በኢትዮጵያ፣በሱዳን እና በግብጽ መካከል በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅን በተመለከተ የረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለመፈረም ሲያካሂዱት የነበረው ድርድር ሳይቋጭ ተጠናቋል፡፡
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገጻቸው እንዳስታወቁት በአገራቱ መካከል እኤአ ከፌብሩዋሪ 12_13/2020 በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በግድቡ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅን በተመለከተ ሲያካሄዱት የነበረው ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ዝግጅት ሳይቋጭ ተጠናቋል፡፡
—
የህዳሴው ግድብ ድርድር ትኩረቱን ስቶ የውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ ሆኗል ተባለ
በሱዳን በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የቆየው የህዳሴ ግድብ ድርድር ትኩረቱን ስቶ ወደ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ መሄዱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።
እኚህ ምንጫችን ሱዳን የአቋም ለውጥ አድርጋ ከግብጽ ጋር መወገኗን እንዲሁም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለግብጽ መወገናቸውን በመጠቆም አሁን ላይ ጉዳዩ “4 ለ 1″ ሆኗል በማለት ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
አሜሪካ እና ዓለም ባንክ በግድቡ ዙሪያ እጃቸውን እንዲያስገቡ መፈቀዱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል እያደረጋት እንደሆነ እኚህ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ውስጥ አዋቂ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ ከሁለት ቀናት በፊት ተደራዳሪ ቡድኑ ”በብዙ ጉዳዮች ላይ የመከረ ቢሆንም ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ ማዘጋጀት አለመቻሉ ታይቷል” ብለው ነበር።
ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት የሰነዱ አብዛኛው ክፍል የቀረበው በአሜሪካ በመሆኑ፤ ትኩረቱም ስለ ግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በመሆን ፈንታ፤ “ማን ምን ያህል የውሃ ድርሻ ይኑረው? የሚለው ላይ የሚያተኩር በመሆኑ” ከስምምነት መድረስ እንዳልተቻለ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት እኚህ ባለሙያ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
አክለውም በግድቡ ጉዳይ የኢትዮጵያ የህግ አርቃቂ ቡድን አሁንም አሜሪካ እንደሚገኝ በማስታወስ፤ በውሃ ክፍፍል ላይ ለመነጋገር እንደ አገር ዝግጁ አይደለንም፤ የድርድሩ አላማም ይህ አይደለም ብለውናል።
እሳቸው እንደሚሉት ከግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ጋር በተያያዘ በድርቅ፣ በረዥም ጊዜ ድርቅ እና በተከታታይ ድርቅ በሚሉት በሰነዱ ላይ በሰፈሩት ቃላቶች ትርጓሜ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።
ስለዚህም የኢትዮጵያ የህግ አርቃቂች በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሰነዱ ላይ የሰፈሩ በርካታ ነጥቦችን በጥያቄ ምልክት ውስጥ ለማስቀመጥ ተገድደዋል።
“ትልቁ ነገር ሰነዱ የውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ ሊያተኩር አይገባም ነበር። ወደ አሜሪካ የሄደው የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ቡድንም በዚህ ላይ [የውሃ ድርሻ ክፍፍል] ለመነጋገር ስልጣን አልተሰጠውም። ስለ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ኢትዮጵያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ብቻ ሳይሆን ከአስሩም የተፋሰሱ አገራት ጋር ነው መነጋገር ያለባት” ይላሉ።
ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍን ፈርማ ያፀደቀች አገር መሆኗን እና ይህ ስምምነት ሳይጣስ ሁሉም የተፋሰሱ አገራት ባሉበት መነጋገር እንደሚገባት ያስታውሳሉ።
ታዛቢ ወደ አደራዳሪ
ሶስቱ አገራት በሚያደርጉት ድርድር ላይ የሶስተኛ አካል ጣልቃ መግባት ይኖርበታል ብላ ሃሳብ ያቀረበችው ግብጽ መሆኗ ይታወቃል። ፕሬዝደንት አብዱል ፈታ አል ሲሲ አሜሪካ በጉዳዩ ላይ ታሸማግለን ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ኢትዮጵያ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን እንደማትቀበል ገልጻ ነበር። ለዚህም እንደምክንያትነት ያስቀመጠችው በሶስቱ አገራት የተደረሱ ”አበረታች” ስምምነቶችን ያፈርሳል እንዲሁም ሶስቱ አገራት እአአ 2015 ላይ የፈረሙት የመርህ ስምምነትም ይጥሳል የሚል ነበር።
