Connect with us

ቀጭኔዎቹ የት ገቡ?

ቀጭኔዎቹ የት ገቡ?

መዝናኛ

ቀጭኔዎቹ የት ገቡ?

ቀጭኔዎቹ የት ገቡ?
ገራሌ ብሔራዊ ፓርክ-የጠረፉ ዳሩ ድንቅ ውበት፤
****
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የገራሌ ብሔራዊ ፓርክ ቆይታውን እየተረከልን ነበር፡፡ ቀጭኔዎቹን ፍለጋ ሄዶ የገጠመውን ድንቅ የተፈጥሮ ሀብት የጠረፉ ዳሩ ድንቅ ውበት ሲል እንዲህ ያካፍለናል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

በጠዋት ተነሳን፡፡ እንደወታደር ተሰልፈን በእግር ጉዞው ቀጠለ፡፡ እኔ ከፊት ሦስተኛው ነኝ፡፡ መንገዱን የሚመራው ከሙባረክ የያዝነው የሚኒሺያ ኃላፊ ነው፡፡ ይፈጥናል፤ ግን ተከትለነዋል፡፡ ቀጭን የእግረኛ መንገድ መሳይ ጎዳና ይዘን እየገሰገስን ነው፡፡

የወፉ ድምጽ ተአምር ነው፡፡ ዓይነቱም እንዲሁ፤ ዥግራው መሬት ወርዶ መንገድ ዘግቷል፡፡ ላባዋ የሚማርከው ወፍ ዓይነቷ ብዙ ነው፡፡ 250 የሚሆን የወፍ ዝርያ መኖሪያ ነው፡፡ ቄንጠኛ ወፎች በየዛፉ ተንጠልጥለው ትርኢት ያሳዩናል፡፡ ይህ ገራሌ ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡

መንገድ ተአምር ያሳየናል፡፡ መሻታችን ግን ቀጭኔን ነው፡፡ እዚህም እዚያም ብዙ እንስሳ ይታያል፡፡ ዳልጋ አንበሳ ሲያቋርጠን ቀጭኔ ፍለጋ የምንጣደፍ ስለነበርን አልተገረምንም፡፡ ሳላው ብዙ ነው፡፡ ሜዳውን ሰጎን ይዘንጥበታል፡፡ ድንገት ዘለው የሚያስደነግጡን ጉጉፍቱዎች ናቸው፡፡ ሜዳ ፍየል ሜዳው ተመችቷታል፡፡ አጋዘኑ ደርሶ ጉብ ይላል፡፡ አርባ ሁለት የሚደርስ አጥቢ የዱር እንስሳ ዝርያ የተመዘገበበት ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡

ነብር፣ አንበሳ፣ ዝኆን፣ ተኩላ፣ የዱር ድመት መኖሩ ተነግሮናል፡፡ አውራሪስ አየሁ ያለ ሰው አብሮን እየተጓዘ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ያጓጓን ቀጭኔ ነው፡፡

መንገድ መሪው ድንገት ቆመ፡፡ አብረን ቆምን፡፡ መሬት ላይ ዓይኑን ተክሎ አንዳች ነገር ሲፈልግ ያየውን አብረን አየን፡፡ የቀጭኔ ዳና፣ ትኩስ የቀጭኔ ዳና፡፡ ፍጥነት ጨመረ፤ ተከተልነው፡፡ ዳናው ሰውዬውን እኛ ሰውዬው እየመሩን ተከታተልን፡፡

ጠዋት ቢሆንም ይሞቃል፡፡ የብሔራዊ ፓርኩ ቆዳ ስፋት 1734 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ድንገት ቀጭኔዎቹ ድምጻችንን ሰሙ፡፡ የሩጫቸው አቧራ ታየ፡፡ ዳናቸው ጋር ስንደርስ ምድሩን ቆፈረው በረዋል፡፡ ተበትነን ፈለግናቸው፡፡ ፈጥኖ የተከተለው መንገድ መሪ ያነሳው ምስል የማይሆን ነበር፡፡ ከቀጭኔዋ ይልቅ ያቦነነችው አቧራ ጎልቶ ይታያል፡፡

ደስ ብሎናል፡፡ ቀጭኔዎቹ አሉ፡፡ የት ገብተው ይሆን ለሚል ገራሌ ለብዙ ቀናት ማሰስ ይኖርበታል፡፡ አልያም ውሃ ዳርቻዎች ማድፈጥ፤ ያዩ ሰዎች ሲጠቁሙም ቁጥራቸው ስድስት መሆኑን ነግረውናል፡፡ ከቀናት በፊት ተመለከትኩ ያለ ሰው ደግሞ ሰባት ናቸው ብሏል፡፡ ሰባት ሆነን ገብተን አንዳችንም በካሜራችን ሳናስቀራቸው፤ ወይም በዓይናችን ሳናያቸው ተመለስን፡፡ የጠረፉ ዳሩ ውበት ድንቅ የተፈጥሮ ቅርስ ነው፡፡ አንድ ቀን የገራሌ ቀጭኔዎችን አሳያችሁ ይሆናል፡፡

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top