የረሃብ አለንጋ በቅርብ ርቀት እየጠበቀን ነው
አብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል
(Email: ahayder2000@gmail.com)
ብዙዎች እንደሚስማሙት ይህ ወቅት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ትልቅ የፈተና ወቅት ነው፡፡ መሻገራችን አይቀርም፡፡ እስከምንሻገረው ግን ብዙ መስዋእትነት ያስከፍለናል፡፡
ሰሞኑን በሀገራችን በርካታ ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡ ከነዚህ ክስተቶች ውስጥ አንዱ የሰደድ እሳት ነው፡፡ ሰደድ እሳቱ የተነሳው ደግሞ የትግራይ ክልል ብቸኛ ፓርክ በሆነው “በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ” ላይ መሆኑ በመገናኛ ብዙሃን ተነግሯል፡፡ ለትግራይ ክልል “አንድ ለእናቱ” እንደሆነ የሚነገርለት ይኸው ፓርክ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የተከለለና የቱሪስት መዳረሻ እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ የእሳት ሰለባ መሆኑን ሰማን፡፡
ተፈጥሯዊ አደጋዎች “በህግ አምላክ” ተብለው የሚገቱ አይደሉም፡፡ ጥፋታቸውም የከፋ ነው፡፡ ለመከላከል የሚወስደው ጊዜና ጉልበት ብዙ ነው፡፡ … ህዝብን ያንገላታው ሰደድ እሳት ብቻ አይደለም፡፡ የውኃ ሙላትም ያጥለቀለቃቸው አካባቢዎች ነበሩ፡፡ በሶማሌ ክልል ጎርፍና የውሃ ሙላት በሰውና በንብረት ላይ የከፋ አደጋ እያደረሰ መሆኑንም ሰምተናል፡፡ እዚያም አዝመራ እየወደመ ነው፡፡
የአንበጣ መንጋ ሰሞኑን ትኩረት ከሳቡ ሀገራዊ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ መነሻውን ሶማሊያ እና የመን ያደረገ የአንበጣ መንጋ ወደ ሀገራችን ከገባ ቀናት ሳይሆኑ ሳምንታት መቆጠር ጀምረዋል፡፡ ይህ አውዳሚ የሆነ የአንበጣ መንጋ በትግራይ፣ በአፋር፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ታይቷል፡፡ ለአጨዳ በደረሰ አዝመራ ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ነው፡፡
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ሰው ሰራሹም ተፈጥሯዊም አደጋ ተጋርጦብናል፡፡ በበኩሌ ክፉ ስራችን ፈጣሪን እንዳስቆጣ አስባለሁ፡፡ በእሳትም፣ በውኃም፣ በአንበጣም እየቀጣን ያለው ለዚሁ ይመስለኛል፡፡ ተጸጽተን ከክፉ ተግባራችን ካልተመለስን ቅጣቱ በእሳትና በውኃ አሊያም በአንበጣ መንጋ የሚቆም መስሎ አይታየኝም፡፡ የርሃብ አለንጋ የተዘጋጀልን መሆኑም በርቀት ይታያል፡፡ ከፊት ለፊታችን የተደቀኑ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በመቃኘት መጪውን ጊዜ መተንበይ እንችላለን፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት (ማለትም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ) በሀገራችን ከጫፍ እስከ ጫፍ አለመረጋጋት ነበር፡፡ ሁከት ነበር፡፡ መንገድ መዝጋት፣ ንብረት ማውደም፣ ሰው መግደል … በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የኢንቨስትመንት አዝመራ ጭምር በእሳት ጋይቷል፡፡ ፋብሪካዎች ተቃጥለዋል፡፡ ትኩስ የሥራ ኃይል የሆነው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ለተቃውሞ ወደ ጎዳና በመውጣቱ ሥራ አልተሰማራም፡፡ በዚህም ምክንያት የአርሶ አደሩ ማሳ ጦሙን ማደሩ ታይቷል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ኢኮኖሚውን ክፉኛ አድቅቆታል፡፡ የዋጋ ንረቱን አባብሷል፡፡
