አዲሱ የኮሮና (ዴልታ ቫይረስ) የኮቪድ ክትባትን ማምለጥ ይችል ይሆን?
~ የኮቪድ ክትባት የወሰዱም ያልወሰዱም ሰዎች ሊያነቡት የሚገባ፣
(በዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ)
ይህ የወረርሽኝ ወቅት ያልፋል እያልን ብንጠብቅም፣ አሳሳቢ የሆኑ ነገሮች መከሰታቸው አልቀረም፡፡ በአብዛኛው ከራሱ ከሰዎች ባህሪ የሚነሳ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ የኮሮና ቫይረሰ ሥርጭቱን በቀጠለ ቁጥር አዳዲስ ዝርያዎች እየፈጠረ እንደሚሄድ ከተገነዘብን ቆይተናል፡፡ አዲስ የሚፈጠሩት ቫይረስ ዝርያዎች ቁጥር ሥፍር የላቸውም፡፡
ከነዚህ መሀከል ግን በኣሳሳቢነት ደረጃ የሚመደቡ አሉ፡፡ አለም አቀፉ የጤና ደርጅት የነዚህን አሳሳቢ ቫየረስ ዝርያ ቁጥር ወደ አስር ከፍ አድርጎታል፡፡ አሳሳቢ ተብለው የሚመደቡት የባሕሪ ለውጥ ሲያሳዩ ነው፡፡ እነዚህ ባህሪያት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡
በመጀመሪያ አዲሱ ዝርያ ቀድሞ ከመጣው ዝርያ በበለጠ በፍጥነት መሠራጨት ሲችል ነው፡፡ አሳዛኝ ሆኖ አዳዲሶቹ ቫይረሶች በዚህ የተካኑ ናቸው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ፣ ህምም የማስከተል ጉልበቱ ይጨምራል ወይ፣ የመግደል ችሎታው ይጨምራል ወይ፡፡ ሌላው ከፍተኛ አደጋው ደግሞ አሁን በመሠጠት ላይ ያሉ ክትባቶችን ማምለጥ ይችላል ነው ወይ፡፡
አሳሳቢ የሚባሉት አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች፣ ከዚህ ቀደም የሚጠሩት መጀመሪያ በተገኙበት አገር ነበር፡፡ ሆኖም በአገር ሥም መጥራቱ ችግር አለበት ተብሎ፣ ቫይረሶቹ በግሪክ ፊደላት መጠራት በመጀመራቸው ግርታ ፈጥረዋል፡፡
ለአንባቢ ማስታወስ እንደሚች የሚቀጠለውን ሠንጠረዥ አቅርቤያለሁ፡፡ ቫይረሶች በሳይንሳዊ መጠሪያቸው በአሃዝና በእንግሊዝና ፊደላት ነው የሚታወቁት፡፡
ሳይንሳዊ ከዚሀ በፊት አዲስ መጠሪያ
B.1.1.7 የኢንግላንድ አልፋ
B.1.351 የደቡብ አፍሪቃ ቤታ
P.1 የብራዚል ጋማ
B.1.617.2 የህንድ ዴልታ
B.1.429 ኤፕሲሎን
B.1.526 አዮታ
ዴልታ የተባለው አዲስ መጤው ቫይረስ፣ ጉልበቱን ከማሳየት ወደ ኋላ አላለም፡፡ በስፋት በመሠራጨት ላይ ያለው ቫይረስም አሱው ነው፡፡ በኢንግላንድ ባለው የኮሮና ሠርጭት ዘጠና ከመቶ በዚህ ቫይረስ ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ እንግሊዝ ሙሉ በሙሉ ከመክፈት ዘግየት እንድትል የተገደደችው፡፡
በአሜሪካ ደግሞ እሰከ ትላንትና ድረስ፣ ከዚህ ቀደም ሰባት በመቶ የነበረው የዚህ የዴልታ ቫይረስ ሥርጭት ወደ ሀያ ከመቶ አድጓል፡፡ ይህ አሃዝ እይጨመረ አንደሚሄድና ይህ ዴልታ ቫይረስ እንደ ኢንግላንድ ሁሉ ሥርጭቱን ሊቆጣጠረው ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡
ይህ ቫይረሰ ወደ አሳሳቢነት ደረጃ ከተሸጋገረ ቆይቷል፡፡ ለምን ቢባል፤ በከፍተኛ ደረጃ ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ እንደሚቸል በማስመሰከሩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ የበሽታና የመግደል ችሎታውም ጨምሯል፡፡ ሌላው ችግር ወይም አሳሳቢነት ደግሞ ይህ አዲስ ቫይረስ በአሁኑ ወቅት በመሠጠት ላይ ያሉ ክትባቶችን ማሸነፍ ወይም ማምለጥ ይችል ይሆን የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ምላሽ ጥናቶች ተደርገው የቀረበውን ውጤት ላካፍላችሁ፡፡ በዚህ ቫይረስ ላይ ጥናት የተደረገው በፋይዘርና በአስትራ ዜኔካ ክትባቶች ላይ ነው፡፡ አገር ቤት የሚሠጠው የአስትራ ዜኒካው ክትባት ነው፡፡
