ʺጨዋታ ሲመስለን ታምር ሆኖ ፍቅር አለበሰን”
በሰላም መድረክ ከፍ ያለው ሰንደቅ፣ በጋራ እንድንስቅ በጋራ እንድንቦርቅ አደረገን፡፡ ምድር ጠበበችን፣ ደስታ አሰከረችን፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ አምሳለ ቀስተ ደማናው በሰማይ ላይ ሲውለበለብ ልቦች በደስታ ዘለሉ፣ ዓይኖች በደስታ እንባ ተመሉ፣ አንደበቶች በኢትዮጵያዊነት ቃለ መሀላ ተማማሉ፡፡ ቀዳሚ ተራማጅ፣ ዘመናዊነትን አለማማጅ፣ በፍትሕ ፈራጅ፣ ጥንቁቅ እና ምጡቅ የሆኑ ሕዝቦችን የአደራ ቃል የያዙ ልጆች በአቢጃን ሰማይ ሥር ቃላቸውን ለመፈፀም ይተጋሉ፡፡
ʺ ቃል የእምነት እዳ ነው” እንዳሉ ቃላቸውን ካልፈፀሙ የሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ልብ እንደሚከፋ ያውቁታል፡፡ አደራው ከባድ ነው፡፡ ቃሊ ኪዳኑ እዳ ነው፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በቴሌቪዥን መስኮት ልጆቻቸውን አሻግረው እየተመለከቱ ʺ አቤቱ እርዳቸው፤ ደግፋቸው” እያሉ ይማፀኑላቸዋል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ከጨዋታ በላይ ታላቅ አደራ አለባቸው፡፡ ፍቅር፣ ተስፋ፣ እምነት፣ ቃል፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያውነት፤ ሰንደቁን ሰጥተው፣ ልባቸውን አጽንተው፣ የሰንደቁን ውብ ቀለም ተቀብተው አደራ ብለዋቸዋልና፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ተስፋ በሌለበት የጥቁር ዓለም ተስፋ ሆነች፡፡ የጥቁር ዘር በጡጫና በእርግጫ እየተረገጠ ከሰውነት አንሶ፣ ነጭን እንግሶ ይኖራል፡፡ እንደ ሸቀጥ ይሸጣል፣ ይለወጣል፣ መከራው ፀና፣ የተስፋ በሮች ሁሉ የተዘጉ መሰሉ፡፡ ታዲያ በዚያ ዘመን ʺፈጣሪዋን ጠብቀኝ ማረኝ፣ አንድ አድርገኝ መከራን አሻግረኝ እያለች የምትማጸን፣ ጌታዋን በፀሎት ኤሎሄ የምትል፤ ጠላቷን ደግም በጥይት የምታቃጥል” ኃያል ሀገር ነበረች፡፡ በፈጣሪዋ ትመካለች፣ ሕጉን ታከብራለች፣ በትዕዛዙ ትመራለች፤ ጠላቷን አሻፈረኝ ትላለች። በታሪክ፣ በጥበብና በሁሉም ነገር ከዓለም ቀድማለች፡፡
ተስፋ በጠፋበት የጨለማ ዘመን ተስፋ ሆነች፡፡ እንደ ሕልም ርቆ የሚታዬውን የጥቁር ተስፋ አቅርባ እውን አደረገችው፡፡ በአፍሪካ ምድር ያጠላውን የጨለማ ዘመን በብርሃን ገላለጠችው፡፡ ለጥቁር ዘር ሁሉ ዋስ ጠበቃ ሆነችው፡፡ በጭንቁ ዘመን ቤዛ ሆነችው፡፡ በብርሃን ዘመን፣ በብርሃን መንገድ፣ ወደብርሃን ተራራ እንዲገሰግስ አደረገችው፡፡ ከእያንዳንዱ የጥቁር ተድላና ደስታ፣ አንድነትና እኩልነት፣ ነጻነትና ምኞት በፊት የኢትዮጵያ እጅ አለበት፡፡ የሁሉም ምንጭ እርሷ ነችና፡፡
ዓለም አደነቃት፣ ጥቁሮች አመሰገኗት፣ ነጮች ፈሯት፣ አከበሯት፣ ዘመን ዘመንን እየተካ ሄደ፡፡ ይህችው ዘመናዊት የሆነች ሀገር በተናጠል እየተገኙ እንደ እባብ ይቀጠቀጡ የነበሩ አፍሪካዊያንን የሚያስተሳስርና አንድ የሚያደርግ ዘዴ ይኖር ዘንድ ፈለገች፡፡
ግርማዊ ቀደማዊ ኃይለ ስላሴ ከአልጋ ወራሽነት ወደ ንጉሠ ነገሥትነት አልፈው በአስፈሪው ዙፋን ተቀምጠውበታል፡፡ የታላቅ ሕዝብ መገኛዋን አፍሪካን እንድ የሚያደርግ ነገር ለመፍጠር ማሰላሰል ላይ ናቸው፡፡ በውጩ ዓለም እግር ኳስ ጨዋታ ተዘውታሪ ሆኗል፡፡ ሰዎች ይሰባሰቡበታል፣ ይደሰቱበታል፣ ፍቅራቸውን ያንፁበታል፡፡ በአፍሪካም ይህ ነገር እየተለመደ ነው ፡፡ አንድነት ግን አልነበረውም፡፡
