Connect with us

የዶ/ር ተዋበች ቢሻው ሙያዊ ምክር ~ ስለኮቪድ

የዶ/ር ተዋበች ቢሻው ሙያዊ ምክር ~ ስለኮቪድ
የማኀበረሰብ ጤና አጠባበቅ ማኀበር

ነፃ ሃሳብ

የዶ/ር ተዋበች ቢሻው ሙያዊ ምክር ~ ስለኮቪድ

የዶ/ር ተዋበች ቢሻው ሙያዊ ምክር ~ ስለኮቪድ

በማኅበረሰብ ጤና አጠባበቅ የ50 ዓመት ልምድ ያላቸው ዶ/ር ተዋበች ቢሻው ኮሮናን አስመልክቶ የሰጡት ምክር እነሆ

የኮቪድ-19 መመሪያ አስፈፃሚው ማን ነው?

የኮቪድ-19 በሽታ በአገራችን ከተከሰተ ከመጋቢት ወር 2012 ጀምሮ ህብረተሰቡን ከበሽታው ለመከላከል የተለያዩ በሳይንስ የተደገፉ ዘዴዎችን እንዲጠቀም የጤና ሚኒስቴር ፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት ፣ የአገሪቱ የበላይ አመራሮች ፣ በአገር ውስጥ እና በዳያስፖራ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ፣ ቤተ እምነቶች እና የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ሲያስተምሩ ፣ ሲመክሩና እና ቅስቀሳ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

የአስቸኳይ ጊዚ አዋጅም ተደንግጎ አዋጁ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ተግባራዊ ሆኖ ቆይቷል፡፡ 

ከጤና ሚኒስቴር ሪፖርት እንደምንረዳው የአሁኑ ወቅት ከተመረመሩት ሰዎች እስከ 10 በመቶ በላይ በሽታው ተገኝቶባቸዋል፡፡ 

የሞትም መጠን እንዲሁ እየጨመረ ነው፡፡ ይህን በመገንዘብ እና ህብረተሰቡም በሽታውን ለመከላከል የሚያስችለውን ዘዴ፡ለመጠቀም የሚያሳየውን ቸልተኝነት አሳሳቢ በመሆኑ አዲስ መመሪያ በጤና ሚኒስቴር የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት መመሪያ ቁጥር. 30/2013  በማውጣት ህብረተሰቡ ማድረግ የሚገባውን የመከላከያ ዘዴዎች እንዲሁም የተጣሉ ግዴታዎችን በደንብ አብራርቶአል፡፡  ይህንንም መመሪያ በክብርት የጤና ሚኒስትሯ ለሕዝቡ በሚዲያ ገልጸዋል፡፡

አሁን ትልቁ ጥያቄ ለዚህ መመሪያ ተግባራዊነት አስፈጻሚው ማን ነው?? ይህ በመመሪያው ውስጥ ግልፅ አልሆነም!

ይህን ያልኩበት ዋናው ምክንያት ከመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ህዝቡ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ በሳይንስ የተደገፈ መረጃ ፣ ትምህርትና ምክር የተሰጠና እውቀቱ እንዲጨምር የደተረገ ቢሆንም ሁሉንም የበሽታውን መከላከያ ዘዴዎቸ በአንድ ላይ በአግባቡ እየተጠቀመ ያለው ሕዝብ ብዛት አሁንም በጣም አነስተኛ ነው፡፡

እርግጥ የማስተማሩ ዘዴ ሊሻሻል ይገባዋል፡፡

ሆኖም ግን በሽታውን ከባድነት እና ስርጭቱም እየጨመረ መሄዱን እያወቅን የወረርሽኙን መስፋፋት ለመከላከል የሚያስችሉ ቀላል የሆኑ  ዘዴዎችን ሕዝባችን ተግቶ ተግባራዊ ሲያደርግ አይታይም፡፡ እንዲያውም ከመጀመሪያው ጊዜ አሁን እየባሰበት ሄዷል፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ፡-

አብዛኛው ህዝብ  የመከላከያ ዘዴዎችን ላለመጠቀም የወሰነና እምቢተኛነቱን በሚያደርገው ቸልተኝነት እየገለፀ ያለ ይመስላል፡፡ ይህም፦

ሀ) ወይ ስለበሽታውና ስለአስከፊነቱ ስላልገባው፡ 

ለ) ወይም ያላዋቂ ድፍረት 

ሐ) ወይም ደግሞ በአሳዛኝና በሚያሳፍር  ሁኔታ በራሱ ፣  በቤተሰቡ እንዲሁም በማህበረሰቡ ላይ በመለገም እና ደንታ ቢስ በመሆነ ነው፡፡

ስለዚህ  አሁን ያለንበት ደረጃ የበሽታው ክብደትና ስርጭት እየጨመረ  በመሔድ ላይ  ያለ መሆኑን ተገንዝበን ይህን የወጣውን መመሪያ በአፅንኦት ተግባራዊ  እንዲሆን ከቀድሞው የተለየ፡ ስልት መቀየስ አለብን!