ሁለቱም ክትባቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሠጡ በኋላ በተደረገው ጥናት እነዚህ ክትባቶቸ በዴልታ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ወደ በሽታ እንዳይቀየር የማድረግ ችሎታቸው 33 ከመቶ ነበር (33%). እንደሚታወቀው በቂ መከላከያ ለማግኝት አነዚህ ክትባቶች ሁለት ጊዜ ነው የሚሠጡት፡፡
እናም ሁለተኛው ክትባት ከተሠጠ በኋላ፣ በዴልታ ቫይረስ ምክንያት የበሽታ ስሜትን የማሰጣል ችሎታቸው በፋይዘሩ ክትባት በኩል ወደ 88 በመቶ 88% ሲያድግ በአስትራ ዜኔካው ክትባት በኩል ደግሞ ወደ 60 ከመቶ 60% ከፍ ብሏል፡፡
ነገር ግን በዴልታ ቫይረስ አማካኝነት ሰዎች ወደ ሆስፒታል እንዳይገቡ የመከላከል ችሎታ ሲታይ ክትባቶቹ የሚያረጋጋ ውጤት አሳይተዋል፡፡ ሰለዚህ ከሁለት ክትባቶች በኋላ፣ የፋይዘር ክትባት 96 በመቶ 96% ሰዎች በህመም ምክንያት ሆሰፒታል የሚያስገባ ደረጃ እንዳይደርሱ የሚያደርግ ሲሆን፡፡ የአስትራ ዜኒካውን ደግሞ በ92 በመቶ 92% የማሰጣል ወይም የመከላከል ችሎታ እንዳለው ተገልጧል፡፡
ይህ መረጃ ከኢንግላንደ በኩል የሕዝብ ጤና ካደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ የተገኘ ነው፡፡ ክትባት ለወሰዱ ሰዎች ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ምንም እንኳን በዘገባው የፋይዘሩ ክትባት ቢገለጥም፣ ሌላው ሞደርና የተባለው ክትባት በአሠራር ከፋይዘሩ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ተመሳሳይ የመከላከል ችሎታ ሊኖረው እንደሚችል ነው የሚጠበቀው፡፡
ክትባትን ካነሳን፣ ሰለ ብራዚል ጥቂት ልበል፣ ብራዚል ዜጎቿን ከትባ እንደነበር ይታወቃል፣ የሠጠችው ክትባት ደግሞ አሰትራ ዜኔካና የቻይናውን ሳያኖቫክ ነበር፡፡ ሆኖም ሥርጭቱ በመቀጠል በዚህ ጊዜ የብራዚል በኮቪድ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር አምስት መቶ ሺ ተሻግሯል፡፡
ወደ አሜሪካ ስንመለስ ቀደም ብሎ የተጠቀሰው የአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እየጨመረ የመጣው በበቂ መጠን ክትባት ባልተሠጡበት አካባቢዎች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሥርጭቱ መጠን ዝቅ እያለ ቢመጣም በነዚህ ክትባትለ ባልወሰዱ ሰቴቶችና አካባቢዎች የኮቪድ ሥርጭትና ህሙማን ቁጥር እንደገና እያንሠራራ ይገኛል፡፡
ሌላው መልካም ውጤት ደግሞ ክትባት የወሰዱ ሰዎች ያገኙት ጠቀሜታ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በኮቪድ ምክንያት ህይወታቸው እያለፈ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ በጥልቀት ሲታይ ምንም እንኳን በየቀኑ የሚሞተው ሰው ቁጥር ከሶስት መቶ በታች ቢወርድም አብዛኞቹ የሚሞቱት ሰዎች ክትባት ያልወሰዱ ናቸው፡፡ በአሃዝ ሲገለፅ፣ መረጃው የተገኘው አሶሴትድ ፐሬስ ሲዲሲ ከሰጠው ሪፖረት በመነሳት ካቀቀናጀው ዘገባ ነው፡፡
ባጠቃላይ በኮቪድ ምክንያት ወደ ሆሰፒታል ከገቡ ከ 853ሺ ህሙማን መሀከል 1200 ብቻ ክትባት የወሰዱ ናቸው፡፡ ይህ ሰበር ኮቪድ (Breakthrough infection) የሚባለው ሁኔታ ነው፡፡ በንፅፅር ሲታይ ከመቶው (0.1 %) ብቻ ነው፡፡ በኮቪድ ምክንያት ከሞቱ ሰዎች ሲታይ ከ18ሺ መሀከል 150ዎች ብቻ ከዚህ ቀደም ሙሉ ክትባት የወሰዱ ናቸው፡፡ ይህም ከመቶው 0.8 % ነው፡፡
መታወቅ ያለበት የሚሠጡት ክትባቶች በመቶ ፐርሰንት መከላከል እንደማይቸሉ፡፡ በተጨማሪም ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች አኩል የመከላከል ችሎታ ምላሽ እንደማይሠጡ ነው፡፡ ከነዚህ መሀከል በዕድሜ የገፉት እንደጎልማሶቹ ምላሽ ሰለማይሠጡ የመከላከል ችሎታው በንፅፅር ይቀንሳል፡፡