ኢትዮጵያም በ1943 ዓ.ም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አቋቋመች፡፡ እግር ኳስ ጨዋታ ብቅ ብቅ ማለት ጀምሯል፡፡ የሀገራት ጨዋታ ወደ አህጉር አድጎ መገናኛ እንዲሆን ሀሳብ ተጠነሰሰ፡፡ አብዛኛዎቹ ሀገራት በቀኝ ግዛት ማንነታቸውን ስላጡ የሚወክላቸው ብሔራዊ ቡድን ማቋቋም ተስኗቸዋል፡፡ በዚያም ላይ ጉዳዩን ትኩረት የሰጠው አልተገኘም፡፡ ያም ሆኖ ሀሳቡ መልካም ነውና ሰፋ፡፡ ኢትዮጵያ የጠነሰሰችውን ሀሳብ ሱዳንና ግብፅ ገቡበት፡፡ ደቡብ አፍሪካም በጉዳዩ ላይ አለሁ አለች፡፡
በካርቱም ጉባኤ ተካሄደ፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ እንዲካሄድም ተስማሙ፡፡ ጉባኤውን ለመታደም የሄዱ ሀገራት ውድድሩ በዚያው እንዲጀምር ስለፈለጉ ብሔራዊ ቡድናቸውን ይዘው ሄዱ፡፡ ከጉባኤው መጠናቀቅ ከቀናት በኋላ ውድድሩ እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡
የሚሳተፉት ሀገራት አራት ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ፤ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ግብፅ ደግሞ ከሱዳን ጋር ተደለደሉ፡፡ ያለፈ ለዋንጫ ይደርሳል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በወቅቱ በነበረባት ችግር ከውድድሩ ተሰናበተች፡፡ ሦስቱ ሀገራት መስራች ሆኑ፡፡ የአፍሪካ ዋንጫም ተመሠረተ፡፡ ያ ዘመንም 1949 ዓ.ም ነበር፡፡ ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ ሀሳብ ጠንስሳ፣ የአፍሪካን ምድር በፍቅር አረስርሳ አንድ የማድረጊያ የፍቅር መድረክ እንካችሁ አለች፡፡ ከዚህ ምስረታ በኋላ አፍሪካዊያንን እንድ የሚያደርጉ ነገሮች ተመሰረቱ፡፡
ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇም ኢትዮጵያ ሆነች፡፡ ጃንሆይም በጨዋታው ተገኝተው ተመለከቱ፡፡ እግር ኳስ ታላቅ ክብር እያገኘ ሄደ፡፡ ኢትዮጵያ በመሰረተችው የአፍሪካ ዋንጫ የሚጠበቅባትን ያክል ውጤታማ ባትሆንም የአፍሪካ እግር ኳስ ሲነሳ ስሟን የሚዘል የለም፤ መስርታለችና፤ ፍቅር አምጥታለችና፤ የአንድነት መንገድ አሳይታለችና፣ ምልክትና ግርማ ሆናለችና።
ይባስ ባሎ በመካከል ለዓመታት ጠፋች፡፡ በቀለሰችው ጎጆ፣ በገመደችው የአንድት ገመድ፣ ባደመችውና በሳመረችው መድረክ አልገኝ አለች፡፡ ዓመት ዓመትን እየተካ ከኋላ የመጡ የአፍሪካ ሀገራት በመድረኩ ሲደምቁ መስራቿ አልገኝ አለች፡፡ ዛሬ ትመለሳለች ነገ ሲባል 31 ዓመታት እንደዘበት አለፉ፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ መድረክ የሚመለስ፣ ፍቅርን የሚያድረስ አንጀት የሚያረሰርስ ሥጦታ ተገኘ፡፡
በሰውነት ቢሻው የሚመሩት ዋልያዎቹ የናፈቅንን መድረክ፣ የራቀንን ፍቅር፣ የዘገየብንን የእግር ኳስ ክብር ዳግም መልሰው የድግሡ ተካፋዮች ሆኑ፡፡ ደስታ ወደር አጣ፡፡ ዝማሬ ደመቀ፡፡ ተስፋው ረቀቀ፡፡ ʺ በሠውነት ረቀቀ ኢትዮጵያዊነት” ተባለ፡፡ ዳግም ሌላ ዘመን መጣ፡፡ ኢትዮጵያ ከዚያ መድረክ ጠፋች፡፡ ድጋሜ ለመመለስ ጥረቷን ቀጠለች፡፡
እርሷ የመሰረተችው የአፍሪካ ዋንጫም ለ33ኛ ጊዜ ሊደረግ ካሜሮን ድግስ በመደገስ ላይ ናት፡፡ በዚያ ታላቅ ድግስ ለመገኘት አፍሪካውያን ሀገራት ውድድሮችን ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከዓመታት በኋላ በዚያ ድግስ ለመገኘት 90 ደቂቃዎች ብቻ ቀርተዋት ነበር፡፡ በአቢጃን ሰማይ ሥር ዋልያዎቹ የኢትዮጵያን እና የኢትጵያውያንን አደራ ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
