Connect with us

የመቅደላ ስንብት-ሚያዚያ 

የመቅደላ ስንብት-ሚያዚያ
ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

የመቅደላ ስንብት-ሚያዚያ 

የመቅደላ ስንብት-ሚያዚያ 

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በዛሬው ቀን የሆነውን የመቅደላ ጦርነትና የዳግማዊ ቴዎድሮስ ስንብት ከጦርነቱ አውድ ጋር እያነሳ እንዲህ ይዘክረዋል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

የመቅደላ አምባ ከግዙፍ አውሮጳዊ ሠራዊት ጋር ተፋጧል፡፡ አስቀድሞ እንደ ታላቋ ንግሥት ታላቅ ሀገር ለመስራት የወጠነው ንግሥ የሥርዓትን ጥቅም የተረዳ ነበር፡፡ በሥርዓት ከመጣና ሥርዓት ከገዛው ሠራዊት ጋር ከመፋጠጡ ቀድሞ ህልሙን ሁሉ እውን እንዳያደርግ ብዙ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ ይህ የመጨረሻው ፈተና ነው፡፡

በ669 መርከቦች ተጭኖ የመጣው የእንግሊዝ ሠራዊት 983 መድፈኛ ወታደሮች ያሉት ነው፡፡ የእግረኛው ሠራዊት ብዛ 10‚231 ሲሆን 2‚064 ፈረሰኛ ወታደር አብሮ ተሰልፏል፡፡ ከአራት ሺህ በላይ ፈረሶች፣ ከአስራ ስድስት ሺህ የሚበልጡ በቅሎዎች፣ ከሺህ አምስት መቶ የሚበልጡ አህዮች ከአምስት ሺህ የሚልቁ ግመሎች መድፍ ተሸካሚ በሆኑ አርባ አራት ዝኆኖች ታጅበው ከናፒር ጋር ተሰልፈዋል፤ የአቢሲኒያን ንጉሥ ሊገጥሙ መቅደላ፡፡

ሚያዚያ 2 ቀን ምሽት ገደማ የቴዎድሮስ ሠራዊት በከበበው የእንግሊዝ ጦር ላይ ተኩስ ከፈተ፡፡ በፊታውራሪ ገብርዬ የሚመራው አምስት ሺህ ገደማ ጦር በእንግሊዝ ጦር መድፍ ታመሰ፡፡ በዚህ ውጊያ የንጉሠ ነገሥቱ ቀኝ እጅ፣ ገብርዬ፤ ፍንጭቱ ፊታውራሪ ወደቀ፡፡

ብዙ የጭንቅ፣ የግንኙነት፣ የምክርና የተኩስ መመላለስ አልፎ ሚያዚያ ስድስተኛው ቀን ነጋ፡፡ ገና ሳይረፍድ ጸሐይዋ ዙሪያዋን በጥቁር ክበብ ተከባለች፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ “ይህ ነገር የደም መፍሰስ ምልክት ነው” አሉ፡፡

ጄኔራል ናፒር ውጊያውን እኩለ ቀን አስጀመሩት፡፡ የእንግሊዞች መድፍ ከዝኆን ጫንቃ ወርዶ የመቅደላን አምባ አናወጠው፡፡ አምባው ተደበደበ፡፡ ምድር ተናወጠች፡፡ የኮሎኔል ፊልድ አስረኛው የእግረኛ ብርጌድ የፋላ ኮረብታን ያዘ፡፡

 

እንዳሉትም የባለ ህልሙ መጨረሻ የደም መፍሰሱ ቀን ሆነ፡፡ እጅ ስጡ ተብለው የተማከሩት ንጉሥ በሰው እጅ መውደቅን ነውር አድርገውት በእግዜር እጅ ብወድቅ ይሻለኛል ብለው ተናገሩ፡፡ 

ቀኑ ሚያዚያ ስድስት ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ እንደ አማረባቸው ናቸው፡፡ የሚያምረውን ህልም እውን ባያደርጉም ከነሞገሳቸው ይታያሉ፡፡ ወርቀ ዘቦ ዝምዝም ልብስ ያጌጠ ሀር ለብሰዋል፡፡ የአንበሳ ለምድ አድርገዋል፡፡ በወገባቸው ጎራዴና ሽጉጥ ታጥቀዋል፡፡ 

ሲወድቁ የታየው ልብሳቸው የተቀየረው፡፡ አምባው አናት ቆመው በተተኮሰ ጥይት በመሳታቸው በልብስዎት ተለይተዋል የሚለውን ምክር ሰምተው ነው፡፡ ከዚያ ነው በጥጥ በተሰራ ሱሪ ሀር ሸሚዛቸውን የቀየሩት፡፡ እንዲህ ሆነው እስከ ቋቲት በር ታዩ፡፡ ከዚያ ወደ አምባው ሜዳ ወጡ፡፡ እስረኛውን ለቀቁት፡፡

ከቀኑ አስር ሰዓት ከአስር ደቂቃ ሲሆን ይላል ጳውሎስ ኞኞ ስምንት ሰዓት የተጀመረው ውጊያ ያበቃ ዘንድ እጅ ስጡ የተባሉት ንጉሥ ለራሳቸው ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፡፡ ያኔ ነው ወንድ አለራስዎ ገለውም አያውቁ የተባለው፡፡

ራሳቸውን በመቱበት ሽጉጥ ሲወድቁ ድምጹን የሰሙ የአይሪሽ ወታደሮች በርረው ደረሱ፡፡ ከአልሞተው ንጉሥ ላይ ቀለበትና ሀብል ፈቱ፣ አምባው በወደቀው ንጉሥ ደም የተበከለ ሸሚዝ የይገባኛል ጭቅጭቅ የፈረንጅ አፍ ተሰማበት፡፡ 

ገደለን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፤ አለ ሀበሻ፡፡ እነሆ በዛሬው ቀን ለሀገሩ አንድነትን ስልጣኔን ሥርዓትንና ብልጽግናን የሚመኝላት ንጉሥ እንደባተለ በምኞቱ አምባ በመቅደላ ወደቀ፡፡

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top