በከተሞች ብዙ የስራ እድል ፈጥረው የነበሩ የመንገድ ፕሮጄክት፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጄክት፣ የኮንዶሚንየም ቤቶች ግንባታ ፕሮጄክት ከሞላ ጎደል ቁመዋል፡፡ አዳዲስ የመንግስት ግንባታዎች ተገትተዋል፡፡ በሀገሪቱ የነበሩ ኢንቨስትመንቶች ባለፉት 5 ዓመታት እየተዳከሙ መጥተዋል፡፡ ብዙዎቹ በሰላም መታጣት ምክንያት ተዘግተዋል፡፡ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ቢሯቸውን ዘግተው ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ሁኔታው ሲረጋጋ ቢመለሱ እንኳ የወደመውን ንብረታቸውን አስልቶ መንግስት ካሳ እንዲከፍላቸው ከመጠየቅ በዘለለ ደግመው ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡ አይመስሉም፡፡ ቢገቡም ቀጥታ ወደ ምርት ማምረት ሳይሆን የተቃጠለን መልሶ በማቋቋም ላይ እንደሚያተኩሩ የሚጠበቅ ነው፡፡
በያዝነው ዓመት ሀገራዊ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በግሌ ይህ ምርጫ ሰማንያ በመቶ አይካሄድም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ፡፡ ከተካሄደ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፖለቲከኞች የሚፈጥሩት ግለት የህዝብን ስሜት ከመለኪያ በላይ ያወጣዋል፡፡ በዚህም መዋከብ ምክንያት መደበኛ ስራ መስራት የምንችልበት ሁኔታ የሚኖር መስሎ አይታየኝም፡፡
ምርጫው ካልተካሄደም ሌላ አጣብቂኝ የፖለቲካ ሁኔታ ይከሰታል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይኸውም፡- ፓርላማው የስራ ዘመኑን ይጨርሳል፡፡ እናም ምርጫው እስኪፈጸም የሽግግር መንግስት ይቋቋማል ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፤ የሽግግሩ ጊዜ በእነማን ይቋቋም? የሽግግሩ አባላት እነማንን ያካትት? በምን መስፈርት ይመረጡ? የሽግግሩ ዘመን ስንት ዓመት ይሁን? በሽግግሩ ጊዜ ምን ይሰራ? ህገ መንግስቱ በሽግግሩ ጊዜ ይሻሻል?… የሚሉ በርካታ ፈታኝ ጥያቄዎች ፊት ለፊታችን ተደቅነዋል፡፡
ፖለቲከኞቹ በነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ሰፊ ንትርክ እንደሚያደርጉ የሚገመት ነው፡፡ ሶሻል ሜዲያውና አክቲቪስቶች ይህንን ንትርክ በስፋት በማራገብ ህዝቡን እንደሚያንገላቱት የሚጠበቅ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መደበኛ ስራ የሚሰራበት ሁኔታ አይኖርም ብዬ አስባለሁ፡፡
መደበኛ ስራ ካልተሰራ፣ ምርት ካልተመረተ፣ ፋብሪካዎች ካልተንቀሳቀሱ፣ ኢንቨስትመንቶች ካልተስፋፉ የደቀቀው ኢኮኖሚ ይብስ ይደቃል፡፡ ለስራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ካልተፈጠረ ሁከትና መንገድ መዝጋት ይቀጥላል፡፡ ወደ ገበያ የሚወጣ ምርት አይኖርም፡፡ ከእሳት፣ ከጎርፍና ከአንበጣ መንጋ ተርፋ የተሰበሰበች ምርት እንኳን ወደ ገበያ ልትቀርብ አርሶ አደሩን መመገብ የምትችል መስላ አትታየኝም፡፡ በፖለቲከኞች ውዝግብ የሚታመሰውና በሶሻል ሜዲያ የሚላጋው ከተሜ ለእለት ጉርሱ የሚሸምተው እህል ገበያ ላይ ስለማግኘቱ አላህ ይወቅ፡፡ የርሃብ አለንጋ በያንዳንዳችን ቤት ግድግዳ ላይ ተሰቅላ ትታየኛለች የምለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ዛሬ ብዕሬ ጨለምተኛ ሃሳብ መክተቧ ያልተለመደ ነው፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ከፊት ለፊታችን ድቅድቅ ጨለማ መኖሩ ነብይነትን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ “ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል” የሚለውን ብሂል እያስተጋባን በተስፋ መጠበቅ ትርጉም የሚኖረው ነገሮችን ቀድመን አስተውለን አንዳንድ ሁኔታዎችን ከወዲሁ ማስተካከል ከቻልን ብቻ ነው፡፡