ማሸነፍ፣ አቻ መውጣት ወይም ተሸንፈው ኒጀርና ማዳጋስካር አቻ መለያዬት ወይንም የማዳጋስካር መሸነፍ ኢትዮጵያን ወደካሜሮን ያስጉዛታል፡፡ ብዙ እድል፣ የበረታ ትግል፣ ደስ የሚል አንድነትና የኢትጵያውያንን ጸሎት ይዘዋል፡፡
ጨዋታው ተጀመረ፡፡ የኢትዮጵያውን ልብ ተንጠልጥሏል፡፡ ዋልያዎቹ በተከታታይ ባሳዩት ጥሩ አቋም ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በጥቂት ደቂቃ ግብ ተቆጠረባቸው፡፡ ጭንቀቱ በዛ፡፡ ሌላ ግብ ተቆጠረባቸው፡፡ እየባሰ ሄደ፡፡ እረፈት ሆነ፡፡ ወጎች ሁሉ ስለ ብሔራዊ ቡድኑ ሆኑ፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ተጀመረ፡፡ ጨዋታው እየተገባደደ ነው፡፡
ጌታነህ ከበደ ግብ አስቆጠረ፡፡ ውጤቱ ጠበበ፡፡ ተስፋ መጣ፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት ግብ ተቆጠረባቸው፡፡ ሌላ ጭንቀት፡፡ ሌላ ተስፋ ማጣት፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ማዳጋስካርና ኒጀር ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታቸውን ቀጥለዋል፡፡
የአይቮሪኮስትና የኢትዮጵያ ጨዋታ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት የመሀል ዳኛው ድንገተኛ ሕመም ገጠማቸውና ጨዋታው ተቋረጠ፡፡ ጭንቀቱ ቀጥሏል፡፡ የዋልያዎቹ ተስፋ በማዳጋስካርና በኒጀር ጨዋታ ላይ ወደቀ፡፡ ጨዋታውም 0ለ0 ተጠናቀቀ፡፡
የተንጠለጠሉ ልቦች በደስታ ዘለሉ፡፡ ለረጅም ደቂቃዎች ያፈጠጡ ዓይኖች በእንባ ተመሉ፡፡ ደስታ ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አሰበችው ተመልሳለችና ሠንደቁ ከፍ ብሎ ተውለበለበ፡፡ ጨዋታ ሲመስለን ታምር ሆኖ ፍቅር አለበሰን፡፡ ያ ድል ከጨዋታም ከተዝናኖትም በላይ ኖሯል ለካስ፡፡ ድሉ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ኩራትና ሕብረት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በየጎራው ሲታሰቡ የነበሩ ሀሳቦች ሁሉ ቀርተው የጋራ ደስታ የጋራ ፌሽታ ሆነ፡፡ ፍቅር ተመለሰ፡፡ አንድነት ነገሠ፡፡ ምድር በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ካባ ለበሰ፡፡
ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ንፍቅ ʺኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” ተባለ፡፡ ተዘመረ፡፡ የጠፋ የመሰለውን ፍቅር ሰጡን፡፡ የቀረ የመሰለውን ክብር አለበሱን፡፡ የላላ የመሠለውን የአንድነት ገመድ አጠበቁልን፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አደረጉት፡፡ በዚያ ሰማይ ኢትዮጵያ ከፍ አለች፡፡ አሸነፈች፡፡ ሠንደቋ በግርማ ተውለበለበ፡፡
ከፖለቲከኞች ይልቅ ተጫዋቾች እያዝናኑ አፋቀሩን፣ እያሳሳቁ አስተሳሰሩን፣ እያስደመሙ ጭንቀታችን፣ የመንደር ሀሳባችን፣ የጓሮ ወጋችንን አስረሱን፤ እኛም ጠንክሩና አጠንክሩን፣ አሸነፉና አስተሳስሩን፣ ንገሡና አስተደስቱን አልናቸው፡፡ እናንተ እያሸነፋችሁ፣ መዝሙሩ ሲዘመር፣ ሠንደቁ ከፍ ሲል ኢትዮጵያዊነትም አብሮ ከፍ ይላል፡፡ የእናንተ መጠንከር ከጨዋታ በላይ ነው፡፡ አሁን ግን ጨዋታ ሲመለስን፣ ፍቅር አልብሳችሁናልና እናመሰግናችኋለን፡፡
(ታርቆ ክንዴ ~ አብመድ)