የኋላ ኋላ ግን ዓለም ባንክ እና አሜሪካ በሶስቱ አገራት መካከል በሚደረጉ ውይይቶች ላይ የታዛቢነት ሚና ኖሯቸው ይሳተፋሉ ሲባል ቆየ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ጥር 25 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ የአሜሪካ መንግሥት እና ዓለም ባንክ ‘ለማደራደር’ ጥያቄ አቅርበው ‘ሲያደራድሩ’ ቆይተዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ “ለአሜሪካ እና ዓለም ባንክ ምስጋና ማቅረብ የሚያስፈልገው፤ በሚያውቁን እና አቅም ባላቸው ፊት ስንነጋገር መስማማት ጀምረናል” ሲሉም ተደምጠዋል።
እኚህ የቢቢሲ ምንጭ እንደሚሉትም የአዲስ አበባ የመጀመሪያው ስብሰባ ላይ በታዛቢነት ተቀመጡ፣ ካይሮ ላይ በታዛቢነት ቀጥለው ሱዳን ካርቱም ላይ ግን አደራዳሪ ሆኑ። ከዚያም ተመልሰው አዲስ አበባ ላይ አደራዳሪ መሆናቸውን ቀጠሉ።
“አሁን እኮ ዋሽንግተን ላይ የሕግ እና የቴክኒክ ቡድኑ ተገኝቶ፤ ሰነድ ቀርቦ ግልፅ ድርድር ነው እየተካሄደ ያለው” በማለት ያስረግጣሉ።
እነዚህ አካላት ከታዛቢነት ራሳቸውን ወደ አደራዳሪነት ከማሸጋገራቸውም በላይ ኢትዮጵያ ላይ “ከፍተኛ ጫና ማሳደርና ማስፈራራትም ደረጃ ደርሰዋል” ይላሉ ባለሙያው።
እርሳቸው እንደሚሉት አሜሪካና አለም ባንክ በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በኩል የሚነሱ ሃሳቦችን ለመቀበል በፍጽም ፍላጎት አያሳዩም። ይልቁንም እየተቀበሉ ያለው የግብፅና የሱዳንን ሃሳብ ብቻ ነው።
በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ከመጀመሪያ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለራሷ ጥቅም ስትል ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ የነበረችው ሱዳን አቋሟን ቀይራ ከግብፅ ጎን መሰለፏንም ያረጋግጣሉ።
እሳቸው እንደሚያብራሩት በአሜሪካ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳላት የምትፈልገው ሱዳን ይህን ፍላጎቷን ይዛ ስትመጣ አሜሪካ በበኩሏ በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች።
ምናልባትም የሚሉት እኚህ ምንጭ ከትናንት በስቲያ እንደተሰማው የቀድሞውን የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አል-በሽርን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፎ መሰጠት ሱዳን ያሟላችው አንድ ቅድመ ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ከግብፅ ጎን መቆም ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ ሲሆን ይህንንም ሱዳን እየፈፀመች ነው።
“ሶስተኛ ወገን ማስገባት ካስከፈለው ከባድ ዋጋ አንዱ ይሄ ነው” በማለት ድርድሩ ለኢትዮጵያ አጣብቂኝ መንገድ ላይ እንዳለ ይገልፃሉ።
አሜሪካ ለግብጽ ለምን ወገነች?
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ሰላም ለብልጽግና [ፒስ ቱ ፕሮስፔሪቲ] የተሰኘውን የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅዳቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይህ የትራምፕ እቅድ እየሩሳሌም ያልተከፋፈለች የእስራኤል መዲና ትሆናለች ከማለቱም ባሻገር ፍሌስጤማውያን እና የተቀረው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሕገ-ወጥ የሚለውን የእስራኤልን የዌስት ባንክ ሰፈራ እውቅና ይሰጣል።
ይህ የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ በፍልስጤማውያን ወዲያው ውድቅ የተደረገ ሲሆን እንደ ኢራቅ እና ሶሪያ ያሉ የሰላም እቅዱን በይፋ ከተቃወሙት አገራት መካከል ይገኙበታል።
ቀላል የማይባሉ የአረቡ ዓለም አገራትም የትራምፕን የሰላም እቅድ በጥርጣሬ ዕይን መመልከታቸው አልቀረም። ታዲያ በአረቡ ዓለም ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነችው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ግብጽ፤ የትራምፕ ዕቅድ በአረቡ አገራት ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ የሆነ የራሷን አስተዋጽኦ ልታበረክት ትችላለች።
እኚህ የቢቢሲ ምንጭ እንደሚሉት፤ የፕሬዝደንት ትራምፕ እቅድ እንዲሰምር ግብጽ የበኩሏን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ልታበረክት ትችላለች።(© BBC)