የአስመራና አዲስ አበባ ያልተሄደበት መንገድ….
(እስክንድር ከበደ –ለድሬ ቲዩብ )
የምስራቅና የመካከለኛ አፍሪካ ከ23 ዓመት በታች የእግርኳስ ቡድኖች ውድድር መክፈቻ በኢትዮጵያና በኤርትራ በሔራዊ ቡድኖች ሰሞኑን ተካሂዶ ነበር፡፡ የሁለቱ ቡድኖቸ ወጣት ተጫዋቾች ኢትዮጵያ መንግስትና በኤርትራ አማጺያን ከዐጼ ኃይለስላሴ መንግስት እስከ ደርግ የተካሄዱትን ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ጊዜ አልተወለዱም፡፡
ኢህዴግ አዲስ አበባን ፤ የኤርትራ ሀርነት ግንባር አስመራን ሲቆጣጠሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወጣት በሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ወደ እዚህ አለም አልመጡም፡፡ በባድመ የተካሄደውን ሌላ ደም አፋሳሽ ጦርነት ሲካሄድ ፤ አብዛኛዎቹ ወደ ዚህ ዓለም ለመምጣት እየተንደረደሩ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ለጋ ወጣቶች ያደጉት ኢትዮጵያና ኤርትራ በድንበር ጦርነት እያሉና ማዶ ለማዶ ተፋጠው በ” ጥላቻ ቃላት” ሲወራረፉ ነበር፡፡
የኤርትራ መንግስት ”የነጻነት ቀን ” ብሎ የኢትዮጵያን ግዙፍ ጦር ደምስሶ የሀገሪቱን ነጻነት ማስከበሩንና በጦርነቱ መስዋዕትነት የከፈሉ ”መስዋእት” የሆኑ ኤርትራውያንን 23 ጊዜያት አስመራ ውስጥ ሲከበር ተመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ደግሞ የዛኑ ያህል ግንቦት 20 እየተባለ ”በአፍሪካ ግዙፉን ሰራዊት” ደምስሰን ለድል በቅተናል የሚሉ ታጋዮችና ደጋፊዎች ከልብ የሚያከብሩትን የድል ቀን እየተመለከቱ አድገዋል፡፡
የእነዚህ ወጣቶች ወላጆች ከማልያቸው በስተቀር በመልክና በቀለም አይለያዩም፡፡ ለሀገራቱ ከ28 አመታት በኋላ ለምስራቅና መካከለኛ የአፍሪካ እግርኳስ ዋንጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ባህርዳር ስታዲዮም ሲገቡ ፤ በየትኛውም የአህጉርና ዓለም አቀፍ የእግርኳስ ቡድኖች በየቡድናቸው ከሚነሱበት የፎቶግራፍ አነሳስ ይለይ ነበር፡፡ እንደ አንድ ቡድን ተቀላቅለውና ተዛንቀው አብረው ተነስተዋል፡፡
የዚህች ፎቶግራፍ አነሳስ ፖለቲከኞቹ ቢያደርጉት ፤ ለፖለቲካ ፍጆታ ነው ብሎ ቢጣጣል አይገርምም፡፡ በወጣቶቹ ዘንድ አንድ ከቃላት በላይ ማንም የማይበጥሰው በጎ የወንድማማችነት መንፈስ መኖሩን የምትጠቁም ድርጊት ናት፡፡ ሁለቱም የሀገራቸውን አሸናፊነትና ክብር መንፈስ የጠበቀ የመሸናነፍ ጨዋታ ተጫውተው እኩል ለእኩል ወጥተዋል፡፡
የሁለቱን ሀገር ህዝቦች የወዳጅነትና የወንድማማችነት መንፈስ በእነዚህ ወጣቶች የተገለጸው በቃል ሳይሆን በድርጊት ነበር፡፡ ያቺን ፎቶግራፍ የወጣቶቹ ”ስሌት” ሳትሆን ”ስሜት” የምታሳይ የልብ ቅኝት ማለት ይቻላል፡፡
እንዲህ ያለው የሁለቱ ሀገራት ወጣቶች በጎ መንፈስ ማሳደግ፤በውስጣቸው አንዱ ስለሌላው እንደራሱ ሀገር እንዲያይ ብሩህ አተያይ ማስረጽ ፤ የሁለቱን ሀገሮች ሰላም፣ደህንነትና ልማት ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ትልቅ በረከት ይሆናል፡፡
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተፈጠረው ግጭት የውስጥ ምክንያቶች ብቻ አድርጎ መውሰድ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ ላለፉት 30 አመታት የተዋጉት የራሳቸውን ጦርነቶች ብቻ አልነበረም፡፡ የእብድ ገላጋይ ሆነው የሁለቱ ህዝቦች እትብት እስከነአካቴው ብጥስጥሱ ወጥቶ ዳግም የማይተያዩ ፍጹም ጠላት እንዲሆኑ የውጭ ኃይላት የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ሲነጣጠሉ ፤ ሁለቱን ነጣጥሎ ለመምታት ብሎም በሁሉም አውደ ግንባሮች የደቀቁ እንዲሆኑ ያልተሰራ ሴራ የለም፡፡የሀገራችን የፖለቲካ ዘር ዘመም ልዩ ነት ከመጠን በላይ መራገቡ ፤ የአዛውንት ፖለቲከኞቻችን በአንድ ወቅት ”አሸነፊ” ሆነንበታል በሚሉት መንገድ በመሄዳቸው ብዙ ጥፋቶች ደርሰዋል፡፡ አሁንም መማር አልተቻለም፡፡
ከኤርትራ ጋር መልካም ግንኙነት መኖሩ በቅድሚያ የሚጠቀመው በአቅራቢያው ያሉ የሀገራችን ህዝብ ብሎም ለመላው ኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ ጥቅም፣ደህንነትና ብልጽግና መሆኑ አይካድም፡፡ ለሰላምንና ለእድገት ከተሰራ ልክ እንደሰንሰለት ተያያዠ ሆኖ ከዳር ወደ ማህል ይመጣል፡፡
ግጭትና ጦርነትን እንደ ችግር መፍቻ ዘዴ አብዝተን የምንሰብክና ከቀጠልንበት ከዳር ወደ ማህል እየሰፋ ይሄድና ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ መዋጋት የሌለባቸው የወጣቶቻቸውን ህይወት የሚቀጥፉ፤ ህዝባቸውን የችግር አዙሪት ውስጥ የሚከቱ የአጥፍቶ መጥፋት ጨዋታ ውስጥ አሸናፊ ባለመኖሩ ነው፡፡ በቀጣይ መስራት ያለባቸው እስካሁን ያልሞከሩትን መንገድ ነው፡፡ የሄዱበትን የጦርነትና ግጭት መንገድ ቀየረው፤ እጅግ የሰነፉበትን የሰላም፣ የትብብርና የአንድነት መንገድ ወጣቶቻቸው እንዲበረቱበት ከመቼው በበለጠ ዛሬ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