“ዳዊት ግን ይገባዋል” አርቲስት አብርሃም ወልዴ
ይገባዋል፤ አለማሳካትን የሚያኽል ጎልያድ በብርታቱ ጠጠር ጥሏልና” እኔ በሙዚቃ አልበሙ ምረቃ ምሽት
****
ሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
የሚገባው ሰው ስራ ምረቃ ላይ ታድሜያለሁ፡፡ አዲስ አበባ፤ ራስ ብሩ ሰፈር፡፡ ማርዮት ሆቴል፡፡ ስፍራው ሞልቷል፡፡ ብዙውን ሰው በዓይኔ አውቀዋለሁ፡፡ ብዙው ሰው ባለ ስም ነው፡፡ ብዙው ሰው ዝነኛ ነው፡፡ ዝናን በጥረቱ የገዛው ዳዊት ሰውን እንዲህ ሰብስቦታል፡፡
የዳዊት ጽጌን የኔ ዜማ የሙዚቃ አልበም ምረቃ መጀመር እየጠበቅን ነው፡፡ መድረኩ ላይ የአብርሃም ወልዴ የአብረሃም እድሜ የሚቸራቸው የባለሃገር ሙዚቃዎች ይሰማሉ፡፡ ደስ የሚል ምሽት እንደሚሆን ገመትኩ፡፡ እርግጥ እንዲህ ላለው ስፍራ ባዕድ ነኝ፡፡ ነፍሴ ደስ አይላትም፡፡ የገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥም ትዝ አለቺኝ፡፡
“ለሚወዱት ምነው?”
ለምወደው ስራ፣ ለወደድኩት ዘፋኝ፤ ላከበርኩት ጥበብ ብዬ ታድሜያለሁ፡፡ ከተቀመጠው የቆመው ይበልጣል፡፡ መቆም መልካም ሆነ፤ ሙሽራው ታጅቦ መግባት መጀመሩ ተነገረን፤ ስላልተቀመጥሁ መነሳት አላስፈለገኝም፡፡ ቀና ብዬ አየሁ፡፡ አበበ ብርሃኔ፣ ዳዊት ጽጌ፣ አብርሃም ወልዴ፣ በረከት መንግስተ አብ……ዳዊት ታጅቦ ገባ፡፡
ምሽቱ ድባቡ ተቀየረ፡፡
መድረክ መሪዋ ገጣሚዋ ረድኤት ጥሩ ጥሩ ገለጻዎች ነበሯት፡፡ ግን የምሽት ድምጽ ይዋጣል፡፡ ሊያውም ሆቴል፣ ሊያውም እየተጎነጩ፤
አርቲስት አብርሃም ወልዴ ወደ መድረኩ ወጣ፡፡ ንግግሩን ሸጋ ነበር፡፡ ምስክረነቱን ሰጠ፡፡ አብረሃም ቁጥብና ትሁት ሰው ነው፡፡ ቀና ብሎ የመሰከረለትን ስራ አወደሰ፡፡ ከቃሉ ሁሉ አንዷ ገዘፈችብኝ፡፡
“ዳዊት ግን ይገባዋል፡፡” አለ፡፡
እርግጥ ነው ዳዊት ይገባዋል፡፡ እኔም እላለሁ፡፡ ዳዊት በጥረቱ አለመድረስን የሚያህል ጎልያድ በብርታቱ ጠጠር የጣለ ሰው ነው፡፡ እናም ይገባዋል፡፡ ዝናውና ክብሩ የስራው ውጤት ነው፡፡ የትም ኖሮ የትም መከበር የቻለ ነው፡፡ በመጥፋት ያልተወደደ፣ በመራቅ ያልተናፈቀ፤ በመቅረብ ያልተሰለቸ ሰው ነው፡፡ ከጥላሁን ገሠሠ በኋላ የትም ኖሮ የትም መወደድ የጀመረ ዘፋኝ እያገኘን ይሆን ብዬ አስብኩ፡፡
ይሄንን ሳስብ ነው፤ መድረኩን በሙሐሙድ አህመድ ዜማ አንድ ድምጻዊ የነገሠበት፣ ይሄንን ሀሳብ ሳውጠነጥን የሴት ከያኒያን መድረኩን ነግሠውበት ነበር፡፡ ስለ ዳዊት እያሰብሁ፤ ከሩቅ እንደሚፈስ ድምጽ የፍቅረ አዲስ ምስክር ዜማ ከራሷ ሲስረቀረቅ ይሰማኝ ነበር፡፡ እንዲህ እያሰብኩ ዓይኖቼ መድረኩ ላይ የኩኩ ሰብስቤን ድንቅ አቀራረብ አየሁ፡፡ የበረከት መንግስተ አብ ክራር ከድምጹ ጋር ያስገመግም ነበር፡፡