Connect with us

ኸረ ምን እየሆነ ነው?…ኸረ ወደየት እየሄድን ነው?

ኸረ ምን እየሆነ ነው?...ኸረ ወደየት እየሄድን ነው?
Photo: Social media

ማህበራዊ

ኸረ ምን እየሆነ ነው?…ኸረ ወደየት እየሄድን ነው?

ኸረ ምን እየሆነ ነው?…ኸረ ወደየት እየሄድን ነው?

(ጫሊ በላይነህ)

ዛሬ ጠዋት የሰፈር ጁስ ቤት ገብቼ ለአንድ ብርጭቆ ጁስ 38 ብር ስከፍል በጣም ደንግጫለሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ ዋጋው 25 ብር ገደማ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ የተጠየኩትን ሂሳብ እየከፈልኩኝ አስብ የነበረው ወርተኛው እንደምን እየኖረ ይሆን የሚለውን ነው፡፡ በየጥቃቅን ምክንያቱ ሽቅብ እየጎነ የመጣው የዋጋ ንረት እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡

አሁን አሁንማ በተለይ በቋሚ ወርሃዊ ደመወዝ የሚተዳደረው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ከዕለት ዕለት እየተሰቀለ በመጣው የዋጋ ንረት መኖር የማይችልበት ደረጃ መድረሱን መንግስታችን ተገንዝቦት ይሆን የሚል ገራገር ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ 

ከታላቅ ይቅርታ ጋር የማከብራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አሳሳቢ የሆነው የዋጋ ንረት ከወንዞች ልማት፣ ከሸገር ፕሮጀክቶች አጀንዳ በላይ ያሳሰባቸው ስለመሆኑ በግሌ ያየሁት ነገር አለመኖሩም ጭምር ያሳስበኛል፡፡

የሸቀጦች ዋጋ ጨመረ በተባለ ቁጥር የንግድና ኢንደስትሪ ቢሮዎች ነጋዴዎች ላይ ብቻ ጣታቸውን ከመቀሰር፣ “እርምጃ እወስዳለሁ” እያሉ ከማስፈራራት በዘለለ እውነተኛ ምክንያቱን መርምሮ መፍትሔ ለማስቀመጥ ዝግጁ አይመስሉም፡፡ ደግሞ እኮ ጩኸቱም የአህያ ባል ከጀብ አያስጥልም አይነት ነው፡፡

በአዲስአበባ ከተማ በቅርቡ 5 ሊትር ዘይት ከዚህ በላይ እንዳትገዙ ብሎ ንግድ ቢሮው በየሱቁ መሀተም ያዘለ እና የዋጋ ተመን የያዘ ደብዳቤ ለጠፈ፡፡ ይህ ደብዳቤ ለምስኪኑ ሕዝብ ምን አስገኘ ሲባል መልሱ ምንም ይሆናል፡፡ 

በአሁን ሰዓት በበርካታ የአዲስአበባ የሸቀጣሸቀጥና የሱፐርማርኬት መደብሮች ብትሄድ ባለ5 ሊትር የምግብ ዘይት አታገኙም፡፡ አልፎ አልፎ ቢገኝም ዋጋው ንግድ ቢሮው ከለጠፈው ጋር አይገናኝም፡፡

ወዳጄ ጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ በጻፈው አጭር መጣጥፍ ባሰፈረው ቁምነገር ስለዳቦ ዋጋ ንረት እንዲህ ይለናል፡፡”…በአዲስ አበባ ከፍተኛ የዳቦ እጥረት አጋጥሟል፣ ዳቦ አምራቾች አንድ ዳቦ ሶስት ብር ለመሸጥ ተገድድዋል፣ ነዋሪዎች በዳቦ ግራም መቀነስ እየተማረሩ ነው። ከ1680 ዳቦ ቤቶች ውስጥ 20 በመቶው ስራ አቁመዋል።

መንግስት የስንዴ ድጎማውን በማቆሙ ኩንታል ስንዴ ከ 1600 ብር የ600 ብር ጭማሪ አሳይቶ ወደ 2200 ብር ገብቷል።

ከዚሁ የስንዴ እጥረት ጋር በተያያዘ ሁሩታን ጨምሮ ቃሊቲ ዩኒቨርሳል፣ ሆራ እና ሃያት ያሉ ነባር የምግብ ማቀነባበሪያዎች ስራ አቁመዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት (ከጥቅምት እስከ መጋቢት ወር) በተለምዶ ስንዴ በበቂ መጠን የሚገኝበት ወቅት ቢሆንም የዘንድሮው እጥረት አነጋጋሪ ሆኗል። በተለይ ወደአዲስ አበባ  ስንዴ እየገባ አይደለም።

ምን እየሆንን ነው? ኑሮ ወዴት እየሄደ ነው? ኢኮኖሚው ምን ነክቶታል? ከዚህ በላይ የምንነጋገርበት ርዕሰ ጉዳይ አለ?”

አዎ ወደየት እየሄድን ነው የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ነው፡፡ ጎበዝ በጉዳዩ ላይ እስቲ በጨዋ ደንብ እንመከርበት? ሀሳብ እንስጥበት?

 

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top