የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አደገ
~ መቋቋሚያ አዋጁ ፀድቋል።
የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ማሳደግ ያስፈለገበትን ዝርዝር ሃሳብ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ሰጥዬ ትላንት በተካሄደው የምክር ቤት ጉባዔ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ ድርጅቱ ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዲያድግ የተፈለገበት ዋናው ምክንያት ድርጅቱ ሲቋቋም ከነበረው የበኩር ጋዜጣ ውጭ የራዲዮ፣ የቴሌቭዥንና የድረ ገጽ የመገናኛ አውታር ያልነበሩትና አሁን ላይ እነዚህን በማሟላት ስድስት የራዲዮ ጣቢያና ከ10 በላይ የማቀባባያ ጣቢያዎች ያሉት ፤ በአንድ ቋንቋ ብቻ የነበረውን ስርጭት በአምስት ቋንቋዎች መረጃ ማስተላለፉ፣ ከ700 በላይ ሠራተኞች በማስተዳደር የደሞዝና የካፒታል በጀትን ጨምሮ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የሚጠቀምና ሌላ ተጨማሪ የቴሌቭዥን ቻናል ለመክፈት ዝግጅት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
በውስጥ ገቢ ደረጃም ሲጀመር ከነበረው ከ10 እስከ 15 ሚሊዮን ብር በአሁኑ ወቅት እስከ 130 ሚሊዮን ብር ገቢ ማሳደጉንም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ድርጅቱ ወቅቱ ከሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ጋር የሚመጥን ስያሜና አደረጃጀት ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲዘጋጅ ድርጅቱ ወደ ኮርፖሬሽን ማደግ እንዳለበት በእቅድ ተይዞ ሲሠራ መቆየቱንም አስታውቀዋል፡፡ ድርጅቱ ወደ ኮርፖሬሽን ሲያድግ የበለጠ ሕዝቡን የማገልግል አቅም ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ድርጅቱ ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ማደግ ጋዜጠኞች የበለጠ ሙያዊ መርህን አክብረው እንዲሠሩ እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን እንዲያድግ ከሠራተኞች፣ ከምሁራን፣ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ተሞክሮ ለመውስድ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡
የቀረበውን ሃሳብ ተከትሎ የምክር ቤት አባላትም ሃሳብ አንስተዋል፡፡ አንድ ተቋም ወደ ኮርፖሬሽን ሲያድግ በራሱ በጀት እንዲተዳደር ይገደዳልና በቀጣይ እንዴት መሥራት ታስቧል፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የእንግሊዘኛ ቃላትን ቀላቅሎ መጠቀም ለምን አስፈለገ፤ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ በተቋሙ መቋቋሚያ አዋጅ ከማስቀመጥ ይልቅ በሌሎች ሕጎች መጠየቅ አይቻልም ወይ? የሚሉና ሌሎች ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡
በተነሱ ሃሳቦች ላይ የክልሉ ርእስ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሚለው መጠሪያ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መጠቀሙ ሚዲያው ዓለም አቀፍ ተቋም ለመሆን በእቅድ እየሠራ የሚገኝ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ በአፍሪካ፣ ከአውሮፓ፣አሜሪካና ሌሎች የዓለም ሀገራትም ዘጋቢዎች ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ወደ ኮርፖሬሽን ያደጉት የሀገር አቀፍና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም የሚሠሩትን ሥራ ታሳቢ በማድረግ በመንግሥት በጀት ይደጎማሉ፤ኮርፖሬት መሆን በመንግሥት በጀት ከመደጎም አይከልክልም ነው ያሉት፡፡
የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ሰጥዬ ድርጅቱ ወደ ኮርፖሬሽን ሲያድግ ዋና ዓላው ሕብረተሰቡን የበለጠ ማገልገል ነው፤ ሙሉ ወጪውን በራሱ እንዲሸፍን ከተደረገ ወደ ንግድ ተቋምነት ያዘነብላል፡፡ በመሆኑም ለሕዝብ የሚሰጠውን ጥቅም መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ድርጅቱ የራሱን ገቢ በማሳደግና በመንግሥት በጀት መደጎሙ ለሕዝብ ተገቢ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መቋቋሚያ አዋጅን በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል።(አብመድ)
ፎቶ :- የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ሰጥዬ