ሌሎች የሰውነት የመከላከያ አቅማቸው በበሽታ ወይም በመድሀኒት ምክንያት የደከመባቸው ሰዎች በተለይም አንዳንዶች ክትባት ቢወሰድም በቂ ምላሽ ቀርቶ ምንም አይነት ምላሽ እንደማይኖራቸው ይታወቃል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ የቫይረሱ ሥርጭት ከኣሳሳቢነት ደረጃ አስኪወጣ ድረስ እነዚህ የተጠቀሱት ሰዎች ክትባት ቢወስዱም፣ ከዚህ በፊት ሲያደርጉት የነበረውን ጥንቃቄ መከተል አለባቸው የምንለው፡፡
ሌሎችም ቢሆን እነዚህ የቤተሰብ አባላት የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ አልፎ ሊሄድ በሚችል ነገር በመጨረሻዋ ሰአት ጉዳት እንዲደርስ አለማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ምንም እንኳን ሙሉ ክትባት ቢወስዱም በዕድሜ የገፉ ሰዎችና የሰውነት መከላከያ አቅም የሚያደክም በሽታ ያለባቸውን ወይም መድሀኒቶችን የሚወስዱ ሰዎችን በግድ ድግስና ስብስብ ላይ ካልተገኛችሁ ብሎ መወትወት ተገቢ አይደለም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ እነሱን መከላከሉና መጠበቁ ሰብአዊ ነው፡፡
የክትባት ጠቀሚታው በግልፅ በታየበት ሁኔታ፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ድርጅቶች ማስገደድ ባይችሉም የግል ድርጅትና ቀጣሪዎች ግን ሠራተኞቻቸውን የኮቪድ ክትባት አንዲወሰዱ ማስገደድ ጀምረዋል፡፡ በቴክሳስ የሚገኝ ትልቅ የጤና ድርጅት ይህንን ግዴታ ተግባራዊ በማድረጉ ወደ 150 የሚሆኑ የኮቪድ ክትባት አንወስድም ያሉ የጤና ባለሙያ ሠራተኞች ወይ በገዛ ፈቃዳቸው አለዚያም ከሥራ እንዲለቁ ተደርገዋል፡፡
ከነዚህ መሀል መብታችን ተደፈረ በማለት ክስ ያቀረቡ ሠራተኞችን የፍርድ ቤት ዳኛው ውድቅ እንዳደረገባቸው ተዘግቧል፡፡ ሥራ የለቀቁት ሠራተኞች ያላስተዋሉት ነገር፣ አዲስ የሚቀጥራቸው መስሪያ ቤት ካልቸገረው በስተቀር እንዴት ብሎ ሊቀጥራቸውስ ይችላል፡፡
በሌላ በኩል፣ ክትባት አንወስድም ግን ሥራ መቀጠል አለብን፣ ቤተክርስቲያን ወይም የዕምነት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ይክፈቱልን ሲሉ፣ በሌሎቹ ክትባት በወሰዱና ተገቢውን ጥንቃቄ በሚያደርጉ በአብዛኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚፈጠረውን ስሜት ያገናዘቡ አይመስልም፡፡ የተከተቡ ሠራተኞችም ቢሆን እንድ ቀን ሁሉ ምን በወጣን እንጋለጣልን ካልተከተቡት ጋር አብን እንሠራም የሚሉበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም፡፡
አንከተብም የማለት መብታቸው የተጠበቀ ቢሆንም በነሱ ምክንያት አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል እያወቁ ከህብረተሰቡና ከቤተሰብ ጋር ለመቀላቅል መፈለጋቸው አጠያያቂ ነው፡፡ እንግዲህ እስካሁን ክትባቱን ያልወሰዱ ሰዎች፣ በሥራ ቦታ ወረርሽኙ እስከሚያልፍ ድረስ የግድ ማስክ ማድረግ እንዳለባቸው ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገፅ የተቀመጠውን ንባብ ይመልከቱ፡፡
ማሳረጊያው ምክር፣ አሁን ዴልታ ቢሆንም፣ ነገ የሚመጣው ወይም የሚፈጠረው አዲስ የቫይረስ ዝርያ ባህሪ እየከፋ እንጂ እየለዘበ አይሄድም፡፡ ሰለዚህ አዲስ የቫይረስ ዝርያ የሚፈጠረው ደግሞ ሥርጭቱ በቀጠለ መጠን መሆኑን በመገንዘብ፣ ሁላችንም የዚህ ቫይረስ ሥርጭት ለመግታት መጣር አለብን፡፡
በነገራችን ላይ ዴልታ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሰማንያ አገሮች ውስጥ የተሠራጨ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡
via Gosh Health
Dr. Gebeyehu Teferi, MD is an Infectious Disease Specialist in Washington, DC, and has over 34 years