ለህዝብ ጤና እና ለሀገር ደህንነት ሲባል እኔ የሚጠቅም የሚመስለኝ ትምህርቱንና ምክሩን ሳያቋርጡ ዝምታውና ልመናው አብቅቶ በአገር ደረጃ የሚከተለውን የማስገደጃ እርምጃ መውሰድ መጀመር አለበት፡፡

1ኛ. በመጀመሪያ ስለመመሪያው በተለያዩ ቋንቋ ፣ በልዩ ልዩ መገናኛ ዘዴዎች ፣  በሚዲያ በተለይ በሬዲዮ እና ሶሻል ሚዲያ  እንዲሁም ቤት ለቤት በማስተማር ፣  ለከተማና ለገጠር ፣ ለልማት

ሠራተኞችና ለቀበሌ የጤና ሰራተኞች ጨምሮ ከአገር አቀፍ እስከ ቀበሌ ድረስ  በስፋት ሕዝቡን ማሳወቅ፡፡ 

2ኛ. ለተግባራዊነቱም እያንዳንዱ ሰው የውዴታ ግዴታ እና ተጠያቂነትና ሃላፊነት ያለበት መሆኑን ፣ መንግሥትም የማስፈፀም ሐላፊነትና ግዴታ እንዳለበትና እርምጃ እንደሚወስድ ዝግጁ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

3ኛ፡ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ደንብ የሚያስከብሩ ፣ ልዩ መለያ የተሰጣቸው ፣ በከተማና በገጠር በከተማው አስተዳደር እና በቀበሌ አስተዳደሩ የሚመደቡ  የደንብ አስከባሪዎች በበቂ ቁጥርና በስፋት አሰልጥኖ  መመሪያውን ለማስከበር መመደብና ማሰማራት  ያስፈልጋል፡፡

4ኛ፡ ማስክ ማድረግን በሚመለከት እነኝህ የደንብ አስከባሪዎች  በየትኛውም ቦታ ማንኛውም ማስክ ያላደረገን ሰው አስቁመው መታወቂያውን በትህትና ጠይቀው በመውሰድ መታወቂያው ወዲያው የሚመለስለት መሆኑን በቅድሚያ ግን ከአቅራቢያው ማስክ ሻጭ ሁለት ማስክ ገዝቶ አንዱን አድርጎ  ሁለተኛውን ለሌላ ጊዜ  መቀየሪያ እንዲሆነው ይዞ ለደንብ አስከባሪው በሚያሳይበት ጊዜ ብቻ መሆኑን ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ 

ሁሉም ሰው አሠራሩን በቅድሚያ እንዲያውቀውና የመተባበር ግዴታም እንዳለበት በሰፊው ስለሚተዋወቅ ይህ አሠራር እንዲሰፍን ህብረተሰቡ በሞላ መተባበር ብቻ ሳይሆን በባለቤትነት ግዴታው መሆኑን ተረድቶ ማገዝ ይገባል፡፡

5ኛ፡ ተገቢ ርቀትን ለማስከበር ደግሞ በመመሪያው የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ማንም ሰው ከሚገባው ርቀት ባነሰ ሲጠጋ  አትቅረበኝ በማለት ድምፅን ከፍ አድርጎ  የመናገር መብት አለው፡፡ ሕዝቡም ደንብ አስከባሪውም መመሪያውን የጣሰውን ሰው በማመናጨቅ ሳይሆን በእርጋታና በከበሬታ በመጠየቅ በመራቅ  እንዳለበት ማሳጣትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

6ኛ፡  ህዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ሁሉ ስፖርት ፣ ቀብር ፣ ሰርግ ፣ የኪነጥበብ ትርኢት ፣ መዝናኛ ፣ የመሳሰሉት ቦታ ደንብ አስከባሪ ተገኝቶ ዝግጅቱን ከሚያዘጋጀው ግለሰብም ይሁን ተቋም ፣ ቤተእምነትንም ጋር ጨምሮ በመሆን መምሪያውን በጋራ ማስከበር  ይገባቸዋል፡፡ ተጠያቂም ናቸው፡፡

7ኛ. ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በሞላ ባንኮች ፣ ምግብ ቤቶች ፣ የንግድ ተቋማት ፣ ቴሌ ፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ወዘተ… በማንኛውም የሥራ ሰአት መግቢያ በሩ ላይ በሥርዓት የተቀመጠ ውሃና ሳሙና ማኖር እና ተገልጋዩም መጠቀሙን ማረጋገጥ አለበት፡፡ 

ይህን የማያደርግ በመመሪያው መሰረት ይቀጣል፡፡ ደንብ አስከባሪዎች ይህን ተግባራዊ የማስደረግ ሀላፊነት አለባቸው፡፡

8ኛ. እጆችን አዘውትሮ በሚገባ በውሃና ሳሙና መታጠብ ፣ ውሀ ሳይኖር፡ በሳኒታይዘር ማፅዳት ከኮሮና ብቻ ሳይሆን ከብዙ የጤና ችግሮችም ሊከላከል ስለሚችል የዘወትር ልምዳችን ማድረግ አለብን፡፡ ለዚህ እያንዳንዱ ሰው ራሱን ተቆጣጣሪና ተገዢ ማድረግ አለበት፡፡

እንግዲህ ቸልተኛውም ሰው ሆነ ቸልተኛውን በዘፈቀደ በዝምታ የሚያሳልፍ ሰውም ሆነ ሃላፊ ፣ ሁለቱም ራስን ፣ ቤተሰብን ፣ ማህበረሰብን ፣  ህዝብን እና አገርን ይጎዳሉና የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመግታት ኃላፊነትን መወጣት የእያንዳንዱ ሰው ሰብአዊ መብትና ግዴታም ነው፡፡ ዛሬውኑ ቆርጠን እንነሳ፡፡ 

⚠️ ተለዋጭ በሌለው በህይወት መቀለድ ከስብእና በታች መሆን ነው፡፡

እግዚአብሔር ይጠብቀን! ቅን ልቦናና ማስተዋልን ይስጠን፡፡ አሜን!

(የማኀበረሰብ ጤና አጠባበቅ ማኀበር)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top