የአዳማው ውሎዬ | የጋዜጠኛው ማስታወሻ
ከትላንት በስቲያ ለሊቱን የጀዋር መሐመድን “ጠባቂዎቼ ሊነሱ ነው፤ በወታደር ተከብቤአለሁ…” መልዕክት ሳነብ ቆየሁና ማልጄ በአንድ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ የስልጠና መድረክ ላይ ለመገኘት ወደ አዳማ ከተማ አቀናሁ። አዳማ ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ገደማ ስደርስ መንገዶችዋ በተቆጡ ሰልፈኞች ተሞልተው አገኘኹዋቸው። ከመኪና እንደወረድኩኝ በጥድፊያ የንግድ ተቋሞቻቸውን እየዘጉ ከነበሩ አንዱ ጋ ተጠግቼ የሚሆነውን መከታተል ጀመርኩኝ። ተሰላፊዎቹ አብዛኞቹ በአስራዎቹ እድሜ ክልል ያልዘለሉ ወጣቶች ሲሆኑ በእኔ ግምት 99 በመቶ ወንዶች ናቸው። ለከተማው ነዋሪም እንግዳ መሆናቸውን የተረዳሁት አጠገቤ የነበሩ ነዋሪዎችን ካነጋገርኩኝ በኋላ ነው። ሶስት ሆነው በቡድን ሁኔታውን ይታዘቡ የነበሩ ጎልማሶች “እነዚህ የከተማዋ ነዋሪዎች አይደሉም፣ ከሌላ አካባቢ ተጭነው የመጡ ናቸው” አሉኝ
“በምን አወቃችሁ?” አልኳቸው “እትብታችን ተቀበረበት ሀገር እኮ ነው፤ ምን ማለትህ ነው? መጤና ነዋሪ መለየት የሚያቅተን ይመስልሃል?” ተመልከት (ጣታቸውን እየቀሰሩ) በትዝብት እየተመለከቱ ያሉትን ወጣቶች? ለምን ሄደህ አትጠይቃቸውም?” አለኝ አንደኛው በግምት በ40ዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ጎልማሳ፡፡ ሌላኛውም ተመሳሳይ ትንታኔ ሰጠኝ፡፡
እናም ሰልፈኛ ወጣቶቹ “በኦሮምኛ ጀዋር አባታችን ነው” ይሉ ነበር። “ነፍጠኛ” የሚል ቃል ደጋግመው እየጠሩ ይራገሙ ነበር፡፡ በዚያች ደቂቃ ልጆቹ የተነገራቸውን ከማንበልበል በስተቀር ስለጀዋር መሐመድ የሚያውቁት ነገር ይኖር ይሆን እያልኩ አስብም ነበር።
ለሰልፍ የወጡት ልጆች አብዛኛዎቹ ዱላ የያዙ ከመሆናቸው አንፃር ፀብ ሊፈጠር የሚችልበት እድል ሰፊ ነበር። ፖሊሶች ሰልፈኛውን ከማጀብ በስተቀር በወቅቱ የወሰዱት እርምጃ አልነበረም።
እንዲሁ የአዳማን አጭር ዋና አውራ ጎዳና እየጮሁ ሲመላለሱበት ከቆዩ በሀላ ዘረፋ ተጀመረ። ዘረፋው ጣራ ላይ ወጥቶ ለመገንጠል እስከመሞከር የደረሰና የከፋ እንደነበር ከአይን እማኞች ተረድቻለሁ።
ትንሽ ዘግይቶ በወጣቶቹ ድርጊት የተናደዱ የአዳማ ወጣቶች በቁጣ በመውጣታቸው ግጭት ተፈጠረ። እኩለ ቀን ላይ የመከላከያ ሀይል መግባቱ ሰልፈኞች እንዲበተኑና የተዘጋው መንገድ እንዲከፈት ረድቷል። በትላንትናው ዕለት በአዳማ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ መንግሥት ያረጋገጠ ሲሆን የአዳማ ነዋሪዎች ግን የሰሙትን በመናገር ቁጥሩ የበለጠ መሆኑን ሊስረዱን ሞክረዋል፡፡ ግን ከነጻ ወገን ማረጋገጥ ባለመቻሌ ዘልዬዋለሁ፡፡
ከቀኑ 11:00 ሰአት አዳማን ለቀን በፍጥነት መንገዱ ላይ እየተጓዝን ገላን አካባቢ ስንደርስ እንዲሁ መንገድ ተዘግቶ ጠበቀን።
ወጣቶቹ ፈጣን መንገዱን ከዳገት ላይ ቁልቁል ናዳ ድንጋይ በመልቀቅና በአካባቢው በሚገኝ ድልድይ ላይ በመሆን ወደታች ወደመንገዱ የድንጋይ መአት በመወርወር የትራፊክ ፍሰቱን አውከዋል።በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ባሉበት ለመቆም ተገደዋል።
መኪኖቹ በቆሙበት ሰዓት አጋቾቹን ለማየት እንደሞከርነው በግምት ዕድሜያቸው ከ20 በታች የሆኑ ወጣቶች የሚበዙበት መሆኑን ተረድተናል፡፡ በግምት ለግማሽ ሰአት በዚህ ሁኔታ ከተጉላላን በኋላ የመከላከያ ሠራዊት መኪና መምጣቱን በሩቁ የተመለከቱት ወጣቶች አካባቢውን ለቀው በተራሮቹ ላይ እግሬ አውጪኝ ብለው ፈርጥጠዋል፡፡ ወዲያወኑም መንገዱ ተከፍቶ ከእገታ ድነናል፡፡
አንድ የግል ጥበቃ ተነሳብኝ ባለ ግለሰብ መከፋት ምክንያት በዚህ ደረጃ ሀገራችን መታመሷ፣ ሰዎች መሞታቸው፣ ንብረት መውደሙ ከተለያዩ ሚድያ ለስልጠና የተገናኘን ጋዜጠኞችን በእጅጉ አሳዝኖን ነበር። ክስተቱ ምንም እንኳን ሕይወትን ያህል መተኪያ አልባ ዋጋ ያስከፈለ ቢሆንም ማን ከማን ጋር ወግኖ እንደቆመ ቁልጭ አድርጎ ማሳየቱ ለበጎ መሆኑን አንስተን ተወያይተንበታል፡፡ በእርግጥም በመንጋ አስተሳሰብ ተነድቶ መንገድ መዝጋት፣ ሰው መግደልና መጉዳት እንዲሁም ዘረፋ የዘረኞችና ጠባቦች የትግል ስልት መሆኑ በአለም ፊት አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡
የአዳማ ወጣቶች ከጸጥታ ሐይላት ጋር በመቀናጀት ከስርዓት ውጪ የነበሩ ሰልፈኞችን ሥርዓት እንዲይዙ በራሳቸው ተነሳሽነት የወሰዱት እርምጃ ለሌላ አካባቢም መልካም አርአያ የሚሆን ነውና በግሌ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በተቃውሞ ሰልፍ ስም ግድያ፣ ንብረት ውድመትና ዘረፋ መፈጸም በምንም መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ ሠላማዊ ትግል የሚወክል ባለመሆኑ ሠላም ወዳድ ወገኖች ሁሉ አጥብቀው ሊታገሉት ይገባል፡፡
በተረፈ በዚህ ዓላማ የለሽ ግርግር ለሞቱ ወገኖች ቤተሰብና ወዳጆች መጽናናትን እመኛለሁ፡፡