብረው የተጓዙ ተሳፋሪዎችም ለጊዜው በሆስፒታል እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡
የአካባቢው ማኅበረሰብ በሁኔታው መደናገጡን ያስታወቁት የመምሪያ ኃላፊዋ በቫይረሱ ስለመጠቃቱ ጥርጣሬ ቢኖርም ግለሰቡ ተጠቅቷል ማለት አለመሆኑን በመገንዘብ ከመደበኛ ሠራው እንዳይነጠል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ከሌሎች ሀገራት የሚገቡ ሰዎችን ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥርጣሬ የታየባቸው ሰዎችን በማግለያ እንዲቆዩ ያደርጋሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ጃፓናዊ ጎልማሳ በኮሮና ቫይረስ መያዙን ከማረጋገጡ ውጭ ተጨማሪ ተጠቂዎች መገኘታቸውን አላሳወቀም፡፡
ኅብረተሰቡ ግን አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ የግልና የአካባቢ ንጽሕናውን እንዲጠብቅ፣ ለቫይረሱ የሚጋልጡ ልምምዶችን እንዲቀንስ መልእክት ተላልፏል፡፡
ጥርጣሬ የታየባቸውን ሰዎች ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ በማድረግ በኩልም ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድና ማንኛውም ሰው ሪፖርት እንዲያደርግም በተደጋጋሚ ጥሪዎች እየቀረቡ ነው፡፡ ሰዎች በራሳቸው ላይ የተለዬና አጠራጣሪ የጤንነት ሁኔታ ሲያዩ ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱና በሽታውን ወደ ሌላ ሰው ላለማስተላፍ ኃላፊነት የተሞላበት ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ይመከራል፡፡
ምንጭ:- አብመድ